ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔዘርላንድስ በአሜሪካ እና ካናዳ የነበራትን የወርቅ ክምችት ወደ ለንደን አዘዋወረች
የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ባንክ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጣ ወርቅ ከሰሜን አሜሪካ ወደ ለንደን ማዘዋወሩን አስታወቀ። ለዚህም ምክንያቱ "እየተባባሰ የመጣ ጂኦፖለቲካዊ አለመረጋጋት" መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ባንኩ እንዳለው 86 ቶን የሚመዝነውን ወርቅ ከካናዳ እና ከአሜሪካ ወደ ለንደን የማዘዋወር ሒደት ወራት የወሰደ ውስብስብ ሥራ ነበር።
ወርቁ አሁን ላይ በእንግሊዝ ባንክ የገባ ሲሆን "ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት" በቀላሉ ለግብይት ማዋል እንደሚቻልም ተገልጿል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ኦላፍ ስሌጅፒን "ወርቁን ማዘዋወር ዝግጁነታችንን እና ጽናታችንን ለማጠናከር አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔውን ያሳለፈው አሜሪካ እና ካናዳ አንዳቸው በሌላቸው ላይ ታሪፍ እየጣሉ ባለበት ወቅት ነው።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማስተካከል የተደረጉ ውይይቶች ውጤታማ አልሆኑም።
ባንኩ እንዳለው ወርቁ የተዘዋወር ከየካቲት እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ውስጥ ነው። 27 ቶን ወርቅ ከኒው ዮርክ እና ከኦታዋ ወደ ኔዘርላንድስ፣ ዚስት ተዘዋውሯል።
ተመሳሳይ መጠን እና ጥራት ያለው ወርቅ ወደ ለንደን ተወስዷል። ወርቁን ወደ ለንደን ለማዘዋወር ማቅለጥ እንዳላስፈለገም ተገልጿል።
በትክክል ምን ያህል መጠን ያለው ወርቅ አትላንቲክን ውቅያኖስን እንዳቋረጠ ግልጽ አይደለም።
የተቀረው ወርቅ የተዘዋወረው በኒው ዮርክ ከተሸጠ በኋላ በለንደን ገበያ በድጋሚ ተሸምቶ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
ባንኩ ባወጣው መግለጫ "ከመሸጥ እና ከመግዛት በተጨማሪ ወርቁን በቀጥታ ማዘዋወርም ተችሏል። ሒደቱ ውስብስብ ነበር" ብሏል።
ባንኩ ወርቁን ለማዘዋወር ምክንያት የሆነው "ጂኦፖለቲካዊ አለመረጋጋት" መሆኑን ከመጥቀስ ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
አሜሪካ በኢራን ጦርነት ሳቢያ ምጣኔ ሃብቷ ላይ ከተፈጠረው ጫና ባሻገር ዓለም አቀፍ ንግድም በጦርነቱ ምክንያት ተቃውሷል።
በሌላ በኩል ካናዳ ከአሜሪካ ከፍተኛ ታሪፍ ተጥሎባታል። በብረት፣ አልሙኒየም፣ እንጨት እና ተሽከርካሪ ዘርፎች ላይ የተጣለው ተጨማሪ 50 በመቶ ታሪፍ በዚህ ነሐሴ ወር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ባንክ "የእንግሊዝ ባንክ በቀላሉ የወርቅ ግብይት የሚደረግበት ባንክ በመሆን በመላው ዓለም ይታወቃል" ብሏል።
ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት የኔዘርላንድስ ወርቅ በአሜሪካ እና ካናዳ ከሚቆይ ይልቅ በለንደን ቢቀመጥ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ገልጿል።
ባንኩ 31.3 በመቶ የወርቅ ክምችቱ በኒው ዮርክ፣ 19.7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በኦታዋ ይገኝ ነበር። አሁን በአሜሪካ እና ካናዳ ያለው ወርቅ ወደ 18.5 በመቶ ወርዷል።
በአውሮፓውያኑ 2025 የኔዘርላንድስ የወርቅ ክምችት 612.4 ቶን ሲሆን፣ የገበያ ዋጋው 72.2 ቢሊዮን ዮሮ እንደሚገመት የብሔራዊ ባንኩ መረጃ ያሳያል።
ባንኩ ወርቁን በማጓጓዙ በለንደን ያለው የወርቅ ድርሻ ከ18.1 በመቶ ወደ 32.1 በመቶ ከፍ ብሏል። በኔዘርላንድስ ያለው የመጠባበቂያ ክምችት ደግሞ 30.8 በመቶ ደርሷል።