ከፑቲን ጋር የተወያዩት የአሜሪካ ልዑካን ወደ ዩክሬን ሊያቀኑ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሁለት የአሜሪካ ልዑካን በሞስኮ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተወያዩ ሲሆን በቀጣይም ወደ ዩክሬን እንደሚያቀኑ ተገልጿል።

ጦርነቱን ለማስቆም ከፑቲን ጋር ካደረጉት "ውጤታማ ውይይት" ጋር "ዕኩል የሆነ ውይይት" በዩክሬን እንደሚያደርጉ እንደሚጠብቁ ልዑካኑ አስታውቀዋል።

ልዑካኑ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር ዛሬ እሑድ ኪየቭ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ "የቀጣዩን ምዕራፍ ዕቅዶች በተመለከተ ቅዳሜ ዕለት ከፑቲን ጋር ትርጉም ያለው ውይይት አድርገዋል" ብሏል።

የውይይቱ ይዘት ይፋ ባይደረግም የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ በቀጣይ ሳምንት መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋነኛ ተደራዳሪ ልዑካን ወደ ዩክሬን መዲና ሲጓዙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ፑቲን እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለሦስት ቀናት ያህል አንዳቸው በሌላቸው መዲና ላይ ጥቃት ላለመፈጸም ተስማምተዋል።

ዊትኮፍ እና ኩሽነር በክሬምሊን ድርድር ሲያደርጉ፤ ዜሌንስኪ "ትርጉም ላለው ውይይት ዝግጁ ናቸው" ብለዋል።

ቅዳሜ በሞስኮ የተካሄደው ውይይት ሦስት ሰዓት ወስዷል። በሞስኮ በሚገኘው የፑቲን ይፋዊ መኖሪያ በምሥጢር የተከናወነ እንደሆነ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ዝርዝር መረጃዎች ገና ይፋ ባይደረጉም ሁለቱም ወገኖች ጠቅለል ባለ ሁኔታ በሰጡት አስተያየት አወንታዊ ምልክቶች ታይተዋል።

የፑቲን አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ውይይቱን "ገንቢ እና ፍጹም ግልጽ" በማለት ገልጸዋል።

"ውይይቱ የዩክሬንን ቀውስ በመግታት ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። የምጣሄ ሃብት ጉዳዮች እንዲሁም አሜሪካ እና ሩሲያን የሚመለከቱ የጋራ ጥቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች ላይም በዝርዝር ተወያይተናል" ብለዋል።

አማካሪው እንደተናገሩት "የሩሲያ ጦር በውጊያ አውድማው እያሳየ ያለው ግስጋሴ" በውይይቱ የተነሳ ሲሆን፤ "የግጭቱን መንስዔ" በተመለከተ ንግግሮች መደረግ እንዳለባቸውም በውይይቱ ተነስቷል።

ሩሲያ የዩክሬን መዲና ኪየቭን ጨምሮ በከተሞች ላይ የምታደርሰው የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት እየተባባሰ ቢሆንም፤ የእግረኛው ጦር እንቅስቃሴ ዝግ ያለ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2022 አንስቶ ሩሲያ የዩክሬንን አንድ አምስተኛ ግዛት ትቆጣጠራለች።

የአሜሪካ ልዑካኑ ኩሽነር እና ዊትኮፍ በተደጋጋሚ ወደ ሩሲያ ተጉዘዋል።

ከ2022 ወዲህ የዩክሬን የአየር ክልል ለበረራ ዝግ የተደረገ ሲሆን፤ ልዑካኑ በምን ሁኔታ ወደ ኪየቭ እንደሚገቡ ግልጽ አይደለም።

ባለፉት ወራት ዩክሬን እና ሩሲያ የሚፈጽሙት ጥቃት ተባብሷል።

ዩክሬን ሚሳዔል መቃወሚያ ስለሌላት የሚተኮስባትን ባለስቲክ ሚሳዔል መቋቋም እንደፈተናት አስታውቃል።

በሩሲያ ላይ የምታደርሰው ጥቃት የነዳጅ ማምረቻዎችን ጨምሮ ዋነኛ የምጣኔ ሃብት መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ነው።