በሱዳን ሀዘንተኞች እና ገበያ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ምንጮች ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የሱዳን ጦር ፈፅሟቸዋል በተባሉ የድሮን ጥቃቶች ወደ ለቅሶ ሲጓዙ የነበሩ ሀዘንተኞችን ጨምሮ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

እሑድ ምሽት በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት ሁለት ስፍራዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት 150 ሰዎች መገደላቸውን ምንጮች ጦርነቱን ለሚከታተለው 'ሱዳን ዋር ኦብሶርቫቶሪ' ተናግረዋል።

በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የይገባኛል ውዝግብ ባለበት አቢዬ ግዛትደግሞ ሠኞ ዕለት ገበያ ላይ በተፈፀመ ጥቃት 73 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢውን የመረጃ ሚኒስትር ተናግረዋል።

የሱዳን ጦር ገበያው ላይ ጥቃቱን መፈፀሙን ወታደራዊ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረው፤ ገበያው ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) የነዳጅ ማቅረቢያ ጣቢያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ጥቃቱ አቢዬ ግዛትን በጋራ በሚያስተዳድሩት በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን መካከል ውጥረት አስነስቷል።

ሁለቱ አገራት በነዳጅ የበለፀገው አካባቢ የይገባኛል ውዝግብ ያላቸው ሲሆን፤ ይህ ጉዳይ ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2011 ነፃ አገር ከሆነች ጀምሮ ያልተፈታ ነው።

ደቡብ ሱዳን ይፋዊ ተቃውሞ ለማሰማት የሱዳንን አምባሳደር ጠርታለች። ጦርነቱ ድንበር ተሻግሮ ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት አለ።

ከፊል የጦር መሣሪያ እቀባ ሱዳን ላይ ቢጣልም የውጭ አገራት ለጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድሮን የሚያስታጥቁ ሲሆን፤ መሣሪያው በጦርነቱ ተፈላጊነቱ እየጨመረ ነው።

የሱዳን ጦርነት በዓለም እጅግ የከፋ የተባለ የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፤ ከ14 ሚሊዮን የሚበልጡት ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ "በመላ አገሪቱ ሕፃናትን ጨምሮ ንፁሃንን እየገደሉ ባሉ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን እያስተጓጎሉ ባሉ እና በቀጠሉ የድሮን ጥቃቶች ተጨንቀናል" ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

በጦርነቱ ድሮን ጥቅም ላይ የሚውልበት መጠን እየጨመረ የመጣው፣ 20 ሚሊዮን ሰዎች ከፍተኛ ረሃብ ተደቅኖባቸዋል የሚለው ዜናበተሰማበት ወቅት መሆኑንም ተናግረዋል።

ታላቁ ኮርዶፋን አካባቢ ሦስት ግዛቶችን የያዘ ሲሆን፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተያዘውን ዳርፉርን በጦሩ የተያዘው ካርቱም የሚያገናኝ ወሳኝ መስመር ነው።

የድሮን ጥቃት ማዕበሉ እሑድ ምሽት እንደጀመረ እና ጥቃቶቹ በጦሩ ከተያዘው ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ካዱጊሊ ከተማ የተነሱ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ተናግረዋል።

ከሰሜን አቢዬ ግዛት የተነሳ እና 200 ሀዘንተኞችን የያዘ የጭነት ተሽከርካሪ ምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት አል-ዳባብ ከተማ ሲደርስ በድሮን መመታቱን ጦርነቱን የሚከታተለው ቡድን ተናግሯል።

ምንጮች ለቡድኑ እንደነገሩት ከሆነ 145 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ ሀዘንተኞች የነበሩበት ድንኳንም ተመትቶ ሌሎች አምስት ሰዎች ተገድለዋል።

በጥቃቱ ተጨማሪ 150 ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።

በዚያ ምሽት አል-ሙጅላድ በተባለ ከተማ ገበያ ላይ የድሮን ጥቃት ተፈፅሞ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ እና እንደቆሰሉ እስካሁን ማወቅ እንዳልተቻለ ቡድኑ ገልጿል።

የሱዳን ጦር ጥቃቶቹን ፈፅሟል የመባል ውንጀላውን በተመለከተ ምላሽ አልሰጠም። ሆኖም ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተቀላቅለዋል ተብሎ ቢታመንም እንኳ ንፁኃን ላይ ጥቃት አልፈፀምኩም ብሏል።

'ቢቢሲ ቨሪፋይ' የሳተላይት ምሥሎችን የተመለከተ ሲሆን በገበያው ላይ የተቃጠሉ ሕንፃዎችን መርምሯል። እንዲሁም በገበያው አቅራቢያ የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የጥቃቶችን ክብደት አሳይተዋል።

በጥቃቶቹ በተነሳ እሳት ምክንያት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሟቾቹን አስከሬን ማንሳት እንዳልቻሉ የአቢዬ የመረጃ ሚኒስትር ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በአቢዬ ከተማ በሚገኘው በአምታ ቤክ ሆስፒታል የቆሰሉ 20 ሰዎችን መቀበሉን አስታውቋል።