ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰው ሠራሽ አስተውሎት "ትጥቅ መፍታት አለበት" ሲሉ አስጠነቀቁ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፤ ወደ ጵጵስናው ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባቀረቡት ትልቅ የማስተማሪያ ሰነድ ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) "ትጥቁን ሊፈታ" እንደሚገባ አስጠነቀቁ።

"ቃሉ ጠንካራ ነው። አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሆነ ብዬ ነው የመረጥኩት፤ ምክንያቱም ይህ ጊዜ ትኩረትን መሳብ የሚችሉ ቃላት ያስፈልጉታል" ብለዋል።

'ኢንሳይክሊካልስ' የሚባሉት እነዚህ የማስተማሪያ ሰነዶች ለካቶሊክ ጳጳሳት የሚጻፉ ደብዳቤዎች ናቸው። ከቅርብ አስርት ዓመታት ወዲህ ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለዓለም የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶችን የሚይዙ ሆነዋል።

የአሁኑ ደብዳቤ በአብዛኛው ያተኮረው ኤአይ ላይ ቢሆንም፤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ ውስጥ በባሪያ ንግድ ላይ ስለነበራት ሚና ይቅርታ ጠይቀዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይቅርታ ከዚህ ቀደም ከቫቲካን ከቀረቡት በሙሉ ጠንካራ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ነው።

"በርካታ ሰዎች ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ስቃይ እና ውርደት በምናስብበት ወቅት ጥልቅ ሀዘን ላይሰማን አይችልም" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ፤ በቤተ ክርስቲያኗ ስም "ከልብ የመነጨ ይቅርታ" ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በጽሑፋቸው የባርያ ንግድ እና ከኤአይ ጋር የሚደረግ ግንኙነትን አመሳስለው አቅርበዋል። ዓለም በምርት ሂደት እና አተገባበር ላይ የሚፈጸም ሰዎችን የመበዝበዝ ድርጊትን በድጋሚ እንደተለመደ ነገር እየቆጠረው መሆኑን ጠቁመዋል።

በታሪካዊው የባርነት አሳዛኝ ክስተት እና እየመጣ ባለው "አዲስ የዲጂታል ባርነት" ስጋት መካከል ተመሳስሎሽ እንዳለ አስጠንቅቀዋል።

ብዝበዛን የተለመደ ተግባር የማድረግ ተመሳሳይ ልማድ መደቀኑን እንዲሁም የሰው ልጅ ተመሳሳይ የሞራል መስቀለኛ መንገድ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከኤአይ ጋር በተያያዘ በርካታ ድብቅ አደጋዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገልጸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መልዕክት፤ ሥልጣን ላይ ያሉ አካላት "አደጋዎቹን" የማስወገድ ቀጥተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በግልጽ አስፍሯል።

ለምሳሌ፤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጦርነት ውስጥ ኤአይን መጠቀምን አውግዘዋል። የሰው ልጅ በጦር መሣሪያዎች ላይ ያለውን ቁጥጥር መቀነስ፤ የጦርነቱን "ፍትሐዊነት" ይበልጥ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው ገልጸዋል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የጦር መሣሪያ እሽቅድድም ሊነሳ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል። "አንድም አልጎሪዝም ጦርነትን የሞራል ተቀባይነት ያለው ሊያደርገው አይችልም" ሲሉ ጽፈዋል።

የኤአይ ጥቅም ላይ መዋል ጦርነትን "በተፈጥሮው ኢሰብአዊ" የሆነ ድርጊት መሆኑን እንደማያስቀር ተናግረዋል።

ይልቁንም "ወደ ጥቃት ለመግባት የሚቀመጠውን ደረጃ ዝቅ በማድረግ፣ የመከላከል እርምጃን ወደ ስጋት ትንበያ በመቀየር እንዲሁም ተጎጂዎችን ወደ ዳታነት በማውረድ" ጦርነቶች በፍጥነት እንዲቀሰቀሱ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባልተለመደ ሁኔታ "ታላቅ ሰብአዊነት" (Magnifica Humanitas) ሲሉ የሰየሙትን መልዕክታቸውን ያቀረቡት ራሳቸው ናቸው።

በቫቲካን መልዕክታቸውን ሲያቀርቡ ግዙፉ የአሜሪካ የኤአይ ኩባንያ 'አንትሮፒክ' አንዱ መስራች የሆነው ክርስቶፈር ኦላህን ጨምሮ ሌሎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ባለሙያዎች አብረዋቸው ነበሩ።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልዕክት በኋላ ንግግር ያደረገው ክርስቶፈር ኦላህ፤ ኤአይ ነክ ጉዳዮች እንደ እሱ ባሉ የኮምፒውተር ሳይንቲስቶች ብቻ መያዛቸው የተሻለ ነው ብሎ ማመን ስህተት እንደሆነ ጠቅሷል።

"በኤአይ ምክንያት የተነሱት ጥያቄዎች በሚያስከትሉት ነገር ብቻ ሳይሆን በተፈጥሯቸውም ጭምር ከኤአይ ምርምር ማኅበረሱ የገዘፉ ናቸው" ብሏል።