ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ከስምምነት የደረሱባቸው የመግባቢያ ነጥቦች ይፋ ሆኑ

አሜሪካ እና ኢራን ከሦስት ወራት በላይ የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ። በመካከለኛው ምሥራቅ ብሎማ በመላው ዓለም ከባድ ቀውስን አስከትሎ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም ለወራት ሲደረግ የነበረው ድርድረ አርብ ዕለት ስዊትዘርላንድ ውስጥ በሚካሄድ የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ይቋጫል ተብሏል። አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱ እንዲቆም በደረሱት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ጦርነቱ እንደሚቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደሚከፈት ተዘግቧል።

ጭምቅ ሃሳብ

አሜሪካ እና ኢራን ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ጦርነቱን ለማቆም ተስማሙ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የተባበሩት መንግሥታት እና የተለያዩ አገራት በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አደነቁ

    ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ ቃል አቀባይ “ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን የሰላም ስምምነቱ ላይ መድረሳቸውን ይፋ በማድረጋቸው” ደስተኛ መሆናቸውን ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ አክለውም “ይህ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ እርምጃ” መሆኑን ገልጸዋል።

    የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱን ካደነቁ የዓለም መሪዎች መካከል ናቸው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጃፓን “በሆርሙዝ ወሽመጥ ነጻ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ በተግባር እንደሚረጋገጥ በብርቱ ተስፋ ታደርጋለች” ካሉ በኋላ “በኢራን የኒውክሌር እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ስምምነት በቅርቡ ይደረሳል” ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒሲትር አንቶኒ አልባኔዝ ስምምነቱ “ቋሚ እና ዘላቂ ሰላም” ያመራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    “ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድም ይህንን ወሳኝ የንግድ መተላለፊያ መልሶ መክፈት በኢነርጂ ዋጋ እና ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ይቃለላል” ብለዋል።

    የኒው ዚላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊንስተን ፒተርስ “ወሳኝ እና ገንቢ ስምምነት” እንዲሁም “ውጥረትን ለመቀነስ እንዲሁም መረካካትን ለዓለም ምጣኔ ሀብት ደኅንነት ወሳኝ በሆነው ቀጣናው ለማምጣት” ቁልፍ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን ከስምምነቱ በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ አሜሪካን እና ኢራንም እንዲሁ በድርድሩ ውስጥ የተሳተፉትን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

    “ይህ ቀጣናዊ መረጋጋት ለማምጣት እና ዓለም ምጣኔ ሀብትን ለማረጋጋት ጥሩ ዕድል ነው” ብለዋል።

    ስምምነቱ በፍጥነት እና በተሟላ መልኩ ተግባራዊ አንዲሆን ጥሪ ያቀረቡት አገራቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ያለገደብ” እንዲከፈት ጠይቀዋል።

  2. አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማቆም ከስምምነት የደረሱባቸው የመግባቢያ ነጥቦች ይፋ ሆኑ

    የአሜሪካ እና ኢራን ባንዲራዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በቴህራን እና ዋሺንግተን መካከል ጦርነቱን ለማስቆም ስምምነት በተደረሰበት የመግባቢያ ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ነጥቦችን ይፋ አድረገዋል።

    የመገናኛ ብዙኃኑ ባቀረቧቸው ዝርዝሮች ውስጥ የተካተቱት ነጥቦች በሁለቱም ወገን ማረጋገጫ አልተሰጠባቸውም።

    ሜህር የዜና ወኪል ከዘረዘራቸው ነጥቦች መካከል

    • በሁሉም ግንባሮች ሊባኖስን ጨምሮ በቋሚነት ተኩስ ይቆማል
    • አሜሪካ በኢራን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም
    • በ30 ቀናት ውስጥ የአሜሪካ የባሕር ዕገዳ ይነሳል
    • የአሜሪካ ጦር ከኢራን ለቅቆ ይወጣል
    • የሆርሙዝ ወሽመጥ “በኢራናውያን ቁጥጥር” በ30 ቀናት ውስጥ ዳግም ይከፈታል
    • አሜሪካ እና አጋሮቿ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ያቀርባሉ
    • በኢራን የነዳጅ ዘይት እና ኢነርጂ ምርቶች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሳት
    • ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ላለማምረት ዳግም ታረጋግጣለች
    • አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ጦር አትጨምርም እና አዲስ ማዕቀብም አትጥልም

    ሜህር አክሎም የስምምነቱ መጨረሻ የኢራን እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ግማሽ ሃብቷ እስኪለቀቅ፣ የኢራን ነዳጅ ዘይት ላይ የተጣለው ማዕቀብ እና የባሕር ላይ ዕገዳው እስኪነሳ ድረስ የመጨረሻው ድርድር አይጀመርም ሲል ዘግቧል።

    እንዲሁም የመጨረሻው ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚጸድቅ ዘግቧል።

  3. 15 ሰዓት የፈጀ ንግግር ወደ ስምምነት አድርሷል

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዘም ጋህሪባባዲ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዘም ጋህሪባባዲ

    የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኳታር አሸማጋዮች ትናንት በቴህራን ተገኝተው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ከስምምነት እንዲደረስ በረቂቅ የመግባቢያ ሰነዱ ላይ “ከ14 እስከ 15 ሰዓታት ያህል የረዘመ ንግግር” ማድረጋቸውን ገለጹ።

    ካዘም ጋህሪባባዲ ለኢራን መገናኛ ብዙኃን ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት “ይህ ድርድር ረዥም ጊዜ የወሰደ ነው” ብለዋል።

    “የኳታር የልዑካን ቡድን ኢራን እና በዩናይትድ ስቴትስ ኢዝላማባድ ባቀረበችው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ዙሪያ ውይይቶታቸውን እንዲቋጩ ለማስቻል ትናንት ቴህራን ነበሩ” ብለዋል።

    “ወደ 14 እና 15 ሰዓት የፈጀ ረዥም ንግግር ተካሄዷል። በዚህ ጊዜ የእስላማዊ ሪፐብሊክ ሰነዱ ላይ የመጨረሻውን ማሻሻያ አቅርባለች። እነዚያ ማሻሻያዎች ተቀባይነት አግኝተዋል። እንዲሁም ኢዝላማባድ ያቀረበችው የመግባቢያ ሰነድ ጸድቋል”

    ምክትል ሚኒስትሩ የኢራን ዋና ፍላጎት የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ ቢሆንም ”በርካታ የምታነሳቸው ጉዳዮች ስላሏት” የስምምነቱ የመጨረሻው ክፍል ላይ በ60 ቀናት ውስጥ ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።

  4. ስምምነቱ “መካከለኛው ምሥራቅን ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት በመሠረታዊነት የሚለውጥ ነው”-ቫንስ

    ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ለፎክስ ኒውስ ስምምነቱ “በመሠረታዊነት መካከለኛው ምሥራቅን ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት የሚለውጥ ነው” ሲሉ ተናገሩ።

    “ይህ የዓለማችን ቀጣና በእኔ የእድሜ ዘመን በሙሉ ከዚያም ለረዘመ ጊዜ የአለመረጋጋት ምንጭ ነበር” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃኑ ገልጸዋል።

    ቫንስ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የኢራንን ስጋትነት ማስወገድ ችለዋል” ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።

    አክለውም አሁን “የመካከለኛው ምሥራቅ ብልጽግና እና ስኬት አዲስ ዘመንን መገንባት ይቻላል” ብለዋል።

    “እውነቱን ለመናገር ከቀጣናው ለአሜሪካ ሕዝብ በርካታ ሃብት ማመንጨት እንችላለን” ሲሉም ተደምጠዋል።

  5. አሜሪካ እና ኢራን በሁሉም ግንባሮች፣ ሊባኖስን ጨምሮ ጦርነቱን ለማቆም ተስማሙ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ከሦስት ወር በላይ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናገሩ።

    ፕሬዚዳንቱ “ከእስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር እያደረግን የነበረው ስምምነት አሁን ተሟልቷል” ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸወ ላይ አስታውቀዋል።

    ትራምፕ ስምምነቱን ተከትሎ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ዘግቶት የነበረውን የኢራን ወደብ እንዲከፍት ያዘዙ ሲሆን መርከቦችም ያለምንም ክፍያ በወሽመጡ መጓዝ እንዲጀምሩ ተናግረዋል።

    “የዓለም መርከቦች አሁን ሞተራችሁን አንቀሳቅሱ። ነዳጅ መፍሰሱን ይቀጥል።”

    ሁለቱን አገር ስታደራድር የነበረቸው ፓኪስታን በጠቅላይ ሚኒስትሯ ሼህባዝ ሻሪፍ በኩል ባወጣችው መግለጫ ደግሞ “በተከታታይ ከተደረገ ንግግር በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ እና የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መካከል ስምምነት ላይ መደረሱን ስናሳውቅ በደስታ ነው” ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ሁለቱም ወገኖች አሁኑኑ በሁሉም ግንባሮች፣ ሊባኖስን ጨምሮ ቋሚ የሆነ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማቋረጥ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

    “የፊርማ ሥነ ስርዓቱ አርብ ሰኔ 12 በስዊዘርላንድ ይካሄዳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ለማቆም ዲፕሎማሲያዊ መንገድን ለመፈለግ ላሳዩት ቁርጠኝነት እናመሰግናለን።"

    ለድርድሩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ያሏቸውን ኳታርን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ እንዲሁም ቱርክን ጨምረው አመስግነዋል።

    “ከስምምነት ላይ በመደረሱ በዚህ ሳምንት ተከታታይ የሆኑ ስብሰባዎችን እናዘጋጃለን። ይህ የቅድመ ትግበራ ውይይት ዝርዝር ነገሮችን ለመነጋገር እና ለይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓቱ መሠረት የሚጥል ይሆናል”ብለዋል።

    ኢራን በበኩሏ በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ካዘም ጋሪባባዲ በኩል ሁለቱ አገራት ከስምምነት መድረሳቸውን አረጋግጠው አርብ እንደሚፈረም ተናግረዋል።

    “ከአሁን ጀምሮ በሁሉም ግንባሮች የሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎች፣ ሊባኖስን ጨምሮ እንደሚቆሙ" ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው፣ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴን ላይ የጣለችውን እገዳም እንደምታነሳ አስታውቀዋል።