ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለፉት 5 ወራት አሜሪካ የወሰደቻቸው 5 እርምጃዎች
ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት እንዲገታ ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው አካላት መካከል የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ ይጠቀሳሉ።
አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ምዕራባውያን አገራት አንዷ ናት።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከሳምንታት በፊት ዳግም ሲቀሰቀስ ቀድመው መግለጫ ካወጡ አገራትም አንዷ ናት።
አሜሪካ ከጦርነት መነሳት በፊት እና በኋላ የወሰደቻቸውን እርምጃዎች እንደሚከተለው ቃኝተናል።
የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ማንሳት
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ማንሳቷን ያስታወቀችው ግንቦት 3/2018 ዓ. ም. ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር መከላከያ ንግድ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት እንዳለው በኢትዮጵያ ላይ ይከተል የነበረውን የክልከላ ፖሊሲን አንስቷል።
በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ዝውውር ደንብ (ITAR) ቁጥጥር የሚደረግባቸውን እና ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ የፈቃድ ማመልከቻዎችን በየተራ እየገመገመ መሆኑንም አስታውቆ ነበር።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ዝውውር ደንብ (ITAR 126.1) ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙ አገራት ተርታ እንድትሰረዝ የተደረገው በትግራይ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነበር።
ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የተጣለባት በትግራይ ጦርነት ምክንያት ነበር።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ለማንሳት ከውሳኔ ላይ የደረሰችበትን ምክንያት በይፋ አልገለጸችም።
የአሜሪካ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፖሊስ፣ ለደኅንነት እና ለሌሎችም የአገር ውስጥ የደኅነንት ኃይሎቿ የሚውሉ የመከላከያ ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን ከውጭ ገዝታ ማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ አገራት መላክ ያስችላታል።
አሜሪካ በኤርትራ የመከላከያ ኃይል እና ሌሎች ተቋማት ላይ የተጣለውን ማዕቀብም ማንሳቷ አይዘነጋም።
በህወሓት መሪዎች ላይ የተጣለው የቪዛ ማዕቀብ
አሜሪካ በህወሓት አባላት እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ የጣለችው ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ነበር።
ለዚህም ምክንያት ያለችው "በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት ውስጥ ተሳታፊ" መሆናቸውን ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ "በአክራሪ" ህወሓት አባላት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንዲያገረሽ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ይህም "በቀጣናው ያለውን ሰላም እና መረጋጋት የሚያናጋ ነው" ሲል ገልጾ ነበር።
የቪዛ ክልከላው የተጣለው በትግራይ ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፉ እና በተባባሪዎቻቸው ላይ መሆኑ ተገልጿል። ህወሓት የቪዛ ክልከላውን ተቃውሟል።
በወቅቱ የህወሓት አመራሮች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በማድረግ በክልሉ ነዋሪዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ሲወነጀሉ እንደነበር ይታወሳል።
የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ እንዲወያይ መጠየቅ
የመንግሥታቱ ድርጅት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስላላው ወቅታዊ ሁኔታ በአሜሪካ ጠያቂነት በፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ የተጠየቀው በዚህ ሳምንት ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና ፀሐፊ ማርቲን ኪማኒ ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በውይይቱ ስለተላለፉ ውሳኔዎች እስካሁን ይፋዊ መረጃ አልወጣም።
አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲወያይ ከመጠየቋ አስቀድሞ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለምክር ቤቱ በጻፉት የተናጠል ደብዳቤ አንዳቸው ሌላቸውን ከስሰዋል።
ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤ ልካለች።
"ኤርትራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን በመጣስ ወረራ ፈጽማለች፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የወረራው ሰለባ ናት" ስትል ኢትዮጵያ አስታውቃለች።
ኤርትራ በምላሹ ለፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ "ራስን በመከላከል ስም" በሉዓላዊት የተመድ አባል ላይ የምትፈጽመውን ጦርነት ምክንያታዊ ለማድረግ እየሞከረች ነው ስትል ወንጅላለች።
በትግራይ ጦርነት ዳግም ከተጀመረ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በብዛት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች መታየታቸው ቢቢሲን ጨምሮ በሌሎችም መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል።
የአምባሳደር ማሲንጋ መግለጫ
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግመኛ መቀስቀሱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት በተመለከተ የህወሓት አመራሮችን "መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት" ከስሰዋል።
የህወሓት መሪዎች "መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመክፈት ባሳለፉት ደካማ ውሳኔ ማዘናቸውን" መግለጻቸውም ይታወሳል።
ህወሓት ከፍተኛ አመራር እና የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ በአምባሳደሩ ወቀሳ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በወቅቱ ባወጡት መግለጫ "ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በዚህ ጦርነት ውስጥ ባለመግባት ብልህ እንዲሆኑ" መክረዋል።
ጦርነት ዳግመኛ ከመነሳቱ ከቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራውን መንግሥት ከሥልጣን ማስወገድ ዓላማው ያደረገ ነው የተበላው "ትብብር ለኅልውና" የተሰኘ ጥምረት መመሥረቱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በጥምረቱ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አፋብን)፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) ጨምሮ ሌሎችም ታጣቂ ቡድኖች ይገኙበታል።
የአሜሪካው አምባሳደር በህወሓት መሪዎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ውዝግብ በተባባሰበት ወቅት በተደጋጋሚ ወደ መቀለ አምርተው ከህወሓት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ለማድረግ መሞከራቸው ይታወሳል።
የህወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ አማኑኤል አሰፋ የአምባሳደር ማሲንጋን መግለጫ "ፍትሐዊ አይደለም" ሲሉ በወቅቱ አጣጥለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር የስልክ ውይይት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በስልክ ተወያይተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ንግግራቸው "ከኤርትራ ጋር እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት" የተመለከተ መሆኑ ተገልጿል።
"የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁሉም ወገኖች በኩል ውጥረት ማርገብን ይደግፋሉ" ይላል መግለጫው።
ለውስጣዊ እንዲሁም ውጭያዊ ውጥረቶች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ውይይት መሆኑም ተመልክቷል።
ማርኮ ሩቢዮ "ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት የጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር አለባቸው" ማለታቸው ተጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም አገራቱ "ድንበር ተሻጋሪ ወረራ እንዳይፈጽሙ" አሳስበዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት "ቀጣናው ሌላ ግጭት መቋቋም አይችልም" ማለታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከማርኮ ሩቢዮ ጋር መወያየታቸው የተሰማው በአሜሪካ ጥያቄ የመንግሥታቱ ድርጅት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስላላው ወቅታዊ ሁኔታ በዝግ ከተወያየ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው የውይይቱን ዝርዝር ሳይጠቅሱ "በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮች ላይ እጅግ ፍሬያማ የሆነ የስልክ ውይይት አድርጌያለሁ" ብለዋል።