የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር በእንግሊዝ ለተፈጸመው ባርነት ይቅርታ ለመጠየቅ እንጂ ካሳ ለመክፈል ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም፣ አገራቸው የአትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥ በተካሄደው የትራንስአትላንቲክ የባርያ ንግድ ውስጥ ለነበራት ሚና በይፋ ይቅርታ የምትጠይቅበት እድል ላይ "ክፍት አቋም" እንዳላቸው ተናገሩ።

ይሁን እንጂ የገንዘብ ካሳ የመክፈል ዕቅድ እንደሌላቸው ይፋ አድርገዋል።

በርንሃም "በባርነት ንግድ ከተጎዱ ሰዎች ጋር ውይይት ማድረግ እፈልጋለሁ" ያሉ ሲሆን፣ "ይቅርታ እንዲጠየቅ የሚቀርቡ ጥሪዎችን ለመቀበልም ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

ነገር ግን የገንዘብ ካሳ የመክፈል ሀሳብን "ትክክለኛው መፍትሔ አይደለም" በማለት እንደማይቀበሉት ከወዲሁ አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፣ እርሳቸውም የሚሳተፉበት እና በካሪቢያን የሚካሄደው የኮመንዌልዝ መሪዎች ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት ከመጀመሩ በፊት በሰጡት አስተያየት ነው።

የካሪቢያን አገራት፣ ንጉሥ ቻርለስ ሦስተኛ ቀጣናውን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት፣ ዩኬ በባርነት ንግድ ውስጥ ለነበራት ሚና ይቅርታ እንድትጠይቅ እና ካሳም እንድትከፍል በድጋሚ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በርንሃም፣ አፍሪካውያን በባርነት ተይዘው ወደ አሜሪካ አገራት በተጓጓዙበት የትራንስአትላንቲክ የባርነት ንግድ ዘመን የተፈጸመውን ድርጊት "ጭካኔያዊ እና አረመኔያዊ ጥሰት" ሲሉ ገልጠው፣ ብሪታንያ "ካለፈው ታሪኳ ጋር በቀጥታ መጋፈጥ አለባት" ብለዋል።

የብሪታንያ መንግሥት ለዚህ ድርጊት እስካሁን በይፋ ይቅርታ አልጠየቀም፤ የካሳ ክፍያም አላቀረበም። በርንሃምም የካሳ ክፍያዎችን በተመለከ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ፖሊሲ የማስቀጠል አቋም ይዘዋል።

"ዛሬ ያሉ ብሪታንያውያን፣ ምንም እንኳን አሰቃቂ ቢሆኑም፣ በተለየ ዘመንና በተለየ ሕግ ስር ለተፈጸሙ በግል ያልተሳተፉባቸው ታሪካዊ በደሎች ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል ብዬ አላስብም" በማለት በርንሃም በጋርዲያን ላይ ባወጡት ጽሑፍ አመልክተዋል።

በተጨማሪም፣ የኮመንዌልዝ አገራት ለብዙ ዓመታት "እውነተኛ ውይይት" እንዲካሄድ ሲጠይቁ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ "በተደራጀ መንገድ ውይይት" ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

"በብሪታንያ መንግሥት ስም በይፋ ይቅርታ እንዲጠየቅ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ማዳመጥ የዚህ ሂደት አስፈላጊ አካል ይሆናል። ለእነዚህ ጥሪዎች ክፍት ነኝ" ብለዋል።

አንድ የመንግሥት ምንጭ፣ ይህ እርምጃ "ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክለኛ ነው" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ፣ ቻይናና ሩሲያ በዓለም ዙሪያ ተፅዕኖአቸውን ለማስፋፋት በሚጥሩበት በዚህ ወቅት፣ የኮመንዌልዝን ጥንካሬ ማሳደግ የዩኬን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ያምናል።

በዚህ ሳምንት፣ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሞስኮ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤን አስተናግደዋል።

ለባርነት ንግዱ ካሳ እንዲከፈል ከዚህ ቀደም ጥሪ ሲያቀርቡ የነበሩት የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ፣ የበርንሃምን መግለጫ በደስታ ተቀብለው "የካሳ ፍትሕ" መጠየቃቸውን እየቀጠሉ በውይይቱ ላይ በቅን ልቦና እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።

የቅኝ ገዥ አገራት በባርነት ንግድ የነበራቸው ሚና እንዲቀበሉ እና ካሳ እንዲከፍሉ የሚጠይቀው "ዘ ሪፔይር ካምፔይን" የተባለ ንቅናቄ መሥራች ዴኒስ ኦብራየን በበኩላቸው፣ የበርንሃም መግለጫ አሳዛኝ እና የሚገባውን ርቀት ያልሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።

"የብሪታንያ መንግሥት ማደናገሩን አቁሞ አሁኑኑ የተሟላ ይፋዊ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይህ ወደ ካሳ ፍትሕ ለመድረስ ጠቃሚና ተምሳሌታዊ የመጀመሪያ እርምጃ ይሆናል" ብለዋል።

የእንግሊዝ ባለሥልጣናትና የንጉሣዊው ቤተሰብ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለዘመናት በቀጠለው የባርነት ንግድ ውስጥ ጉልህ ተሳታፊዎች ነበሩ።

ብሪታንያ እአአ በ1833 ባርነትን ለማስወገድ የወጣውን ሕግ በፓርላማዋ በማጽደቅ በባርያ ንግድ መቋረጥ ውስጥ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።

በዚያ ሕግ መሠረት ብሪታንያውያን የእርሻ መሬት ባለቤቶች ባርያዎቻቸውን በማጣታቸው ምክንያት ካሳ ተከፍሏቸው ነበር። ብሪታንያ እነዚህ ካሳዎች ለመክፈል የገባችውን ዕዳ ሙሉ ከፍላ ያጠናቀቀችው እአአ በ2015 ነው።