ትራምፕ "ጓደኛዬ" ሲሉ የጠሯቸውን ፑቲንን፤ ዜሌንስኪ "ገዳይ" ሲሉ ፈረጁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያውን ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንን "ገዳይ" ሲሉ ፈረጁ።

ዘሌንስኪ ይህን ያሉት በዚህ ሳምንት በቻይና በተካሄደው ጉባኤ ወቅት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ፑቲንን "ጓደኛዬ" ብለው መጥራታቸውን በመቃወም በሰጡት ምላሽ ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ለሲኤንኤን ሲናገሩ፣ ፑቲንን "እንዴትም ብሎ መጥራት" የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጉዳይ እንደሆነ ተናግረው፤ ነገር ግን "ለእኛ ጠላት ነው. . . ለእኛ ገዳይ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ እና ፑቲን ጋር ሐሙስ ዕለት ባካሄዱት እና ታሪካዊ የተባለ የሦስትዮሽ ስብሰባ ፑቲንን "ጓደኛዬ" ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን ለብዙ ዓመታት ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸውም አስታውሰዋል።

በማግሥቱ አርብ ዕለትም ሩሲያ የኪየቭ ድልድዮችን ዒላማ አድርጋ በፈፀመችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል። ጥቃቱ የተፈፀመው ዩክሬን በክሪሚያ ድልድይ ላይ በፈፀመችው ጥቃት ከባድ ጉዳት ካደረሰች ከቀናት በኋላ ነው።

ዜሌንስኪ የአርብ ዕለቱን ጥቃት በዚህ ዓመት ከተፈፀሙ ጥቃቶች "ከባዱ" ሲሉ ገልጸውታል።

110 ሚሳዔሎችን እና ከ400 በላይ ድሮኖችን በመጠቀም አገራቸው ላይ በተፈጸመው ከባድ ጥቃት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሞት እና ጉዳት እንደደረሰ አስረድተዋል።

ጥቃቱ በዩክሬን ላይ ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላም ትራምፕ "ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም እንደሚፈልጉ" በዋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

"እነርሱ [ዜሌንስኪ እና ፑቲን] ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋሉ፤ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት መኖሩ በጣም ጥሩ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ የሩሲያውን ፕሬዚደንት በተደጋጋሚ "ጓደኛዬ" ሲሉ ቢጠሩም ፤ ፑቲን ለአሜሪካ ወዳጅ መሆን አለመሆናቸውን በተመለከተ ግን "መናገር አልችልም" ብለዋል።

ዜሌንስኪ በበኩላቸው የትራምፕ አቋም ምንም ይሁን ምን ፑቲንን "ገዳይ" አድርገው እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

" እኔ እንደማስበው ለአብዛኛው የዓለም ሕዝብ [ፑቲን] ገዳይ ነው፤ ምክንያቱም እየገደለ ነው። በነገራችሁ ላይ ቀን ከሌት እየገደለ ነው" ብለዋል።

ዘሌንስኪ ጨምረውም ፑቲንን እንደ ጓደኛ መግለጽ ጫና እንዳይሰማቸው የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህ የቃላት ጦርነት የተፈጠረው ፖላንድ አርብ ዕለት የአየር ክልሏን ጥሰው ከገቡ ሦስት ነገሮች መካከል የሩሲያ ክሩዝ ሚሳዔል እንደሚገኝበት ባስታወቀችበት ወቅት ነው።

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ እንዳሉት ምዕራባውያን በአካባቢው ወታደራዊ ልምምዶችን ሲካሄዱ ይህ ድንገተኛ ነገር አይመስልም።

በዚህ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ዋርሶ ክስተቱን ከሞስኮ የመጣ "ትንኮሳ" ሲል ገልጾታል።