ዶናልድ ትራምፕ በአምሳያቸው የተሠሩ የኤንኤፍቲ ስብስቦችን ለገበያ አቀረቡ

ትራምፕ ካርድ

የፎቶው ባለመብት, COLLECTTRUMPCARDS.COM

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእሳቸው ፊት አምሳያ የተሰሩ የዲጂታል ሥነ ጥበብ ሥራዎችን ይፋ በማድረግ ለገበያ አቀረቡ።

ትራምፕ እነዚህ ውስን የሆኑት ዲጂታል ካርዶች የሥራ እና የጥበብ ሕይወቴን የሚያንጸባርቁ ናቸው ብለዋል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ይፋ የማደርገው ጉዳይ አለ ማለታቸውን ተከትሎ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳግም ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ምክትላው አድርገው የሚያቀርቡትን ዕጩ ይፋ ሊያደርጉ ነው ተብሎ በስፋት ተጠብቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አዲስ ይፋ ያደረጉትን የኤንኤፍቲ ስብስብ በቪዲዮ መልክ አስተዋውቀዋል።

እያንዳንዳቸው በ99 ዶላር ለገበያ ከቀረቡት የዲጂታል ሥነ ጥበብ ሥራዎች መካከል አንዱ ልዕል ኃያል ሆነው የሚያሳየው ይገኝበታል።

ኤንኤፍቲ (NFT) ምንድነው?

NFT የሚለው Non-fungible token የሚለው ምሕጻረ ቃል የሚወክል ነው።

የnon-fungible (ነን-ፈንጀብል) ምጣኔ ሃብታዊ ትርጉም ደግሞ መተኪያ የሌለው፤ በሌላ የማይቀየር ነገር ማለት ነው።

ሰዎች የዶናልድ ትራምፕን ኤንኤፍቲ በ99 ዶላር ሲገዙ የገዙት ዲጂታል ካርድ ብቸኛው ባለቤት ይሆናሉ።

ከክሪፕቶከረንሲ ተቀባይነት መጨመር ጋር ተያይዞ የዲጂታል ሥነ ጥበብ ሥራዎች በኤንኤፍቲ በስፋት መሸጥ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

የዲጂታል ጥበብ ብቸኛ ባለቤት የመሆን ፍላጎት እንዲሁም ኤንኤፍቲ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው የሚሉ ምክንያቶች የዲጂታል ሥነ ጥበብ ሥራዎች በኤንኤፍቲ አማካይነት ግብይታቸው እንዲጨምር አድርገዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እነዚህን ዲጂታል ካርዶች ሲያስተዋውቁ ጥሩ የገና ስጦታ ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።

ያልተጠበቀው የትራምፕ አካሄድ ከትችት አላመጠም። ተጽዕኖ ፈጣሪ ሪፐብሊካኖችን ጨምሮ በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የትራምፕን ውሳኔ አብጠልጥለዋል።

የትራምፕ የቀድሞ ስትራቴጂስት ስቲቭ ባነን፤ “ከዚህ በላይ መታገስ አልችልም” ካሉ በኋላ በትራምፕ ዲጂታል ካርዶች ላይ ተሳትፎ ያደረጉ “ዛሬውኑ ከሥራቸው መባረር አለባቸው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ ለዶናልድ ትራምፕ ምላሽ በሚመስል መልኩ በቅርብ ቀናት ያከናወኗቸውን ሥራዎች ዘርዝረዋል።

ፕሬዝዳንቱ የዋጋ ንረትን ማረጋጋታቸውን፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የከናወኗቸውን በትዊተር ገጻቸው ዝርዝረዋል።