የአዲስ አበባ አየር ከሌሎች ከተሞች ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ተበክሏል?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ዛሬ ዓለም አቀፍ የንጹሕ አየር እና የሰማያዊ ሰማይ ቀን ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ከስድስት ዓመታት በፊት ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ነው ቀኑ መታሰብ የጀመረው።

የአየር ብክለትን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።

የአየር ብክለት በሰው ልጆች ጤና ላይ ከፍተኛ አደጋ ጋርጧል።

በመላው ዓለም ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በተከሰቱ እንደ ልብ ድካም እና የመተንፈሻ አካል ሕመምን በመሳሰሉ በሽታዎች ተይዘው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።

ናሳ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት በአዲስ አበባ ያለውን የአየር ብክለት ይመለከታል።

የማገዶ እንጨት ሲቃጠል፣ በመኪና ጭስ ወይም በሌሎች በካዮች ምክንያት ብላክ ካርበን የተባለው እጅግ ጥቃቅን ቅንጣት ይበተናል።

ጥናቱ በአዲስ አበባ ስላለው የብላክ ካርበን መጠን እንዲሁም በተለያየ ሰዓት ወይም ወቅት የሚፈጠረውን የአየር ብክለት ለውጥ ያሳያል።

የትራፊክ መጨናነቅ ባለባቸው ሰዓቶች እንዲሁም በዓመት በዓል ወቅት የአየር ብክለት ይጨምራል።

ናሳ በአዲስ አበባ ላይ ባደረገው ጥናት የደረሰበት ግኝት አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ ከተሞች "ጠቃሚ" እንደሆነ ተመልክቷል።

የአየር ብክለት ላይ ምርምር የሚሠሩ ባለሙያዎች የአየር ብክለት በአንድ ከተማ፣ አገር ወይም አህጉር ብቻ ታጥሮ የሚቀር ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ።

አዲስ አበባ በብላክ ካርበን መጠን አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የሕንዷ ዴልሂ፣ የባንግላዲሽ ዳካ፣ የናይጄሪያ ሌጎስ እና የፓኪስታን ካራቺ ከተሞች ከአንድ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ተሰጥቷቸዋል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን ቢልልኝ ላለፉት 34 ዓመታት በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዩታ እና በኖርዝ ካሮላይና አግሪካልቸራል ኤንድ ቴክኒካል ስቴት ዩኒቨርስቲ ሲያስተምሩ እና ሲመራመሩ ቆይተዋል።

ናሳ ይፋ ካደረገው ግኝት በተጨማሪ የአዲስ አበባ የአየር ብክለትን በተመለከተ በቅርቡ ይፋ የተደረገ ሌላ ጥናት የተሠራው እሳቸውን ጨምሮ በሌሎችም ባለሙያዎች ነው።

በአዲስ አበባ ከፍተኛ መጠን ያለው ብላክ ካርበን እንደተገኘ በጥናታቸው ተጠቅሷል።

ጠዋት ላይ በርካታ ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት እና የትራፊክ መጨናነቅ በሚከሰትበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የአየር ብክለት የተስተዋለ ሲሆን ወደ ቀትር አካባቢ ምጣኔው ይቀንሳል።

ጠዋት ባለው የትራፊክ መጨናነቅ ከሚከሰተው የአየር ብክለት አንጻር ምሽት ላይ ባለው እንቅስቃሴ የሚከሰተው የአየር ብክለት ያነሰ እንደሆነም ተገልጿል።

ናሳ በአዲስ አበባ ጥናት ያደረገው ከአውሮፓውያኑ 2022 እስከ 2025 ድረስ ነው።

በጥናቱ ወቅት ኢትዮጵያ የአየር ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዷም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ናት።

የአዲስ አበባ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ዕቅድም ተጠቃሽ ነው።

በሌላ በኩል የሳይክል መንገዶች መስፋፋት እና የኤሌክትሪክ መኪናዎች መሠረተ ልማስ መስፋፋት ይገኙበታል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ 99 በመቶው የዓለም ሕዝብ የሚተነፍሰው አየር ተበክሏል። ታዳጊ አገሮች የበለጠ ተጎጂ ናቸው።

በየዓመቱ ከ4 ሚሊዮን እስከ 7 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በአየር ብክለት ሳቢያ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ እየተወሰዱ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከልን ያማከሉ እርምጃዎች "በትክክለኛው አቅጣጫ" የሚደረጉ ጉዞዎች ናቸው። ሆኖም ፖሊሲዎቹ "አፈጻጸም እና በአገር አቀፍ ደረጃ ትግበራ" ይጎድላቸዋል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን የተሳተፉበት ጥናት ምሽት ላይ የሚስተዋለው ልቀት ምግብ ከማብሰል ጋር በተያያዘ እንደሚጨምር ያሳያል።

የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች፣ የከፍተኛ ተሽከርካሪዎች ዝውውር እና በአውቶብስ ማቆሚያ ሥፍራዎች ያለው ልቀት የአየር ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ ይናገራሉ።

በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ዒላማ ያደረጉ ችግሩን መቅረፍ የሚቻልባቸው መንገዶች መተግበር እንዳለባቸውም ያስረዳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ የአየር ብክለት ልኬት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል።

ብላክ ካርበን በሰው ልጆች ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል አየር ላይ የሚለቀቅ ጥቃቅን ቅንጣት ነው።

የናሳ የጥናት ግኝት በአዲስ አበባ ያለው የብላክ ካርበን መጠን በአሜሪካ ከሚገኙ ሦስት ከተሞች (ሎስ አንጀለስ፣ አትላንታ እና ቦስተን) አንጻር "ከአራት እስከ ዘጠኝ እጥፍ የላቀ" እንደሆነ ያሳያል።

በአየር ላይ የሚንሳፈፉ ቅንጣቶች (ፓርቲኩሌት ማተር ወይም ፒኤም 2.5) በሰው ልጆች ላይ የተለያዩ የጤና እክሎች የሚያስከትሉ ሲሆን፤ በመላው ዓለም በየዓመቱ ከሚከሰቱ የ4.9 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ጋር የሚተሳሰር እንደሆነ የናሳ ጥናት ያጣቅሳል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን የተሳተፉበት ጥናት በአዲስ አበባ ያለው የፒኤም2.5 ዋነኛ ምንጭ እንጨት ሲቃጠል የሚወጣው ጭስ፣ የነዳጅ መኪና ጭስ ብክለት፣ ቆሻሻ ሲቃጠል የሚለቀቀው ጭስ እና በአገባቡ ካልተገነቡ መንገዶች የሚወጣው የአየር ብናኝ እንደሆነ ያትታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በኖርዝ ካሮላይና አግሪካልቸራል ኤንድ ቴክኒካል ስቴት ዩኒቨርስቲ እና በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኖርዝ ካሮላይና ቻፔል ሂል ባለሙያዎች የተሠራው ይህ ጥናት፤ እጅግ የተጨናነቀ የትራፊክ እንቅስቃሴ ያለባቸው አደባባዮች ያላቸውን የአየር ብክለት መጠን ይዳስሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ባስቀመጠው አሐዝ፤ አዲስ አበባ ውስጥ 6 ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ያሉ ሲሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2050 ቁጥሩ ከ10 ሚሊዮን እንደሚሻገር ይጠበቃል።

ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚዳርገው የአየር ብክለት በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከዚህ ቀደም የወጡ ጥናቶችም አሳይተዋል።

በአየር ብክለት ሳቢያ ከሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች መካከል የልብ ሕመም፣ ስትሮክ፣ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ)፣ የሳምባ ካንሰር፣ አስም፣ ፓርኪንሰንስ እና አልዛይመርስን መጥቀስ ይቻላል።

በአውሮፓውያኑ 2019 በመላው አፍሪካ በአየር ብክለት 1.1 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል፤ ይህም በ2021 ከደም ግፊት ቀጥሎ ሁለተኛው ገዳይ ተብሏል።

በአየር ብክለት ምክንያት በ2021 በዓለም 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል።

ከ709 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ናቸው።

በአዲስ አበባ ያለው የብላክ ካርበን መጠን፤ እንጨት (ችቦ) ከሚቃጠልባቸው ሁለት ዓውደ ዓመቶች ጋር በተያያዘ መጠኑ እንደሚጨምር የናሳ ጥናት ያሳያል። የመኪና ጭስም ብክለቱን ያባብሳል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን የተሳተፉበት ጥናት ላይ ናሙና የተወሰደው ከአራት ኪሎ፣ አውቶብስ ተራ፣ አያት አደባባይ፣ ቦሌ፣ ጀሞ፣ ቃሊቲ፣ ቁስቋም ማርያም፣ መገናኛ እና ሜክሲኮ አደባባይ ነው።

ጠዋት ላይ የትራፊክ መጨናነቅ ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅት ከፍተኛ የአየር ብክለት እንደሚታይ በጥናቱ ተቀምጧል።

በሌላ በኩል ምሽት ላይ ምግብ በሚበስልበት ወቅትም ብክለት ይከሰታል።

የናሳ ጥናት ላይ "በምሽት ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ ቢቀንስም እንኳን ከእንጨት ጭስ እና ሌሎችም የነዳጅ ዓይነቶች ከፍተኛ ልቀት ይስተዋላል" ይላል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚናገሩት፤ በጥናታቸው ግኝት መሠረት በከተማው የአየር ብክለት መጠን የሚለካባቸው ቋሚ የቁጥጥር ማዕከላት መቋቋም አለባቸው።

በተመረጡ ሥፍራዎች ላይ አነጣጥሮ የበካዮችን መነሻ ማጥናት ያስፈልጋል ይላሉ። በካዮች በሚበዙባቸው ሥፍራዎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ብክለት ቅነሳ ሥራዎችን መተግበርም ተያይዞ ይነሳል።

ከአካባቢ ጥበቃ እና የጥናት ተቋማት፣ ከዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር የአየር ንጽሕናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሳይንሳዊ ግኝቶችን መተግበር ሌላው ምክረ ሐሳብ ነው።

ናሳ የሠራውን ጥናት "የፒኤም 2.5 መጠን ከጤና ጋር ያለውን ትስስር" እንደሚያሳይ ጠቅሶ፤ የፓርቲኩሌት ማተር ብክለትን በተሻለ ሁኔታ መረዳት የአየር ንጽሕናን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ያትታል።

ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚሉት፤ በብዛት በኢትዮጵያ የሚደረገው ጥረት የፓርቲኩሌት ማተር ይዘትን መለካት ላይ ያተኮረ ነው።

በፓርቲኩሌት ማተር ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች በጤና ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ጋር የሚተሳሰሩ እንደሆኑ እና የኬሚካል ይዘታቸውን ማወቅ የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚደረጉ የፖሊሲ ጥረቶችን እንደሚደግፍ ያስረዳሉ።

የፓርቲኩሌት ማተር መነሻ ከሆኑ መካከል የግንባታ ሥፍራዎች፣ በአግባቡ ያልተሠሩ ብናኝ አመንጪ መንገዶች፣ የማገዶ እንጨት ጭስ እና የመኪና ጭስ ይጠቀሳሉ። የአቧራ ማዕበል እና ሰደድ እሳትም መነሻቸው ነው።

ቅንጣቶቹ በአፍንጫ በኩል ወደ ሳምባ እና ደም ሥር ሰርገው ይገባሉ። ለልብ ሕመም፣ ለስትሮክ፣ የሳምባ ካንሰር እና የተባባሰ አስም ያጋልጣሉ።

የአየር ብክለትን በዋናነት የሚያባብሱት በካይ ጭሶች ነው።

ለምሳሌ የማገዶ እንጨት ሲቃጠል ብላክ ካርበን አየር ላይ ይበትናል።

ቆሻሻ ሲቃጠል 'ዳዮክሲንስ' የተባለውን ካንሰር የሚያስከትል ኬሚካል ይረጫል።

ሌላው በካይ የመኪና ጭስ ሲሆን ብላክ ካርበን ወደ አየር ይለቃል።

የአየር ብክለት ከዕድሜያችን ላይ 1.8 ዓመት እየቀነሰ እንደሆነ ይታመናል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የአየር ብክለት በጤና እና በምጣኔ ሃብት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ መጥቷል።

የኢትዮጵያ የአየር ብክለት የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ጣሪያ አምስት እጥፍ የበለጠ ነው።

በአውሮፓውያኑ በ2019 በአየር ብክለት ምክንያት በደረሰው ሞት እና ሕመም ምክንያት በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ የደረሰው ጉዳት በ3.02 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት እንደሆነ ከዚህ ቀደም የወጣ ጥናት አሳይቷል። ይህም ከአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 1.16 በመቶ ይሸፍናል።

ከኢንዱስትሪ እና ከከተማ መስፋፋት ጋር በተያያዘ የአየር ብክለት እየጨመረ ይገኛል።

በመላው ዓለም በአየር ብክለት ምክንያት በዓመት ውስጥ ከሥራ የሚቀሩ ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ የተነሳ ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኪሳራ እንደሚደርስ ይገመታል።