ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መዳረሻዋን ሩሲያ ያደረገች መርከብ በፊንላንድ ባሕረ ሰላጤ የድሮን ጥቃት ተፈጸመባት
ወደ ሩሲያዋ ካሊኒንግራድ ግዛት ስታቀነ የነበረች አንዲት የሩሲያ የጭነት መርከብ በምሥራቅ የፊንላንድ ባሕረ ሰላጤ በድሮን ጥቃት መመታቷን የሩሲያ እና የፊንላንድ ባለሥልጣናት ገለጹ።
ስፓርታ ሁለት የተባለችው መርከብ ቅዳሜ ጠዋት የደረሰባትን ጥቃት ተከትሎ ወደ ፊንላንድ ውሃ ከማቅናቷ ቀደም ብሎ በእሳት ተያይዛለች። የፊንላንድ የመከላከያ ኃይል ዩክሬን ከጥቃቱ ጀርባ ልትሆን እንደምትችል ተናግረዋል። ኪዬቭ በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
"ጦርነት ወደ አካባቢያችን እየገባ ነው" ሲሉ የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔተሪ ኦርፖ ተናግረዋል። "ዩክሬን ወራሪውን የመዋጋት መብት አላት" ሲሉም አክለዋል።
የካሊኒንግራድ ገዢ አሌክሲ ቤስፕሮዝቫኒች በመጀመሪያ መረጃ መረጃ ላይ በመመሥረት ሁለት ድሮኖች ጥቅም ላይ እንደዋሉ እና ጥቃቱ ለግዛታቸው አቅርቦቶች "ምንም ስጋት" እንደሌለው ተናግረዋል።
ስፓርታ ሁለት በ2022 በአሜሪካ እንዲሁም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በዩክሬን ማዕቀብ ተጥሎባታል። ዩክሬን እና አሜሪካ እንደሚሉት በሩሲያ ኩባንያ ነው የምትተዳደረው።
ኩባንያው በድረገጹ ላይ እንደገለጸው በአውሮፓውያኑ 2011 በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር መዋቅር ውስጥ የተቋቋመ ሲሆን ከ2015 ጀምሮ በወታደራዊ የግንባታ ማዕቀፍ ውስጥ እየሠራ ቆይቷል።
የፊንላንድ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ቅዳሜ ዕለት 2፡50 ገደማ ስለ ጥቃቱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠ እና የጭነት መርከቧ በፊንላንድ ባሕረ ሰላጤ ከሱርሳሪ ደሴት በስተ ምዕራብ 50 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኝ ነበር ብሏል።
ይህም በአካባቢው "ጊዜያዊ የአቪዬሽን እና የባሕር ገደቦች" እንዲጣሉ ምክንያት ሆኗል ሲሉ የፊንላንድ የድንበር ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የፊንላንድ የመከላከያ ሚኒስቴር አንድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት ከክስተቱ በኋላ አንድ የሩሲያ ሄሊኮፕተር የአገሪቱን የአየር ክልል ጥሷል ተብሎ ተጠርጥሯል። ይህም "ከነፍስ አድን ወይም የመከታተያ ሥራዎች" ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የሩሲያ የነፍስ አድን መርከብ ወደ መርከቧ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም መልቀቅ እንደማያስፈልጋቸው በሠራተኞቹ ተነግሯቸዋል ሲሉ የካሊኒንግራድ ገዢ በቴሌግራም ላይ ጽፈዋል።
"መርከበኞቹ በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊውን ሥራ እያከናወኑ ሲሆን ጉዟቸውንም ለመቀጠል አቅደዋል" ብለዋል።
የፊንላንድ የድንበር ጠባቂ መርከበኞቹ ወደ ሩሲያ እየሄደ ወዳለ ሌላ የሩሲያ መርከብ እንደተዘዋወሩ አስታውቋል። የሩሲያ የነፍስ አድን መርከብ በተጎዳው መርከብ ቦታ ላይ ቆይቷል።
ምንም ዓይነት የአካባቢ ጉዳት እንዳልተገኘ እና በባሕር ትራንስፖርት ወይም በሰዎች ላይ ምንም ዓይነት የአደጋ ስጋት እንዳልተከሰተ አክሏል።
ካሊኒንግራድ በፖላንድ እና በሊትዌኒያ መካከል የሚገኝ የሩሲያ ግዛት ነው።
የመከላከያ ሚኒስትር አንቲ ሃክኬነን እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር እንደሚተባበሩ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አክለውም ኔቶም ስለጉዳዩ መረጃም ተላልፎለታል ብለዋል።