ቀጥታ, ሩቢዮ ዛሬ ከኢራን ጋር ስምምነት ሊደረስ ይችላል ሲሉ ቴህራን የመሳካት ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ገለጸች

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሁለቱ አገራት መካከል ዛሬ ስምምነት ሊደርስ ይችላል ሲሉ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከዋሺንግተን ጋር በቀረበው መግባቢያ ሰነድ በርካታ ጉዳዮች ከድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ገለጹ። ቃል አቀባዩ አክለውም ይህ ግን ቴህራን ስምምነት ለመፈረም ተቃርባለች ማለት አለመሆኑን አስታውቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ አረብ እና ሙስሊም አገራት ከእስራኤል ጋር ስምምነት እንዲፈርሙ ግፊት እያደረጉ ነው

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    አሜሪካ ከኢራን ጋር ከስምምነት ለመድረስ መቃረቧን እየገለጹ ያሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚያ በፊት ግን ዋነኞቹ ሙስሊም አገራት ከእስራኤል ጋር የአብረሃም ስምምነትን እንዲፈርሙ ጥሪ አቀረቡ።

    ድርድሩ “በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር የሚካሄደውን ጦርነት የሚያስቆመው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ብዙሃኑ ሕዝባቸው ሙስሊም የሆኑ ስድስት አገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያሻሽለውን ስምምነት መፈረም እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ስምምነት ከስድስት ዓመት በፊት ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ባህሬን በማስከተልም ሞሮኮ እና ሱዳን ከእስራኤል ጋር ከተፈራረሙት የአብረሃም ስምምት ጋር አስተሳስረው እያቀረቡት ነው።

    ከበርካታ ሙስሊም እና አረብ አገራት መሪዎች ጋር መነጋገራቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የጠቀሱት ትራምፕ ውስብስቡን ሥራ አሜሪካ መሥራቷን በመግለጽ “በተከታይነት እነዚህ አገራት በሙሉ ቢያንስ የአብረሃም ስምምነትን መፈረም ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

    ከእነዚህም መካከል ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ፓኪስታን፣ ቱርክ፣ ግብፅ እና ዮርዳኖስን በመጥቀስ ስምምነቱን እንዲፈርሙ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

    ነገር ግን ግብፅ እና ዮርዳኖስ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው ሆነው ሳለ ለምን እንደጠቀሷቸው ግልጽ አይደለም። እስራኤል ከቱርክ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ የሻከረ ግንኙነት ያላት ሲሆን፣ የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ የበለጠ ተቃቅረዋል።

    የተጠቀሱት አገራት የአብረሃም ስምምነትን የሚፈርሙ ከሆነ እስራኤል ከአብዛኞቹ አረብ እና ሙስሊም አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሻሽል ነው።

  2. አንድ መኪና ከዝሆን ጋር ተጋጭቶ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ አራት ቆሰሉ

    አደጋው የደረሰበት መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Uganda Police Force

    በኡጋንዳ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ አንድ መኪና ከዝሆን ጋር ተጋጭቶ ቢያንስ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

    ፖሊስ እንዳለው እሁድ ማታ በኡጋንዳ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል ውስጥ በተከሰተው አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ ሌሎች አራት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    ተሽከርካሪው ሰባት የአገሪቱ ገቢዎች ባለሥልጣናትን አሳፍሮ እየተጓዘ ሳለ ነበር ከዝሆኑ ጋር የተጋጨው። በአደጋው የተጎዱት ሰዎች በአካባቢው ወደሚገኝ ከዚያም ወደ ዋና ከተማዋ ካምፓላ ተወስደዋል።

    ስለአደጋው መግለጫ ያወጡት ባለሥልጣናት በሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ከመድረሱ ውጪ በዝሆኑ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ያሉት ነገር የለም።

    በኡጋንዳ ውስጥ ከዱር እንስሳት ጋር በተያያዘ የሚከሰት የመኪና አደጋ በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም ይነገራል። የአገሪቱ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን አሽከርካሪዎች በመንገዳቸው ላይ ለእንስሳት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

    "አሽከርካሪዎች ለእንስሳት በተከለሉ ጥብቅ አካባቢዎች በኩል በሚያልፉበት ጊዜ እንስሳቱ በብዛት መንገዶችን ስለሚያቋርጡ በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ” ጠይቋል።

  3. ትራምፕ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ተናገሩ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ሊደረስ የሚችልበት እንዳለ አስረግጠው ተናገሩ።

    ከቴህራን ጋር እየተካሄደ ያለውን ድርድር አጥብቀው የተከላከሉት ፕሬዝዳንቱ የተቿቸውን ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች “ከኢራን ጋር የሚካሄደው ድርድር ስላለው አቅም የማያውቁ ደደቦች” ሲሉም አንቋሸዋል።

    በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ፖለቲከኞቹን “ትልልቅ ድሎቼን የሚኮንኑ ከፋፋይ ግለሰቦች” ብለዋል።

    “ከኢራን ጋር የሚደረሰው ስምምነት ታላቅ እና ትርጉም ይሆናል፤ አልያም ምንም ስምምነት አይኖርም” ሲሉም ትራምፕ ተናግረዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር በኢራን ያለው ፖለቲካዊ ዓላማ ላይ ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካን የሕዝብ እንደራሴ አባላትም ሳይቀር ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል።

    ከቴህራን ጋር የሚደረገውን ንግግር ከተቹ መካከል የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ እና የቀድሞ የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካካሪ ጆን ቦልተን ይጠቀሳሉ።

  4. ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት ኳታር መግባታቸው ተዘገበ

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን የሰላም ድርድር በዋነኛነት የሚመሩት የኢራን ባለሥልጣናት ኳታር ዋና ከተማ ዶሃ መግባታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ወደ ኳታር ያደረጉት ጉዞ የተጠበቀ እንዳልሆነ ተገልጿል።

    የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሼኽ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታሒኒ ጋር ውይይት ለማድረግ ዶሃ መሄዳቸው ተዘግቧል።

    ውይይታቸው በዋነኛነት የሆርሙዝ ወሽመጥ እና የዩራንየም ጉዳይን የሚመለከት እንደሚሆን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

    የኢራን ብሔራዊ ባንክ ገዢ አብዶልናስር ሔማቲ “ማዕቀብ የተጣለባቸው የባንክ ሒሳቦችን በተመለከተ ለሚደረግ ድርድር” ወደ ኳታር ማቅናታቸውን የቴህራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ባለፈው ሳምንት ደግሞ የኳታር ልዑካን ወደ ኢራን አቅንተው እንደነበር ይታወሳል።

    ኢራን እንደ ቅድመ ሁኔታ ካቀረበቻቸው ነጥቦች መካከል አሜሪካ ከፋይናንስ ይዞታዎቿ ላይ ማዕቀብ እንድታነሳ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

  5. ኢራን ከአሜሪካ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ መግባባቷን ነገር ግን ስምምነት ገና መሆኑን ገለጸች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሰኞ ዕለት ከአሜሪካ ጋር በቀረበው መግባቢያ ሰነድ በርካታ ጉዳዮች ከድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ገለጸች።

    ቃል አቀባዩ አክለውም ይህ ግን ቴህራን ስምምነት ለመፈረም ተቃርባለች ማለት አለመሆኑን አስታውቀዋል።

    ኢስማኤል ባጌይ ኢራን እየተነጋገረች ያለችው ጦርነቱን ለማቆም እንጂ በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ አለመሆኑን ገልጸዋል።

    ቃል አቀባዩ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአቋም መለዋወጥ ለስምምነቱ እንቅፋት መሆኑን በማንሳት ከስሰዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ እሁድ ዕለት አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው ዕገዳ “ከስምምነት ላይ እስክንደርስ፣ ስምምነቱ እስኪጸድቅ እና እስኪፈረም ድረስ በሙሉ ኃይል ተግባራዊነቱ ይቀጥላል” ብለዋል።

    አክለውም “ሁለቱም አካላት ጊዜ መውሰድ እና የሚገባ ነገር ላይ መድረስ አለባቸው” ሲሉ ጽፈዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አክለውም ተወካዮቻቸው ከኢራን ጋር ስምምነት ለማድረግ እንዳይጣደፉ አሳስበዋል።

  6. ሩቢዮ የኢራን ጦርነትን ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት “ምናልባት ዛሬ ሊደረስ” ይችላል አሉ

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሁለቱ አገራት መካከል ዛሬ ስምምነት ሊደርስ ይችላል አሉ።

    በሕንድ ዋና ከተማ ኒው ዴልሂ የሚገኙት ሩቢዮ በአሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪዎች “ጠረጴዛ ላይ ጠንካራ የስምምነት ነጥቦች” መኖራቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ሩቢዮ አክለውም “ገና በሂደት ላይ ያለ ነገር ነው፤ ትናንት ማታ የሆነ ዜና ይኖረናል ብለን አስበን ነበር፥ ምናልባት ዛሬ ይኖረናል” ብለዋል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሰኞ ዕለት አገራቸው ከኢራን ጋር ጥሩ ስምምነት ታደርጋለች ወይም “በሌላ መንገድ” ትፈታዋለች ብለዋል።

    ሩቢዮ ሌሎች “አማራጮችን” ከመፈለግ በፊት ለዲፕሎማሲ ያለውን ዕድል ሁሉ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ተወካዮቻቸው ከኢራን ጋር ስምምነት ለማድረግ እንዳይጣደፉ አሳስበዋል።

    ሩቢዮ “ሆርሙዝን ለመክፈት የሚያስችል ተጨባጭ የሆነ ስምምነት ጠረጴዛው ላይ አለ። ወሽመጡን ክፈቱ፤ ተጨባጭ፣ እውነተኛ በጊዜ የተገደበ ድርድር ወደ ማድረግ ግቡ፤ እናም ተስፋ አለኝ እናሳካዋለን” ብለዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም “በፍጥነት ከድምዳሜ ላይ መድረስ አልፈልግም” በማለት “ከኢራን ምላሽ ለማግኘት ትንሽ ጊዜ ይወስዳል” ሲሉም ተደምጠዋል።

    እሁድ ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው ዕገዳ “ከስምምነት ላይ እስክንደርስ፣ ስምምነቱ እስኪጸድቅ እና እስኪፈረም ድረስ በሙሉ ኃይል ተግባራዊነቱ ይቀጥላል” ብለዋል።

    አክለውም “ሁለቱም አካላት ጊዜ መውሰድ እና የሚገባ ነገር ላይ መድረስ አለባቸው” ሲሉ ጽፈዋል።

    የኢራን መንግሥት በትራምፕ ሆነ በሩቢዮ አስተያየቶች ላይ አስተያየቱን አልሰጠም።

    ታስኒም የዜና ወኪል ግን አሜሪካ የስምምነቱ ወሳኝ ነጥቦችን እያስተጓጎለች ነው በማለት እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ፈንዶች እንዲለቀቁ ጠይቋል።

    የኢራን ፓርላማ ቃል አቀባይ ኢብራሂም ሬዛይ በበኩላቸው በጦርነቱ ወቅት “ዓይን ላጠፋ ዓይን” የሚል መርህ ሲከተሉ እንደነበር ገልጸው፤ በዲፕሎማሲ አለመግባባት ወቅት ደግሞ “ለተግባር ተግባራዊ ምላሽ መስጠት” የሚል መሆኑን ተናግረዋል።

    በኤክስ ገጻቸው ላይ ኢራን በጫናዎች ወይንም ማስፈራሪያዎች አትንበረከክም ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አሜሪካ ስምምነት ላይ መድረስ የምትፈልግ ከሆነ መደራደር አለባት ነገር ግን ነዳጅ በ6 ዶላር ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ማስመሰሏን ትቀጥል ሲሉ ጽፈዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ይፈረማል የሚል ተስፋ እየጨመረ በመምጣቱ ሰኞ ዕለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በ6 በመቶ ገደማ ቀንሷል።

  7. የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴርን ጭኖ የነበረ ጄት በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ ሲግናሉ ተጠለፈ

    የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ጆን ሃሌይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የዩናይትድ ኪንግደም ሮያል አየር ኃይል ጄት ባለፈው ሳምንት የአገሪቱን መከላከያ ሚኒስትርን ጭኖ በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ በሚበርበት ሰዓት ሲግናሉ ተጠልፎ (Jamming) እንደነበር ተገልጸ።

    ክስተቱ ያጋጠመው መከላከያ ሚኒስትሩ ጆን ሃሌይ ኢስቶኒያ ውስጥ የሚገኙ የብሪታኒያ ወታደሮችን ጎብኝተው ሲመለሱ እንደነበር የዩኬው ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

    ጥቃቱ የአውሮፕላኑ አቅጣጫ ጠቋሚ ‘ጂፒኤስ’ እንዲያጠፋ የሚያደርግ በመሆኑ አብራሪዎቹ ሌላ የጉዞ ስርዓት ለመጠቀም ተገድደዋል። ሦስት ሰዓት በሚፈጀው በረራ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ ሩሲያ እጇ እንዳለ ተገምቷል።

    ይህ ጠለፋ ያጋጠመው፤ ሁለት የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች ባለፈው ወር በጥቁር ባሕር በኩል ሲበር የነበረ የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ አውሮፕላንን “በተደጋጋሚ እና በአደገኛ ሁኔታ” መጥለፋቸው ይፋ በተደረገ ማግሥት ነው።

    የአሁኑ ጥቃት የተፈጸመው የመከላከያ ሚኒስትሩን ዒላማ በማድረግ መሆኑ አልተረጋገጠም። ነገር ግን የአውሮፕላኑ ጉዞ በበረራ መከታተያ ድረ ገጾች ላይ ወጥቶ እንደነበር ጋዜጣው ዘግቧል።

    ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ የመከላከያ ሚኒስቴርን አስተያየት ጠይቋል።

    መከላከያ ሚኒስትሩ በኢስቶኒያ ቆይታቸው በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ በሚካሄድ የኔቶ ወታደራዊ ልምምድ ላይ የሚሳተፉ የዩኬ ሠራዊት አባላትን አነጋግረዋል።

    ባለፈው ወር ደግሞ የሩሲያ ሱ-35 ተዋጊ ጄት ‘ሩቬት ጆይንት’ የተባለውን የስለላ አውሮፕላንን እጅግ ተጠግቶ አውቶፓይለቱን እንዲጠፋ በማድረግ የአውሮፕላኑ አደጋ ጊዜ ስርዓቱ እንዲበራ አድርጎ ነበር።

    ሌላ ሱ-27 ጄት ደግሞ ስድስት ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም አውሮፕላን ፊት እንዳለፈ እና ስድስት ሜትር ርቀት ድረስ ወደ አውሮፕላኑ አፍንጫ እንደተጠጋ ተገልጿል።

  8. በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ይደረሳል በሚል ተስፋ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ

    ነዳጅ ወደ መኪና ሲቀዳ

    የፎቶው ባለመብት, Hindustan Times via Getty Images

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ይፈረማል የሚል ተስፋ በስፋት በመታየቱ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ። የእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ላይም ጭማሪ ታይቷል።

    ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሰላም ስምምነቱ ነጥቦች "በአብዛኛው ድርድር ተደርጎባቸዋል" በማለት ዝርዝሩን ይፋ ሳያደርጉ ቀርተዋል።

    ሁለቱ አገራት በበርካታ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው ሲገለጽ ቢቆይም ትራምፕ ተደራዳሪዎች ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፈራረም እንዳይጣደፉ አሳስበዋል።

    ሰኞ ጠዋት በእስያ ገበያ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ 5.5 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን በአሜሪካ ደግሞ የ5.8 በመቶ ቀንሶ 90.99 ዶላር ተሸጧል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ማስከፈትን የሚያካትት ነው ያሉ ሲሆን ይህም ለወራት መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በነጻነት እንዲጓዙ ያስችላል ተብሎ ነበር።

    ጠባቡ የባሕር መተላለፊያ የዓለም አንድ አምስተኛ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚተላለፍበት ሲሆን ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኋላ ተዘግቷል።

    ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ኳታር ጋር “በሰላም ስምምነቱ የመግባቢያ ሰነድ” ዙሪያ “ጥሩ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

  9. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ከኢራን ጋር ስምምነት ለመፈጸም "እንዳይጣደፉ" አሳሰቡ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት የሚያደርጉት ድርድር ወደ ማጠናቀቂያው እንደተቃረበ መነገሩን ተከትሎ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደራዳሪዎቻቸው ከኢራን ጋር “ተጣድፈው ወደ ስምምነት እንዳይገቡ” አዘዙ።

    በሁለቱ አገራት ንግግር እየተደረገበት ያለው የስምምነት ዕቅድ ከያዛቸው ነጥቦች መከካከል የተኩስ አቁሙን ለ60 ቀናት ማራዘም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መክፈት እንዲሁም የኢራንን የኒውክሌር ፕሮግራም በተመለከተ ተጨማሪ ድርድር ማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።

    ትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ንግግሩ “ገንቢ” በሆነ ሁኔታ እየተካሄዱ መሆኑን ቢገልጹም፤ አክለው ግን “ሁለቱም ወገኖች ጊዜያቸውን መውሰድ እና በትክክል ማከናወን አለባቸው” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ዕለት ስምምነቱ “በአብዛኛው ድርድር እንደተደረገበት” መገናራቸው ስምምነት ይፋ መደረጉ አይቀሬ ነው የሚል ግምት ፈጥሮ ነበር።

    የኢራን ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ ሀሳብ አመልክተው ነበር። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ለመድረስ “እጅግ ቅርብ እና እጅግ ሩቅ” ናቸው ብለው ነበር።

    የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡ ከሆነ ድርድር የሚካሄድበት እቅድ የመጨረሻው ስምምነት አይደለም። ይልቁንም ሁለቱ አገራት የተወሰኑ አጨቃጫቂ ጉዳዮች በኋላ ድርድር እንዲካሄድባቸው እንደሚፈቅድ ዘግበዋል።

    ኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚነሳበት መጠን እና ጊዜ፣ የታገደውን የኢራን ገንዘብን የማስለቀቅ ጉዳይ እንዲሁም አሜሪካ የቴህራንን የኒውክሌር ፍላጎት ለመገደብ ያላት ፍላጎት ለበኋላ ድርድር ከሚተዉ ነጥቦች መካከል ናቸው።

    ይህ የስምምነት ዕቅድ ሪፐብሊካኖችን ለሁለት የከፈለ ሲሆን የተወሰኑት ኢራን ላይ ለዘብተኛ አቋም የያዘ እንደሆነ በይፋ እየተናገሩ ነው።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባጋሩት ልጥፍ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ልትሰራ እንደማትችል “መረዳት እንዳለባት” በአጽንኦት አንስተዋል። ቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ ዓላማ እንደሚውል በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

    አንዳንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ጋር በሚደረሰው ስምምነት አማካኝነት ኢራን የበለጸገ ዩራኒየሟን አሳልፋ እንደምትሰጥ ዘግበዋል።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ለአገሪቱ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ቴህራን “ፍላጎቷ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳልሆነ ለዓለም ለማረጋገጥ” ዝግጁ እንደሆነች ተናግረዋል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በድርድሩ “ጉልህ” መሻሻል ቢታይም፤ ሂደቱ “የመጨረሻ ደረጃ እንዳልደረሰ” ገልጸው ነበር።