በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ መካከል የተካረረው ውጥረት እንዳሳሰበው የአፍሪካ ኅብረት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፤ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ መካከል የተካረረው ውጥረት እንዳሳሰበው እና በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ አስታወቀ።
ሦስቱ የኅብረቱ አባል አገራት "ውጥረቱን ከሚያካርሩ እንዲሁም የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ከሚያናጉ ድርጊቶች እና መግለጫዎች እንዲቆጠቡ" አሳስቧል።
ሦስቱ አገራት ልዩነታቸውን በአፍሪካ ኅብረት መርሕ መሠረት "በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች እና በሰማላዊ ንግግር እንዲፈቱ" ኮሚሽኑ አሳስቧል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ትናንት መስከረም 21/2019 ዓ. ም. ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በአገራቱ መካከል የንግግር መስመሮችን "ክፍት አድርጎ መዝለቅ" ያለውን አስፈላጊነት አስምሮበታል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደ አዲስ ካገረሸ ሁለት ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን፤ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች እንደቀጠሉ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ ጋር በመመካከር "መካረሩን ለማርገብ፣ ለንግግር እና ሰላማዊ መፍትሔ ለመስጠት ድጋፍ እንደሚያደረግ" አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በአሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን እንደምትዘጋ ያሳወቀች ሲሆን 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ማቋረጧን አስታውቃለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የግብፅ ዲፕሎማት አሕመድ ሞሐራን አሕመድ ሶሊማን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ስትወስን ግብፅ በበኩሏ የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ኤርትራን እንዲሁም ግብፅን መክሰሳቸው አይዘነጋም።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ብዙም ባልተለመደ መልኩ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱትን ጥምረት በመደገፍ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የግብፅ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡትም፤ ኢትዮጵያ "የውጭ ኃይሎችን ለውስጣዊ ውድቀቶቿ እና ዘላቂ ቀውሶቿ ተጠያቂ ታደርጋለች" ሲሉ የካይሮ ባለሥልጣናት ወንጅለዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ባገረሸበት ማግሥት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ግጭቱ "በአፋጣኝ እንዲቆምም" ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ሊቀ መንበሩ አያይዘውም በቅርቡ በታጣቂ ኃይሎች የተፈጠረው ጥምረት "አለመረጋጋቱን እንደሚያባብስ" ገልጸዋል።
በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል "ግጭትን በማቆም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት" ያለውን ሚና ሊቀ መንበሩ ማሕሙድ አሊ ዩሱፍ ጠቅሰዋል።
ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተገታ በኋላ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ የፌደራል መንግሥቱም የትግራይ አመራሮችም ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል። ለተፈጠሩ ክፍተቶች አንዳቸው ሌላቸውን ሲወቅሱም ነበር።
ሊቀ መንበሩ በበኩላቸው ስምምነቱ "በኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ሰላም የማዕዘን ድንጋይ ነው" ብለዋል።


































