የትራምፕ አስተዳደር "አላግባብ ዒላማ አድርገናል" ለሚሉ የመደበውን 1.8 ቢሊዮን ዶላር የካሳ ገንዘብ መሰረዙን አስታወቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የትራምፕ አስተዳደር መንግሥት ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ዒላማ አድርጎናል ወይንም ምርመራ አድርጎብናል ለሚሉ ግለሰቦች ካሳ ለመፈል አዘጋጅቶት የነበረውን የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ማስቀረቱ ተገለጸ።

ተጠባባቂ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ቶድ ብላንቼ "በአጭሩ የካሳ ፈንዱን ትተነዋል" ሲሉ ለሕግ አውጪዎች ተናግረዋል።

"አንቲ ዌፐናይዜሽን" በሚል ስም ገንዘብ የተመደበው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት የታክስ ሰነዳቸውን አሹልኮ ማውጣቱን በማስመልከት የመሠረቱትን ክስ ተከትሎ ነበር።

ዕቅዱ ከዲሞክራቶች እና ከተወሰኑ ሪፐብሊካኖች ከባድ ትችት አስከትሏል።

ፖለቲከኞቹ በጥር 6/2021 በአሜሪካ ምክር ቤት ሕንጻ አመጽ ላይ ተሳትፈው ለተከሰሱ እና ለተፈረደባቸው ካሳ ለመክፈል ማቀዱን አበክረው ተችተዋል።

ባለፈው ሳምንት ሊዮኒ ብሪንክማ የተባሉ ዳኛ የካሳ ፈንዱን ለጊዜው አግደዋል።

ብሪንክማ የፍትሕ ቢሮ ፈንዱን ለማንቀሳቀስም ሆነ ለሰኔ 12 ከተቀጠረው ችሎት በፊት ይገባናል ብለው ማመልከቻቸውን ላቀረቡ መክፈል እንዳይጀምር ዕግድ ጥለዋል።

ብላንቺ የኮንግረስ አባላት ፊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከፍተኛ ትችት ያስተናገዱ ቢሆንም አስቀድሞ ግን የፍትሕ ቢሮው ለፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተገዢ ብሆንም "በጥብቅ እቃወማለሁ" ብሎ ነበር።

ብላንቼ ለካሳ የተመደበውን ገንብ እንደማይጠቀሙ በቃል ለኮንግረሱ ያረጋገጡ ሲሆን፣ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ይፋ የሆነ መግለጫ ላይሰጥ እንደሚቸል ግን ተናግረዋል።

ዲሞክራቷ የኮንግረስ አባል ግሬስ ሜንግ ይህንን አቋማቸውን በጽሑፍ ቢያሰፍሩ የበለጠ መተማማንን እንደሚያሰፍን ሲገልጹ ብላንቼ ግን "ምንም ነገር በጽሑፍ ለማስፈር ቃል አልገባም፤ የምናገረው የምንሠራውን ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ሰኞ ዕለት የካሳ ፈንዱን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ በኤክስ ገጹ ላይ ፈንዱ ያስፈለገው " ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ በተወሰኑ ሰዎች ለይ የተፈጸሙ ከባድ ጥሰቶችን፣ ጉዳቶችን እና ጥላቻዎችን ለመካስ ነው" ብሎ ነበር።

ፈንዱ "ማንኛውም ዲሞክራትም ሆነ ሪፐብሊካን፣ ወግ አጥባቂ፣ ገለልተኛ ወይም ሌላ ጥቃት ለደረሰበት፣ ዒላማ ለተደረገ ወይም ለተከሰሰ" የሚውል መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።

ዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሲጠየቅ ጥያቄውን ወደ ፍትሕ መሥሪያ ቤቱ መርቶታል።

ፈንዱ "በሕግ ሰበብ ጉዳት ለደረሰባቸው" የሚሰጥ ካሳ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ክፍያው የሚገባቸው ቦርድ ፊት ቀርቦ እንደሚወሰን ተገልጿል።

ባለፈው ሳምነት የችሎቱን ውሳኔ በሚመለከት ያላቸውን አስተያየት የተጠየቁት የፍትሕ ቢሮው ቃል አቀባይ የገንዘቡ ሕጋዊነት ላይ "በጣም እተማመናለሁ" ብለው ነበር።

በርካታ በጥር 6/2021 በካፖቶል ሂል ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተከሰሱ የትራምፕ ደጋፊዎች እንዲሁም የቅርብ አጋሮች ካሳው ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።

በርካታ ሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች እና ዲሞክራቶች የካሳ ገንዘቡ በዐቃቤ ሕጉ ይፋ ከሆነ ጀምሮ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።