የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም ሲል አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የውጭ ዜጎች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ እንደገና ማመልከት አይችሉም ሲል ወሰነ።
የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ተገቢ ሕግ ሳይወጣ ያለገደብ በተደጋጋሚ ማመልከቻዎችን እንዲቀርቡ መፍቀድ "ማቆሚያ የሌለው ሂደትን" ሊፈጥር እንደሚችል አስታውቆ፣ ከአገር መባረርን ሊከላከል እና የአስተዳደር ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብሏል።
የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሊዮን ሽሬይበር ውሳኔውን በስደተኞች ሥርዓት ላይ የተፈፀመውን "በደል" ላይ የተገኘ "ትልቅ ድል" ሲሉ አወድሰውታል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሁለት የቡሩንዲ ዜጎች ያቀረቡትን እና ለረዥም ጊዜ ሲታይ ለቆየው አቤቱታ መቋጫ የሰጠ ነው።
ሁለቱ ብሩንዳውያን እአአ በ2014 የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ ዳግም በ2018 የጥገኝነት ማመልካቻ አስገብተው ነበር።
ሁለቱ ግለሰቦች አዲሱ ማመልከቻቸው እአአ በ2015ቱ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ቡሩንዲ በፖለቲካዊ ነውጥ ስለታመሰች ዳግም ሊታይ ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ ጊዜ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በተነሳ አለመረጋጋት ቢያንስ 70 ሰዎች ተገድለዋል።
የቡሩንዲ ዙጎች ጉዳያቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ቢያሸንፉም ነገር ግን ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ውሳኔውን ሽሯል።
የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍረድ ቤት የመጨረሻው የይግባኝ ሰሚ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ (ዩኤንኤችሲአር) በ2025 ደቡብ አፍሪካ ከ167,000 በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ማስተናገዷን ገልጿል።
ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት ከቡሩንዲ፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሩዋንዳ እና ከዚምባብዌ የመጡ ይገኙበታል።
ሽሬበር ውሳኔውን መንግሥት "ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማስተዳደር የበለጠ ውጤታማ እና ፍትሃዊ ስርዓት ለመዘርጋት" ለሚያደረገው ጥረት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኒውዝሩም አፍሪካ ለተባለ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ክርክር ማድረጉን አስረድተዋል።
ሽሬይበር ይህ እርምጃ ግለሰቦች በተደጋጋሚ በመሞከር "አዳዲስ ማመልከቻዎችን በማቅረብ ስርዓቱን ያለማቋረጥ እንዲበበዘብዙ" ያስችላቸዋል ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ በሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ በተነሳው ተቃውሞ እየተናጠች ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዋና ዋና ከተሞች ወደ ጎዳናዎች በመውጣት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞችን ከአገር እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በርካታ የአፍሪካ መንግሥታት በደቡብ አፍሪካ ዜጎቻቸው ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶችን አስጠንቅቀው ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ራማፎሳ "ጥቅም ፈላጊዎች" በውጭ ዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ ጸረ ስደተኛ ጥቃቶችን እንዳቀነባበሩ ተናግረዋል።
"በቅርቡ በአገራችን በውጭ ዜጎች ላይ የቀረቡት ተቃውሞዎች እና የተፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ አመለካከት አይወክሉም እንዲሁም የመንግሥታችንን ፖሊሲ አያንጸባርቁም" ሲሉ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አስታውቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ ወደ 2.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መኖሪያ ስትሆን ይህም ከጠቅላላው ሕዝብ 4 በመቶ ያነሰ ነው።
ብዙዎቹ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንደሚኖሩ ይገመታል።
በአፍሪካ ውስጥ በኢንዱስትሪ የበለፀገች አገር እንደመሆኗ መጠን፣ ከአህጉሪቱ የተውጣጡ በርካታ ሰዎች ሥራ ለመፈለግ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይጓዛሉ።














