"በሰሜን ኮሪያ ታግቼ አሜሪካዊ ወታደር እንዳገባ ተገደድኩ"

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በጃፓኗ ደሴት ሳዶ ሞቃታማ ነሐሴ ነበር። የ19 ዓመቷ ሂቶሚ ሶጋ ሕይወቷ እስከወዲያኛው ተለወጠ።

ከእናቷ ጋር አስቤዛ ልትገዛ ወጥታ ወደ ቤት እየተመለሱ ነበር። ድንገት ሦስት ወንዶች ከኋላቸው መጥተው አግተው ወሰዷቸው።

"አፋችን ላይ የሆነ ነገር አደረጉብን። ፊታችንን ቦርሳ በሚመስል ነገር ሸፈኑት" ስትል ሂቶሚ ታስታውሳለች።

ቀጣዩቹ ቀናት በብዥታ አለፉ። ከባሕር ዳርቻ ተነስተው በፈጣን ጀልባ ተጉዘው ትልቅ መርከብ ላይ እንደደረሱ ትገምታለች።

ከእናቷ ጋር ለማውራት ምንም ዕድል አላገኘችም። እናቷ ደግ፣ ብሩህ እና በፍቅር የተሞሉ መሆናቸውን ታስታውሳለች።

"ከእናቴ ጋር የመጨረሻ ቃላት መለዋወጥ አልቻልኩም" ትላለች።

ከቀናት በኋላ ጭንብል ከፊቷ ሲነሳ ጃፓን እንዳልሆነች አወቀች።

ታግታ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተወስዳለች። መንግሥት የሚደግፈው እገታ በአውሮፓውያኑ ከ1970 እስከ 1980 ባሉት ዓመታት ቀጥሏል።

ሂቶሚ በሰሜን ኮሪያ ለ24 ዓመታት ኖራለች።

መንግሥት የደገፈው እገታ

የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣኖች በእገታ አማካኝነት ሰላዮች ጃፓንኛ እንደሚማሩ ማድረጋቸው አንደኛው መላ ምት ነው።

ጃፓንኛ ተምረው የአገሩን ባህል ካወቁ ኋላ ላይ ሰርጎ ለመግባት ያግዛሉ ተብሎ ይታመናል።

ከአውሮፓውያኑ 1977 እስከ 1983 ድረስ የታገቱ 17 ሰዎችን ጃፓን አግኝታለች። ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

"እኔ ዒላማ ተደርጌ ይሁን የአጋጣሚ ጉዳይ አሁንም ድረስ አላውቅም" ትላለች ሂቶሚ።

ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት በወታደራዊ አጥር ውስጥ ለመኖር ተገድዳለች።

እናቷ የት እንዳሉ አላወቀችም። ለምን ታግታ እንደተወሰደች ወታደሮቹንም አልጠየቀችም። ብትጠይቅም እውነቱ እንደማይነገራት ተሰምቷታል።

"ከአጥሩ ውጭ ሰማይ እመለከት ነበር። ጨረቃ እና ከዋክብት ይታዩኛል። ጃፓን ያለውን ቤተሰቤን አስቤ አለቅሳለሁ። መቼ አገኛቸው ይሆን ብዬ እተክዛለሁ።"

ፍርሃቱ እና ብቸኝነቱ ከባድ ቢሆንም አንድ ቀን ነጻ እወጣለሁ ተስፋ መቁረጥ አልፈለገችም።

"ተስፋን ሁሌም በልቤ ውስጥ ይዤ ነበር። ይሄ ሁሉ ያልፋል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ነገር ግን አልሆነም።"

በ1980 ከአጥሩ እንድትወጣ ተፈቀደላት።

የማታውቀውን ቻርልስ ጄንኪንስ የተባለ አሜሪካዊ ወታደር ማግባት እንዳለባት ተነገራት።

ወታደሩ በ1965 ከድቶ ሰሜን ኮሪያ የገባ ነበር።

ከወታደራዊ ቀጣና ውጭ ወደሆነው አካባቢ የገባው በቬትናም ጦርነት እንዲሰለፍ እንደሚገደድ በማመን ነበር።

እናም እጁን ለሰሜን ኮሪያ መስጠት ወደ አሜሪካ ላለመመለስ እንደሚያግዛው አምኗል።

የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ ጠላት ከሆኑት አገራት ጃፓን እና አሜሪካ የመጡ ሰዎችን ጥንዶች አድርጎ ማጣመር የፒዮንግያንግ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ነበር።

"መጀመሪያ የተገናኘንበትን ቀን አስታውሳለሁ። ዝናባማ ቀን ነበር። በጣም ፈርቼ እና ተጨንቄ ነበር" ትላለች።

ጋብቻውን አለመቀበል አማራጭ አልነበረም። ነገር ግን ለባለቤቷ ጥልቅ ስሜት ይሰማት እንደነበር ትናገራለች።

ሁለት ሴት ልጆች ወልደዋል። አባታቸው ከእንጨት መጫወቻ ይሠራላቸው ነበር።

"ተፈጥሯዊ ስሜት ነበረው፤ የሕይወቴ አስደሳቹ ወቅት ልጆቻችን ሲወለዱ ነው። ለልጆቹ ደግ ነበር፤ ይንከባበካቸው ነበር። ከእሱ በጣም የምወደው ይሄንን ባህሪ ነው" ስትል ታስታውሳለች።

ጥንዶቹ መደበኛ ደመወዝ ያለው ሥራ አልነበራቸውም። የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር ስለሚያደርግባቸው ጊዜያቸውን በነጻነት ማሳለፍ አልቻሉም።

ሂቶሚ ጊዜዋን የምታሳልፈወ አትክልት በመትከል ነበር።

"ኮንሰርት፣ ሲኒማ የለም። ምንም መዝናኛ የለም። በየቀኑ ፍርሃት እና ጭንቀት ይውጠናል። ቤተሰቦቼ መኖራቸው መጽናኛ ሆኖኛል።"

በ2002 ስለ ሂቶማ መታገት ዓለም ሲሰማ ሕይወታቸው ተለወጠ።

በጃፓን እና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ውይይት ተካሂዶ ነበር።

በውይይቱ ላይ የቀድሞው መሪ ኪም ጆንግ-ኢል ከጃፓን ከታገቱ 17 ሰዎች መካከል በ13ቱ እገታ እጃቸው እንዳለበት አመኑ።

በሕይወት ያሉት አምስቱ ብቻ መሆናቸው ተገልጾ ነበር። ይህም የሂቶማን እናት አያካትትም።

እናቷ ወደ ሰሜን ኮሪያ አልገቡም።

ሂቶማ ወደ ጃፓን ተመልሳ ለአጭር ጊዜ መጎብኘት እንደምትችል ተነገራት።

"ጃፓን ያለውን ቤተሰቤን ማየት እፈልግ ነበር። እናቴን የማየት ዕድል ሊኖር ይችላል ብዬ አሰብኩ።"

ሰሜን ኮሪያ ባለቤቷን እና ሁለት ልጆቿን ተሰናበተች።

ጃፓን እህቷ እና አባቷ በጉጉት እየጠበቋት ነበር። በሕይወት መኖሯን ሳያውቁ ቆይተዋል።

"ስንገናኝ ተቃቀፍን። ብዙ አለቀስን።"

እዚያው ጃፓን ለመቆየት ወሰነች። ባለቤቷን እና ሁለት ልጆቿን ያገኘችው ከሁለት ዓመት በኋላ ነው።

ባለቤቷ ቻርልስ ጃፓን ቢሄድ በአሜሪካ ወታደሮች እንደሚያዝ በማሰብ ሰሜን ኮሪያ ቆየ።

ከጊዜ በኋላ በተደረገ ድርድር አማካኝነት አገር ጥሎ በመሸሽ እና ጠላትን በማገዝ ክስ ከ20 እስከ 30 ቀናት እንዲታሰር ተፈረደበት።

በ2004 ቤተሰቡ በሳዶ ደሴት እንዲኖር ተፈቀደ።

"ልጆቼ ሳዶ ደሴት ሄደው ባያውቁም የእናታቸው አገር እንደሆነ ስለሚያውቁ ወደዱት" ትላለች ሂቶማ።

ባለቤቷ በ2017 ሞቷል። ሂቶማ ከዚያ በኋላ ከጃፓን የታገቱ ሰዎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ንቅናቄ ውስጥ ገባች።

ታግተው ሰሜን ኮሪያ እየኖሩ ላሉ ሰዎች "ሁሉም ቀን ዋጋ አለው" ትላለች።

በእናቷ ጉዳይም ተስፋ መቁረጥ አትፈልግም። እናቷ የትም ሊሆኑ ይችላሉ። እሷን በማየት ይነሳሳሉ ብላ ታምናለች።

"ልጄ ተስፋ ሳትቆርጥ መታገል ከቀጠለች እኔም እንደዚያ አርጋለሁ ብላ ታስባለች የሚል እምነት አለኝ።"