ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ጉዟቸውን እንደ ሰረዘችባቸው የተናገሩት የታይዋን ፕሬዚዳንት ኢስዋቲኒን ጎበኙ
የታይዋን ፕሬዚዳንት ላይ ቺንግ-ቴ መንግሥታቸው ቻይና የአፍሪካ አገራትን በግዛታቸው ላይ አውሮፕላናቸው እንዳይበር ጫና አድርጓል ሲል ከወነጀለ በኋላ ኢስዋቲኒ ገቡ።
ኢስዋቲኒ ከታይዋን ጋር ዲሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ነች።
ፕሬዚዳንቱ ይህ ጉብኝታቸው "ለቀናት በጥንቃቄ በዲፕሎማሲ እና በብሔራዊ ደህንነት ቡድኖች ዝግጅት ከተደረገበት በኋላ" መካሄዱን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢስዋቲኒ ለመጓዝ ስለተጠቀሙት መንገድ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ቻይና ጉብኝቱን "በምስጢር የተካሄደ ማምለጥ የሚመስል" ስትል ገልጻዋለች። ቻይና ታይዋንን እንደ ግዛቷ አካል አድርጋ ስለምትመለከታት ከሌሎች አገራት ጋር ግንኙነት የመፍጠር መብት እንደሌላት ትገልጻለች።
ፕሬዚዳንቱ በኢስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ራስል ድላሚኒ አቀባበል ሲደረግላቸው እና በተደረደሩ ወታደሮች ፊት ሲያልፉ የሚያሳይ ምሰል ተጋርቷል።
የታይዋን የልዑካን ቡድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊን ቺያ-ሉንግ እና የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት አማካሪ አሌክስ ሁዋንግን የተካቱበት መሆኑን የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የፕሬዚዳንት ላይ ጉብኝት በሁለቱም መንግሥታት አስቀድሞ አልተገለጸም።
ጉዞው መጀመሪያ ላይ ታቅዶ የነበረው እአአ ከሚያዚያ 22 እስከ 26 ሲሆን ይህም የኢስዋቲኒ ንጉሥ ምስዋቲ ሳልሳዊ የ40ኛ ዓመትየንግሥና በዓልን ለማክበር ነበር።
ታይዋን ሲሼልስ፣ ሞሪሺየስ እና ማዳጋስካር የላይ አውሮፕላኖች በአየር ክልላቸው እንዳያቋርጡ በመከልከላቸው የተነሳ ጉብኝቱ መሰረዙን አስታውቃ ነበር።
የታይዋኑ ፕሬዚዳንት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ታይዋን በውጫዊ ጫናዎች ፈጽሞ አትደናቀፍም። ቁርጠኝነታችን እና ውሳኔያችን የተመሰረተው ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች ቢገጥሟትም ታይዋን ከቀሪው ዓለም ጋር መገናኘቷን እንደምትቀጥል ያሳያል።"
በሌላ ልጥፍ ደግሞ ኢስዋቲኒን "የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ታይዋን በዓለም አቀፍ መድረክ ላላት ስፍራ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ በጽናት በመቆሟ" አወድሰዋታል።
"ይህ ጉዞ በታይዋን እና በኢስዋቲኒ መካከል የበለጠ ጥልቅ ወዳጅነት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ይህም በኢኮኖሚ፣ በግብርና፣ በባህል እና በትምህርት ትስስር እንዲሁም የታይዋንን ዓለም አቀፍ ትብብር ለማሳደግ ይረዳል" ብለዋል።
የታይዋን የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እንደዘገበው ላይ ከኢስዋቲኒ ንጉሥ ምስዋቲ ሳልሳዊ ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን ከማድረግ በተጨማሪ በጉምሩክ ላይ ስምምነት ይፈራረማሉ።
ቀደም ሲል ስዋዚላንድ በመባል የምትታወቀው ኢስዋቲኒ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላቸው 12 ትናንሽ አገራት አንዷ ናት። እነዚህን ግንኙነቶች መጠበቅ የታይዋን መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ቻይና ለዓመታት አገሮች ከታይዋን ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ጫና ስታደርግ ቆይታለች።
ላይ ወደ ኢስዋቲኒ ከሄዱ በኋላ የቤይጂንግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ዓለም አቀፍ መሳቂያ" ሆነዋል ብሏል።
"የዴሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ባለሥልጣናት ከውጭ ኃይሎች ጋር ምንም ቢተባበሩ ወይም 'የሌሎችን ታማኝነት በምንም መልኩ ቢገዙ'፣ ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን ሊለውጥ የማይችል ከንቱ ጥረት ነው" ሲል ሚኒስቴሩ በመግለጫው ላይ የላይን ፓርቲን ጠቅሷል።
ቤይጂንግ በተጨማሪም ኢስዋቲኒ "የታሪክን አጠቃላይ አዝማሚያ በግልጽ እንድታይ" እና "ጥቂት የታይዋን ነፃነት" ተገንጣዮችን "ከማገዶው ውስጥ እንድታወጣ" አሳስባለች።
አርብ ዕለት ቻይና ከኢስዋቲኒ በስተቀር ለሁሉም የአፍሪካ አገራት ከታሪፍ ነጻ የሆነን ንግድ ፈቅዳለች።