በየመን የባህር ዳርቻ የታገተች አንዲት ነዳጅ ጫኝ መርከብ ወደ ሶማሊያ ተወሰደች

የኤደን ባሕረ ሰላጤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የባህር ላይ ወንበዴዎች አንድ የነዳጅ መርከብ ከየመን የባህር ዳርቻ አግተው ወደ ሶማሊያ መውሰዳቸውን የደህንነት ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የየመን የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ቀደም ሲል እንደገለጹት ኤምቲ ዩሬካ የተባለው መርከብ ተጠልፎ ወደ ሶማሊያ ተወስዷል።

የሶማሊያ የደህንነት ምንጮች እንዳሉት በቃና ወደብ አቅራቢያ የሚገኘው የኤደን ባሕረ ሰላጤ በባሕር ላይ ወንበዴዎች እጅ ወድቋል።

ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ሦስት የደህንነት ባለሥልጣናት የባህር ወንበዴዎቹ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የምትገኘውን ቃንዳላ የባህር ዳርቻ ከተማን ለቅቀው ወጥተዋል ብለዋል።

ከሳምንት በፊት በሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች የተጠለፈውን የሆነር 25 መርከብን ተከትሎ በ10 ቀናት ውስጥ በአካባቢው ሌላ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ሲጠለፍ ይህ ሁለተኛው ነው።

ሆነር 25 ወደ ሞቃዲሾ እያመራ የነበረው 18 ሺህ 500 በርሜል ነዳጅ ጭኖ ነበር።

ኤምቲ ዩሬካ ከመታገቷ በፊት የምዕራብ አፍሪካዊቷ ቶጎን ባንዲራ እያውለበለበች የነበር ሲሆን ቅዳሜ ንጋት 11፡00 ሰዓት ላይ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መወሏን የደህንነት ባለሥልጣናቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መርከቧ በአሁኑ ወቅት በየመን እና በሶማሊያ መካከል ባለው የኤደን ባሕረ ሰላጤ እየቀዘፈች ሲሆን በሚቀጥሉት ሰዓታት በሶማሊያ የውሃ ክልል መልሕቋን እንደምትጥል ይጠበቃል።

የዩናይትድ ኪንግደም የባህር ትራንስፖርት ኦፕሬሽን (ዩኬኤምቲኦ) አርብ ዕለት እንደገለጸው ከሆነ " የታጠቁ ሰዎች" በጀልባ በመሆን በየመን አል-ሙካላ አቅራቢያ ወደሚገኝ መርከብ ተጠግተው ነበር።

ሦስት የተለያዩ የደህንነት ባለሥልጣናት እንደገለጹት እነዚህ የታጠቁ ሰዎች በካልኡላ (አሉላ) የአሳ ማጥመጃ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኝ የባህር ዳርቻ አካባቢ የተነሱ ናቸው።

ካልኡላ የባሐረር ላይ ወንበዴዎእ የኤምቲ ዩሬካን ለመያዝ ከሄዱበት ቦታ 209 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

እነዚህ ሁለት ጠለፋዎች በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ አካባቢ እየተስፋፋ የመጣውን የባሕር ላይ ውንብድና ያሳያሉ ተብሏል።

ዛሬ እገታ በሁለት ሳምንታት ብቻ በባሕር ላይ ወንበዴዎች ቁጥጥር ስር የገቡትን መርከቦች ቁጥር አራት አድርሶታል።

የሶማሊያ ባለሥልጣናትም ሆነ በሶማሊያ ውሃዎች ላይ የባሕር ላይ ውንብድናን የሚከላከለው የአውሮፓ ኅብረት የባህር ኃይል ስለሰሞኑ እገታዎች ምንም አላሉም።

ከ2011 ጀምሮ እየቀነሰ የመጣው የሶማሊያ የባህር ላይ ዝርፊያ እአአ ከ2023 መጨረሻ ጀምሮ የሁቲ አማጽያን በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በቀይ ባህር መርከቦች ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ እንደገና ጨምሯል።

በጥቃቶቹ የተነሳ ዓለም አቀፉ የባህር ኃይል የሁቲ ስጋትን ወደ መከላከል ትኩረቱን ሲያደርግ፣ በሶማሊያ የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙ የታጠቁ ቡድኖች ክፍተቱን ተጠቅመው መርከቦችን ማገት ጀምረዋል።

"እየተካሄደ ያለው የባህር ላይ ውንብድና ብዙዎች ከሚያስቡት በላይ የከፋ ነው። በሁሉም የባህር ዳርቻ የታጠቁ ቡድኖች እንቅስቃሴ እየጨመረ ነው" ሲሉ የፑንትላንድ ክልል የጸጥታ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።