ኢትዮጵያ በአሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሐሙስ መስከረም 21/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ይህንን እርምጃ የወሰደው ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ ለምትፈፅመው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ገልጿል።
ጨምሮም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፈዋል ያላቸው 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ኤርትራን ከከሰሱ በኋላ ነው።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርም አመሻሹን ባወጣው መግለጫ አስመራም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቋል።
"ኤርትራ አደገኛ ግጭቶችን ለማስቀረት ትዕግስት ስታሳይ እና ስትቆጠብ መቆየቷን" የጠቀሰው መግለጫው፣ " አሁን ላይ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ ምላሽ ከመስጠት ውጪ ምርጫ የላትም" ብሏል።
መግለጫው አክሎም "ላለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን እና የባሕር ዳርቻዎችን በመውረር የባሕር በር ማግኘት ግዴታ ነው ስትል በአደባባይ ጦርነት በማዋጅ በኤርትራ ላይ የማያባራ የጥላቻ አጀንዳ ስታራምድ የቆየችው ኢትዮጵያ ናት" ሲል ከስሷል።
ኤርትራ በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ውስጥ በመሳተፍ ተደጋጋሚ ክስ ቀርቦባታል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ማገርሸቱን ተከትሎም የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት ከህወሓት ኃይሎች ጎን በመሰለፍ እየተዋጉ ነው ሲሉ የአፋር ክልል ባለሥልጣናት ለቢቢሲ አማርኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከስሰዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባም በዚህ ሳምንት ለአልጀዚራ በሰጡት መግለጫ የኤርትራ ጦር በክልሉ ላይ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "እየተዋጋን ያለነው የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተሰባሰቡ እና ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ነው" ብለው ነበር።
"ሻዕቢያ [ኤርትራ] እና ቲፒኤልኤፍ [ህወሓት] ያለ ሱዳን፣ ያለ ግብፅ እና ከዚያም ባሻገር ያሉ ኃይሎች ካልደገፏቸው ብቻቸውን ተጣምረውም ቢሆን ዋጋ የላቸውም። ሲነጣጠሉ ደግሞ ትርጉም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ብዙም ባልተለመደ መልኩ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱትን ጥምረት በመደገፍ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል "አገሪቷን እየመራ ያለው የብልጽግን መንግሥት በአገሪቷ ለተፈጠረው ችግር የውጭ ማሳበቢያ ይፈልጋል" ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ አመሻሹን ባወጣው መግለጫው ኤርትራ ከሉዓላዊ አገራት የግንኙነት መርሆዎች ካፈነገጡ ድርጊቶች እንድትቆጠብ አሳስቧል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ጠንካራ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዋጋ እንደምትሰጥ የጠቀሰው መግለጫው፣ ለዚህም በሰላም አብሮ ለመኖር፣ ለቀጣናዊ መረጋጋት እና ግንኙነት ቅድሚያ ሰጥታ መቆየቷን አስረድቷል።
ጨምሮም አገራቱ ያላቸውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ከቀጣናው አገራት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
ሁለቱ አገራት ከግንቦት 1990 እስከ ሰኔ 1992 ዓ.ም. ድረስ ከባድ ጦርነት ያካሄዱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸውን አድሰው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ጳጉሜ 1/2010 ዓ.ም. ነበር ከ20 ዓመታት በኋላ በአሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዳግም የከፈተችው።
ኤምባሲው ዳግም ሲከፈት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገኝተዋል።
ሁለቱ አገራት ዳግም ግንኙታቸውን ካደሱ በኋላ በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ነበሩ።
በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩት ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸው ተሻሽሎ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ውስጥ በጋራ የትግራይ ኃይሎችን ሲዋጉ የነበረ ቢሆንም ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ አለመግባባቶች ተከስተው ግንኙነታቸው ቀስ በቅስ ተቀዛቅዞ ወደ ፍጥጫ አምርቷል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን በይፋ ካሳወቀች በኋላ በኤርትራ ዘንድ ቁጣ የተፈጠረ ሲሆን ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።



































