አገራት ከኢራን እንዲርቁ አሜሪካ ያወጣችውን ማስጠንቀቂያ ሩሲያ ውድቅ አደረገች
አገራት ለኢራን የሚሰጡትን ድጋፍ እና የንግድ ግንኙነታቸውን በማቆም እራሳቸውን ከቴህራን እንዲያርቁ አሜሪካ የሰጠችውን ማስጠንቀቂያ ሩሲያ ውድቅ አደረገች።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በቅርቡ፣ “በኢራን ላይ ከዚህ በፊት ያልታዩ ቅጣቶችን እየጣልን ነው። ግጭቱን በፍጥነት ለማቆም የሚረዳውን መንገድ በሚያደናቅፍ ሁኔታ ማንም ለኢራን አገዛዝ እንዳያደርግ” ሲሉ አሳስበው ነበር።
ስድስት ወራት በሞላው ጦርነት አሜሪካ በኢራን ላይ ከምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማሳደር ያላትን ዕቅድ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጋለች።
በዚህም በኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እና ዕገዳዎችን መጣል እንዲሁም ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው አገራት እና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰድን ዓላማ አድርጋለች።
አገራትም ከኢራን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ አሜሪካ በይፋ ጥሪ ብታቀርብም ኃያላኑን ቻይናን እና ሩሲያን ጨምሮ ከአንዳንድ አገራት ጠንካራ የተቃውሞ ምላሽ ገጥሟታል።
አሁን ሩሲያ በይፋ እንዳስታወቀችው በአሜሪካ ጫና ከኢራን ጋር የሚኖራት ግንኙነት ላይ ለውጥ እንደማይኖር ገልጻለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ እንደሉት “አጋሮች እና ወዳጆች አሉን፤ እነዚህን የወዳጅነት እና የሽርክና ግንኙነቶች ጠብቀን እናስቀጥላለን፣ ከዚያም በላይ እናጠናክራቸዋለን” ሲሉ ኢንተርፋክስ ለተባለው የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ፔስኮቭ አክለውም፣ አሜሪካ “ከሌላ አገር ጋር ያሉ ግንኙነቶችን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ወይም ለመጠቅለል የምትችል አይደለችም” ሲሉ የአሜሪካንን ማስጠንቀቂያ አጣጥለውታል።