ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ብሔራዊ እዳ ከ40 ትሪሊዮን ዶላር አለፈ
የአሜሪካ ብሔራዊ እዳ በአሥር ዓመት ውስጥ በእጥፍ ጨምሮ ከ40 ትሪሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የአገሪቱ ግምጃ ቤት መረጃ አሳየ።
ይህም በዶናልድ ትራምፕ እንዲሁም በጆ ባይደን አስተዳደር ወቅትም አገሪቱ ለዓመታት ከፍተኛ ገንዘብ እንዳወጣች እና የወለድ ክፍያ መጠን እንደጨመረ ያሳያል።
በአውሮፓውያኑ 2016 ብሔራዊ እዳ ከ20 ትሪሊዮን ዶላር በታች ነበር።
ለምክር ቤት የበጀት እና ምጣኔ ሃብት መረጃ የሚያቀርበው የፌደራል ተቋም የሆነው ኮንግረሽናል በጀት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በአውሮፓውያኑ 2026 መጨረሻ የአገሪቱ አጠቃላይ ብድር 39.6 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል።
የአገሪቱ ብሔራዊ እዳ ከተጠበቀው በላይ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ የመንግሥት ብድር እያደገ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን እንደሚያሳይ ተገልጿል።
የአሜሪካ ብሔራዊ እዳ አሁን 41.1 ትሪሊዮን ዶላር እንደደረሰ እና በ2036 ወደ 64 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ ኮንግረሽናል በጀት ቢሮ አስታውቋል።
የፌደራል መንግሥቱ የበጀት ጉድለትን ለመሸፈን በርካታ ገንዘብ ሲያወጣ፤ ሸማቾች በዋጋ ንረት እና በከፍተኛ ወለድ እየተፈተኑ ነው።
ይፋ የተደረገው ብሔራዊ እዳ፣ አጠቃላይ የቦንድ እዳን እንዲሁም በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የሥልጣን ዘመን የነበሩ ብድሮችን የሚያጠቃልል እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ያለፉት 30 ዓመታት የቦንድ ወለድ 5.34% ደርሷል። ይህም በ20 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው።
የወለድ መጠኑ የአሜሪካ መንግሥት፣ ተቋማት እና ሸማቾች ብድር ለመውሰድ የሚከፍሉትን ገንዘብ የሚያሳይ ሲሆን፤ የመኖሪያ ቤት፣ የመኪና እንዲሁም የክሬዲት ካርድ ክፍያ ላይ ጫና ያሳድራል።
ከአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ እና ባለ ሃብቶች በዋጋ ንረት ምክንያት የገጠማቸው ስጋት ከቦንድ ሽያጭ የሚገኝ ትርፍ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
መንግሥት እንዲሁም ሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ የሚሠሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚወስዱት ከፍተኛ የብድር መጠን ከኢንቨስትመንት የሚገኘው ትርፍ አጠራጣሪ እንዲሆን አድርጓል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ለረዥም ጊዜ ቦንዶች "ንብረትን ወደ ጥሬ ገንዘብ በመለወጥ ድጋፍ እንደሚሰጥ" ገልጿል።
ከአውሮፓውያኑ መስከረም 9 እስከ ታኅሣሥ 4 ድረስ ድርሻዎችን መልሶ የመግዛት እርምጃውን ቢያንስ በእጥፍ ጨምሮ ከ2 ቢሊዮን ዶላር ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሳድግ አስታውቋል።
የኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ ዋና ተንታኝ ጆን ካናቫን እንደሚሉት፤ ግምጃ ቤት ግዢውን ለመጨመር ያስተላለፈው ውሳኔ የረዥም ጊዜ ብድር ወጪን "ለማቃለል የሚደረግ ሙከራ" ነው።
የረዥም ጊዜ ብድር ወጪ ላይ የታየው ተጽዕኖ "ከነዳጅ ዋጋ መናር፣ ከዋጋ ንረት ተጋላጭነት እና ከዓለም አቀፍ እንዲሁም ከተቋማት ብድር ጫና" ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን ካለው የእዳ ክምችት አንጻር ግምጃ ቤት ድርሻዎችን መልሶ መግዛቱ "ለረዥም ጊዜ እፎይታ በመስጠት ረገድ ብዙም ትርጉም እንደማይኖረው" አክለዋል።
በጀርመኑ ዲዜድ ባንክ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ረኔ አልበርቻት እንደሚሉት፤ የአሜሪካ መንግሥት በረዥም ጊዜ "5% ወይም ከዚያ ከፍ ያለ ወለድ" የሚያሳድረውን ጫና የሚፈራው የመንግሥትን እንዲሁም የግል ባለ ሃብቶችን የብድር ወጪን ከፍተኛ ስለሚያደርገው ነው።
ከሦስት ወራት በኋላ የአማካይ ዘመን ምርጫ እንደሚደረግ በመጥቀስም ግምጃ ቤት የወለድ መጠንን ለመቆጣጠር "እርምጃዎች መውሰድ" እንደሚኖርበት አክለዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው መሐመድ ኤ ኢል-ኢሪን እንደሚገልጹት፤ የትራምፕ አስተዳደር የሚወስደው እርምጃ የረዥም ጊዜ የብድር ወጪን ከማስተካከል ባሻገር የወለድ መጠንን መቆጣጠርን ያካትታል።
እርምጃው የረዥም ጊዜ የወለድ መጠንን ከመቀነስ ባሻገር በመካከለኛ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የቤት ብድርን ጨምሮ ሌሎችም ዓይነት የብድር ወጪዎችን ለመቀነስ እንደሚረዳም ተናግረዋል።