የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ታዳጊ ሴቶችን የደፈሩት ልጆች ባለመታሰራቸው "ክፉኛ መደንገጣቸውን" ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ሁለት ታዳጊ ሴቶችን የደፈሩ ሦስት ወንዶች የእስር ፍርድ ስላልተወሰነባቸው "ክፉኛ መደንገጣቸውን" ተናገሩ።
በሳውዝሃምፕተን ክራውን ችሎት የተሰጠው ፍርድ ዳግም በጠቅላይ አቃቤ ሕጉ መታየቱ "ትክክል" ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የ15 እና የ14 ዓመት ታዳጊዎቹ የተደፈሩት እአአ በ2024 ኅዳር ወር እና በጥር ወር 2025 በፎርብሪጅ ሐምፕሻየር በ14 ዓመት ወንዶች ነው።
ሌላ የ13 ዓመት ታዳጊ በወንጀሉ ላይ በነበረው ተሳትፎ የተነሳ ጥፋተኛ ተብሏል።
ስታርመር ልጃገረዶቹ "ለዚህ አስከፊ ወንጀል ይህ ነው የማይባል ጥንካሬ እና ብርታት አሳይተዋል" ሲሉ አድንቀዋል።
ሐሙስ ዕለት ጥፋተኞቹ ላይ ውሳኔ የሰጡት ዳኛ ኒኮላስ ሮውላንድ "እነዚህን ልጆች ወንጀለኛ ከማለት እቆጠባለሁ" ብለው ነበር።
ከዚያ ይልቅ ደፋሪዎቹ ወጣት ጥፋተኞች የሚያገግሙበት ትዕዛዝ በመስጠት የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲያከናውኑ ተፈርዶባቸዋል።
ይህም ያለ ክፍያ መስራት፣ የሰዓት ገደብ ወይም ሕክምና እንዲከታተሉ ማድርግ ሊሆን ይችላል።
ነገር ግን ወንጀሉ ከተፈጸመባቸው መካከል አንዷ ውሳኔው "ፊቴ ላይ በድንጋይ የመመታት ያህል ነው የተሰማኝ" ስትል የተሰማትን ለቢቢሲ ተናግራለች።
አሁን 16 ዓመቷ የሆነው ይህች ታዳጊ ውሳኔው "የሰሩት ትክክል እንዳልሆነ፤ ነገር ግን ልጆች ስለሆኑ ከሕግ አንጻር ልክ እንደሆነ ነው የሚመስለው" ስትል ተናግራለች።
እርሷ እና ቤተሰቧ ውሳኔው እንዲቀለበስ እንደሚፈልጉ ተናግራ ልጆቹ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ እንደሚፈልጉ አስረድታለች። የተሰጠውን ፍርድም "ቀላል" ስትል ገልጻዋለች።
"ውጤቱ ይህ ከሆነ ታዲያ ለምንድን ነው ፍርድ ቤት በመመላለስ ያንን ሁሉ ውጣ ውረድ ያየሁት፤ ወደ ችሎት በመመላለስ ዳግም ያንን ስቃይ የኖርኩት ለምንድን ነው" ስትል ያላትን ቅሬታ ገልጻለች።
ታዳጊዋ ስትደፈር 15 ዓመቷ የነበረ ሲሆን በኤቮን ወንዝ በኩል እያለፈች እንደነበር አስረድታለች።
በኅዳር ወር 2024 ከአንዱ ልጅ ጋር በስናፕቻት ተዋውቀው ማውራት ከጀመሩ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ልታገኘው እየሄደች ነበር።
ሁለተኛዋ ተበዳይ የተደፈረችው በዚያው ስፍራ ነው።
የ14 ዓመቶቹ ወንዶች ታዳጊዎቹን ሴቶች ሲደፍሩ በስልካቸው የቀረጹ ሲሆን በኋላ ላይም በኦንላይን አጋርተውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር የቢቢሲ ቃለ ምልልስን ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ይህ በጣም አሰቃቂ እና ጀግንንት የተሞላበት ምስክርነት ነው። በዚህ ክስ ተበዳይ የሆኑት ልጃገረዶች ለዚህ አስከፊ ተግባር ይህ ነው የማይባል ጀግንነት እና ጥንካሬ አሳይተዋል።
"ይህ እጅግ የሚያስደነግጥ ውሳኔ ነው፤ እናም አቃቤ ሕግ በፍጥነት ውሳኔውን ዳግም እንዲመለከተው መደረጉ ተገቢ ነው" ብለዋል።
ውሳኔው በተሰጠበት ወቅት ዳኛው የወንጀሉን "አስከፊነት" አጽንኦት ሰጥተው፣ ጥቃቱን መቅረጻቸው ደግሞ "የበለጠ እንደሚያከብደው" ተናግረዋል። በችሎቱ ወቅት ጥፋተኞቹ ያሳዩትን ምግባርም አድንቀዋል።
አቃቤ ሕግ ውሳኔው ለይግባኝ ሰሚ ችሎት መመራት አለበት የለበትም የሚለውን ለመወሰን 28 ቀናት አሉት።















