ናይጄሪያ በኢቦላ ቫይረስ የተያዘች አንድ ግለሰብ ማግኘቷን አስታወቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ናይጀሪያ ከምሥራቅ አፍሪካ ኡጋንዳ ወደ ዋና ከተማዋ አቡጃ ከተጓዘች ሴት መንገደኛ የመጀመሪያውን የኢቦላ ቫይረስ ማግኘቷን አስታወቀች።

የጤና ሚኒስትር አሊ ፓት ቫይረሱ በላብራቶሪ ምርመራ መረጋገጡን ተናግረዋል።

ታካሚዋ በአቡጃ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ በለይቶ ማቆያ ክፍል የሚገኙ ሲሆን የሕክምና ክትትልም እየተደረገላቸው ነው።

የጤና ባለሥልጣናት የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ከታካሚዋ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች እየለዩ ሲሆን፤ እስካሁን 44 የቅርብ ሰዎች ተለይተዋል።

ናይጄሪያ በምሥራቅ አፍሪካ የተቀሰቀሰው አዲሱ የኢቦላ ዝርያ የተገኘባት የመጀመሪያዋ የምዕራብ አፍሪካ አገር ሆናለች።

ኢቦላ በቫይረስ የሚሠራጭ ልዩ እና ገዳይ በሽታ ነው። በሽታው ሲይዝ ማስመለስ እና ተቅማጥ የሚከሰት ሲሆን የሰውነት ክፍሎች እንዳይሰሩ ሊያደርግ ይችላል። ሁሉም ሳይሆኑ አንዳንድ ታማሚዎች የውስጥ እና የውጭ ደም መፍሰስ ይገጥማቸዋል።

በሽታው ከአንድ ሠው ወደ ሌላኛው እንደ ደም እና ትውከት ባሉ የሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት ይተላለፋል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰው ቫይረስ የ4,600 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፤ 9,500 ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን የአውሮፓ በሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል ገልጿል።

እምብዛም ባልተለመደው 'ቡንዲቡግዮ' በተባለ ዝርያ የተከሰተው አዲሱ የኢቦላ ወረርሽኝ ክትባት ወይንም ሕክምና የሌለው ነው።

ለዝርያው ክትባት ለማግኘት ምርምር እየተደረገ ነው።

ቫይረሱ መቀስቀሱ እንደታወጀ ወዲያ በኡጋንዳ መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል። ባለፈው ነሐሴ ኡጋንዳ የጨረሻውን ታካሚ ካሰነባተች በኋላ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን አውጃለች።

በሽታው በኬንያም የተሠራጨ ሰሆን ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች በፃይረሱ ተይዘዋል ተብለው ሪፖርት ተደርገዋል።

ሰኞ ዕለት በጤና ስጋት ምክንያት አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ኬንያ የሚያደርጉትን ጉዞ ዳግም እንዲያጤኑ የጉዞ ማሳሰቢያ አውጥታለች።

በሽታው ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ናየጄሪያ የቁጥጥር ስርዓቷን ከፍ አድርጋ ቆይታለች።

የአገሪቱ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል በሽታው ከተቀሰቀሰባቸው እና ሥርጭቱ ከተስተዋለባቸው አገራት የሚመጡ መንገደኞች የጤና ማሳወቂያ ቅፅ እንዲሞሉ ያስገድዳል። ከሌሎች አገራት የሚመጡ መንገደኞች ግን ቅፁን እንዲሞሉ አይገደዱም።

መንገደኞች ንቁ እንዲሆኑ እና የቫይረሱን ምልክት ካስተዋሉ ወዲያው የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙም ያሳስባል።

እ.አ.አ በ2014 ናይጄሪያ ስምንት ሰዎችን የገደለውን የኢቦላ ወረርሽኝ መቆጣጠር ችላለች።