በዲሞክራቲክ ኮንጎ በሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተነሳ እሳት ከ20 በላይ ሰዎች ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

‎‎በዲሞክራቲክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ውስጥ በአንድ የሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው መጥፋቱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ቅዳሜ ዕለት በነበረው የሰርግ ድግስ ላይ እሳቱ የተነሳው ምሽት ላይ ሲሆን ለሰዓታት ቆይቷል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከታደሙት ሰዎች መካከል ቢያንስ 22 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

የደስታ ሥነ ሥርዓቱን ወደ ሐዘን የቀየረው የእሳት አደጋ መነሻ ምን እንደሆነ እስካሁን አለመታወቁን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።‎

"በርካታ ሰዎች በታደሙበት የሰርግ ድግስ ላይ በደረሰው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል" ሲሉ የአካባቢው ባለሥልጣን ኖርበርት ሙሺንጋ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

አደጋው የደረሰበትን ስፍራ የጎበኙት የዲሞክራቲክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ያኩሚን ሻባኒ ክስተቱን "አሰቃቂ" ሲሉ ገልጸውታል።‎

‎በርካታ ሕዝብ በተጨናነቀ ሁኔታ በሚኖርባት እና የእሳት አደጋ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ እንዲሁም የከተማ መሠረተ ልማቶች ውስን በመሆኑባት ኪንሻሳ ከተማ የተከሰተው ይህ የእሳት አደጋ በተደጋጋሚ ከሚከሰቱት መካከል አንዱ ነው።

በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በርካታ ከባድ የእሳት አደጋዎች በማዕከላዊ አፍሪካ አገሯ ኮንጎ ዋና ከተማ ውስጥ መከሰታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በአሁኑ አደጋ ሕይወታቸው ካለፈው ከ20 በላይ ሰዎች በተጨማሪ የተወሰኑ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በኪናሻሳ ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች ለሕክምና መወሰዳቸው ተዘግቧል።

የሰርግ ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድበት በነበረው እና እሳቱ በተነሳበት ሕንጻ ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ባለሥልጣናት እሳቱ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ በነበረ ችግር ምክንያት ተቀስቅሶ ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄድበትን አዳራሽ ለማስጌጥ በዋሉ ቁሶች አማካይነት ተባብሶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ያላቸው ሲሆን፣ ትክክለኛውን የእሳቱን መነሻ ለማወቅ ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።