ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሞሮኮ ወደ ስፔን ከተሻገሩ ስደተኞች ጋር በተያያዘ ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች ተካሄዱ
በሰሜን አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ወደምትገኘው የስፔን ግዛት ሴዩታ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች መግባታቸውን በመቃወም ሰልፎች ተካሄዱ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ የስፔን አካባቢዎች ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ መንግሥት የስደተኞችን ጉዳይ የያዘበትን መንገድ ኮንነዋል።
የስፔን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፤ የሴዩታ ነዋሪዎችን ችላ ብለዋል በሚል ወቅሰዋል።
መንግሥት በበኩሉ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የተፈጠረውን ቀውስ እየተጠቀሙበት ነው ሲል ከስሷል።
ፖሊስ ትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ የሞሮኮ የፀጥታ ኃይሎች በከፍተኛ ቁጥር የሚጓዙ ስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ "ጨለምተኛነት አሳይቷል" ብሏል።
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩላቸው ለተፈጠረው ቀውስ ሞሮኮን ተጠያቂ አይደለችም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወር ሐሰተኛ መረጃ ችግሩን አባብሰዋል።
ሞሮኮ ስደተኞች ወደ ስፔን እንዲሻገሩ በማድረግ ውስጥ እጇ እንደሌለበት አስታውቃለች።
ያለፈው ሐምሌ ወር ላይ ቢያንስ 72,000 ስደተኞች ከሞሮኮ ወደ ሲዩታ ተሻግረዋል።
አብዛኞቹ ስደተኞች ቢመለሱም ወደ 5,000 የሚደርሱት በመጠለያዎች እና በተለያዩ የከተማዋ ጎዳናዎች ይገኛሉ።
በዚህም ምክንያት ራስ ገዝ በሆነችው የሰሜን አፍሪካ ከተማ ተቃውሞዎች ቀጥለዋል።
በሴዩታ በየቀኑ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቃውሞ ሲካሄድ ነበር። ሰልፈኞቹ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አልያም በስፔን የተለያዩ ከተሞች እንዲዛወሩ ጠይቀዋል።
ትናንት የስፔን ከተሞች ምክር ቤቶች የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱ ጠርተዋል።
ወግ አጥባቂው ፓርቲዶ ፖፑላር እና ቀኝ ዘመሙ ቮክስ ፓርቲ በምክር ቤቶቹ ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸው።
ሰልፈኞቹ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሥልጣን እንዲለቅቁ ጠይቀዋል።
የፓርቲዶ ፖፑላር መሪ አልበርቶ ኑኔዝ ፌጆ በማድሪድ ከተማ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ተገኝተዋል። በዚህ ሰልፍ ከ50,000 በላይ ሰዎች መታደማቸውን የመንግሥት አሐዝ ያሳያል።
መሪው "የስፔን ከተማ ተጥለቅልቃለች ወይም ተይዛለች። ይሄ የሆነው የስፔን መንግሥት እያወቀ ነው" ብለዋል።
የቮክስ ፓርቲ መሪ ሳንቲያጎ አብስካል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የሞሮኮ መንግሥት አገልጋይ ነው" ሲሉ አውግዘዋል።
በሴዩታ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ "ሴዩታ አትሸጥም" እና "ሴዩታን እንታደግ" የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል።
የ45 ዓመቱ መምህር ዴቪድ ኸርናንዴዝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል "መንግሥት በቂ ምላሽ አልሰጠም፤ ዘግይቷልም" ብሏል።
"ሁለተኛ ዜጋ መሆን የለብንም፤ ድንበራችን መጣስ የለበትም" ሲሉም አክለዋል።
በስፔን መገናኛ ብዙኃን የወጡ ዘገባዎች እንዲሁም የአገሪቱ ብሔራዊ የስደተኞች እና ድንበር ፖሊስ ለብሔራዊው ፍርድ ቤት በሰጠው ሪፖርት ላይ የሞሮኮ የፀጥታ ኃይሎች ተጠያቂ ተደርገዋል።
እነዚህን ሪፖርቶች ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
የሞሮኮ ፖሊስ ከተለመደው ጊዜ ባነሰ ሁኔታ የድንበር ጠባቂዎችን ቁጥር "ቀንሷል" ሲል የስፔን ፖሊስ ሪፖርት ይወነጅላል።
ከስደተኞቹ ዝውውር ጀርባ ሞሮኮ አለችበት የሚል ድምዳሜ ግን አላስቀመጠም።
ሞሮኮ ለረዥም ጊዜ ሴዩታ እና ሜሊላ ከተሞች ላይ የግዛት ጥያቄ ስታነሳ ቆይታለች። በስፔን እና ሞሮኮ ግንኙነት ቁልፍ ከሆኑ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች አንዱም ነው።
ነሐሴ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ የወጡ ልጥፎች በሞሮኮ እና ሴዩታ መካከል ያለው ድንበር ስሱ ስለሆነ በቀላሉ ሊታለፍ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ድንበሩን ተሻግረው ለማለፍ የሞከሩ ቢያንስ 100 ሰዎች ሞተዋል።