ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የግብፅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ ላይ ተገኝቷል የተባለው ጉድለት እና ያስነሳው ውዝግብ
የግብፅ መንግሥት፣ በአገሪቱ የሚገነባው 'ኤል ዳባ' የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ማብላያዎች (ሪአክተር) ላይ "ጉድለት" እንደተገኘ በመግለፅ ግንባታውን የሚያከናውነው የሩሲያው ኩባንያ ላይ አቅርቦታል የተባለው ወቀሳ ውዝግብ አስነስቷል።
የግብፅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ባለሥልጣን 'ሮሳቶም' በተባለው የሩሲያ መንግሥት የኒውክሌር ኤነርጂ ግንባታ ኩባንያ ላይ ይህንን ወቀሳ ማቅረቡን የዘገበው የአሜሪካው ዲጂታል ጋዜጣ 'ፖለቲኮ' ነው። በግብፁ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ተጽፏል የተባለ "ምሥጢራዊ ደብዳቤ" እና ሌሎች የውስጥ ሰነዶች በፖለቲኮ ዘገባ ላይ ተጠቅሰዋል።
የግብፅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ባለሥልጣን፣ ያልተጠናቀቁ የኒውክሌር ማብላያዎች ግንባታ ላይ "ጉድለት" እንደተገኘ እንዲሁም "የኒውክሌር ደኅንነት አሠራር" ላይ ጥሰት መፈጸሙን በመጥቀስ ኩባንያውን እንደከሰሰ ዘገባው ያመለክታል።
ከዚህ ዘገባ ይፋ መሆን በኋላ መግለጫ ያወጣው የግብፁ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት፣ ዘገባው ስለ ፕሮጀክቱ "ትክክለኛ እና ሚዛናዊ ያልሆነ ምሥል" እንዳቀረበ በመጥቀስ አስተባብሏል። ግንባታው እየተከናወነ ያለው ዓለም አቀፍ "የኒውክሌር የደኅንነት መስፈርቶችን" በተከተለ መልኩ እንደሆነም ገልጿል።
ክሱ ቀርቦበታል የተባለው 'ሮሳቶም' በበኩሉ ተጽፏል በተባለው ደብዳቤ ላይ የተጠቀሱት ክሶች፣ በፕሮጀክቱ "የኮንትራት፣ ቴክኒካል እና የቁጥጥር አሠራሮች" የተረጋገጡ እንዳልሆኑ በመግለፅ ለፖለቲኮ ምላሽ ሰጥቷል።
ኤል ዳባ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ
በግብፅ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ እየተገነባ ያለው የኤል ዳባ፣ የአገሪቱ የመጀመሪያው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ 4,800 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።
የኤል ዳባ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰዓት የዓለም ግዙፉ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ እንደሆነ የግብፁ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
ግብፅ ይህንን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ እየገነባች ያለችው ከሩሲያ መንግሥት ጋር በፈረመችው ስምምነት አማካኝነት ነው። ማመንጫው የሩሲያ ዲዛይን የሆኑ አራት 'VVER-1200' ማብላያዎች ይኖሩታል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ 28.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ውል የታሰረለት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 25 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ በሩሲያ መንግሥት ብድር ይሸፈናል።
ግንባታውን የሚያከናውነው የሩሲያ መንግሥት ኩባንያ የሆነው 'ሮሳቶም' ነው። በተመሳሳይ መልኩ በሩሲያ ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባውን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሚያከናውነውም ይህ ኩባንያ ነው።
የኢትዮጵያውም የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ VVER-1200 ማብላያዎች እንደሚገጠሙለት፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተረኺን ተናግረዋል።
በመስከረም 2018 ዓ.ም.የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ እና የሮሳቶም ዋና ዳይሬክተር አሌክሲ ሊካቼቭ፣ የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ የድርጊት መርሃ ግብርን ሞስኮ ውስጥ ተፈራርመዋል።
አሥር ዓመት እንደሚወስድ ለሚጠበቀው ግንባታ፣ "የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ማቋቋሚያ ቦታዎች" ልየታ እንደተከናወነ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኤነርጂ ምክትል ኮሚሽነር አብዱረዛቅ ኡመር ሐምሌ ላይ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ግንባታው ላይ የቀረበው ክስ ምንድነው?
እንደ ፖለቲኮ ዘገባ ከሆነ፣ የግብፅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ባለሥልጣን በግንባታው ላይ "ከፍተኛ የሆነ የኮንክሪት ጉድለት" መታየቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ለሮሳቶም ፅፏል።
ከማብላያ ቁጥር 4 "የብረት ልባስ በስተጀርባ ክፍተቶች" መገኘታቸውን እንዲሁም በቀሪዎቹ ማብላያዎች "የመሠረት ንጣፎች ላይ ጉድለቶች" መታየታቸውን ፖለቲኮ ደብዳቤውን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ ያሳያል።
በሦስቱ ማብላያዎች "የመሠረት ንጣፎች" ላይ የታየው ጉድለትን ለመጠገን አንድ ዓመት መውሰዱን የገለፀው ባለሥልጣኑ፣ ሌሎች የግንባታ እንከኖችንም መጥቀሱ ተዘግቧል።
በተጨማሪም ሮሳቶም የፕሮጀክቱ ግንባታ ከግማሽ በላይ እንደተጠናቀቀ ለማረጋገጥ ሲል "አሳሳች ዘዴዎችን" እና "የፈጠራ ሥራዎችን" ተጠቅሟን በማለት ከስሷል።
ፖለቲኮ የተመለከታቸው ሌሎች አራት የሮሳቶም የውስጥ ሰነዶችም የግንባታ "መዘግየት እንዲሁም የኮንስራክሽን ጥራት እና የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮች" መኖራቸውን እንደሚያሳዩ ዘገባው ያትታል።
አንድ የኩባንያው ሰነድ የኤል ዳባ የመጀመሪያው ማብላያ በመስከረም 2021 ዓ.ም. ሥራ እንዲጀመር የተቀመጠው ዕቅድ 18 ወራት ተራዝሞ ወደ መጋቢት 2022 ዓ.ም. ሊዛወር እንደሚችል ማሳየቱን ፖለቲኮ በዘገባው አካትቷል።
ይሁን እንጂ በግንባታ ሂደት ላይ ቴክኒካል ችግር ወይም ጉድለት ማጋጠሙ በራሱ፣ የኒውክሌር ፕሮጀክቱ የራዲዬሽን አደጋን ያመጣል ማለት እንዳልሆነ ቢቢሲ አረቢክ ያነጋራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል። ኃይል ማመንጫው ገና ግንባታ ላይ መሆኑ እና የትኛውም ማብላያ ሥራ አለመጀመሩንም ጠቅሰዋል።
በእንደዚህ ዓይነት ግዙፍ የኑክሌር ፕሮጀክቶች ላይ የግንባታ ጉድለት ወይም መዘግየት ማጋጠሙ ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ የዓለም አቀፍ የኑክሌር ኤጀንሲ የማረጋገጫ እና የደኅንነት ፖሊሲ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ታሪቅ ኡራፍ ተናግረዋል።
በአውሮፓ አገር የሚገኙ የኒውክሌር ፕሮጀክቶችም ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥመዋቸው ማስተካከያ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
የግብፅ ምላሽ
የግብፅ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ባለሥልጣን ሰኞ ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የፖለቲኮ ዘገባ ስለ የምልከታ ግኝቶችን በተገቢው ቴክኒካዊ እና ተቆጣጣሪ አውድ ውስጥ ሳያስቀምጥ ስለ [ፕሮጀክቱ] ደኅንነት እና አተገባበር ድምዳሜ ላይ ደርሷል" ሲል ወቅሷል።
መሥሪያ ቤቱ፤ የኒውክሌር ፕሮጀክቶች የደኅንነት እርምጃዎች የሚወሰዱት "በግላዊ ግምገማ ወይም በዕይታ የሚከናወን ምልከታ" ላይ ተመሥርቶ እንዳልሆነ አስታውቋል።
ይልቁንም "የስጋት ግምገማዎችን፣ የሥራ ፈቃዶችን፣ የመሳሪያዎች ማረጋገጫ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የቁጥጥር ሥራን" በሚያካትት "የተቀናጀ ሥርዓት" አማካኝነት እንደሚከናወን ገልጿል።
መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው፤ "የዚህን ያህል ስፋት እና ውስብስብነት ባለው ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ግላዊ ቴክኒካዊ ምልከታዎች እና ከአሠራር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች መኖራቸው፤ በቀጣይም ተገቢ የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸው መደበኛ የትግበራ ሂደቱ አካል ነው" ብሏል።
የኤል ዳባ ፕሮጀክት የኢንጂነሪንግ እና ገጠማ ሥራ ተከታታይ ምርመራ እንደሚደረግበት የገለጸው መሥሪያ ቤቱ፤ የተገኘ የትኛውም ጉድለት የግንባታ ምዕራፉ መጠናቀቅ ከመጽደቁ በፊት እንዲጠገን እና እንዲሞከር እንደሚደረግ ገልጿል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ ግንባታው ላይ ጉብኝት እና ግምገማ እንደሚያሂድ በመጥቀስ፤ ፕሮጀክቱ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ እንዳለ አስረድቷል።
ግብፅ በመስከረም 2016 ዓ.ም. የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲን የኒውክሌር ደኅንነት ስምምነትን ያጸደቀች ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ከታኅሣሥ ወር ጀምሮም የስምምነቱ አባል ነች።