ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ከተነገረው በላይ በአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሷን ቢቢሲ አረጋገጠ
ኢራን ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ 20 የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ማውደሟን እና የደረሰው ጉዳት በይፋ ከታወቀው ከፍተኛ መሆኑን የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ የሆነው ቢቢሲ ቬሪፋይ የተነተናቸው የሳተላይት ምሥሎች እና ቪዲዮዎች አመለከቱ።
ኢራን ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ስምንት አገራት ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላትን ዒላማ አድርጋ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ዘመናዊ የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን፣ በአየር ላይ ነዳጅ የሚሞሉ አውሮፕላኖችን እና ራዳሮችን በመምታት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ውድመት አድርሳለች።
ኢራን የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃቶችን ለመበቀል ባለፉት ሦስት ወራት በኢራቅ እና በሊባኖስ ያሉትን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና የጋራ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ አድርጋለች።
የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታገን) ኤፒክ ፊዩሪ ባለው ዘመቻ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ በኢራን ውስጥ ከ13 ሺህ በላይ ዒላማዎች መመታታቸውን ገልጿል።
አዲሱ የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ፣ ማክሰኞ ዕለት ባስተላለፉት መግለጫ፣ መካከለኛው ምሥራቅ ለአሜሪካ ጦር ሰፈሮች "አስተማማኝ ቦታ" እንዳልሆነ በመጥቀስ የአገራቸው ሠራዊት የአሜሪካን ሠራዊትን በማጥቃት ረገድ ስኬታማ እንደነበር አጉልተው ተናግረዋል።
አሜሪካ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የኢራን ጦር ኃይል ከመደምሰስ አፋፍ ላይ ደርሷል በማለት ደጋግሞ ቢናገርም፣ ተንታኞች እንደሚሉት ግን በአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የታየው ጉዳት የቴህራን መልሶ ማጥቃቶች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት ካመኑት በላይ ዒላማውን የጠበቁ እና መጠነ ሰፊ ናቸው።
አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን "ለወታደራዊ ዘመቻዎች ደኅንነት" ሲባል በቢቢሲ ቬሪፋይ ግኝቶች ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አሜሪካ ዋነኛ የሳተላይት ምሥሎች አቅራቢ የሆነው 'ፕላኔት' የተባለው ተቋም የኢራን እና በአብዛኛው የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢዎች የሚያሳዩ ምሥሎችን "ላልተወሰነ ጊዜ" ላለማቅረብ ገደብ እንዲያስቀምጥ በመጠየቅ የግጭቱን የሳተላይት ትንተና ለመገደብ ጥረት አድርጋለች።
ኩባንያውም ምሥሎቹ "በተቀናቃኝ ኃይሎች የአሜሪካ አጋሮችን እና የኔቶ አባላትን እንዲሁም ሲቪሎችን ዒላማ ለማድረግ" ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ እንደሚፈልግ በመግለጽ የዕገዳውን ትክክለኝነት ደግፎታል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ በኢራን ጥቃቶች ምክንያት በአሜሪካ ተቋማት ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ለመተንተን ከሌሎች ዓለም አቀፍ የሳተላይት ምሥል አቅራቢዎች የተገኙ ምሥሎችን እንዲሁም ከፕላኔት ደግሞ ቆየት ያሉ ማነጻጸሪያ ምሥሎችን ተጠቅሟል።
በኢራን ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ወታደራዊ ተቋማት የሚገኙት በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በኳታር፣ በኩዌት፣ በኢራቅ፣ በዮርዳኖስ፣ በባህሬን እና በኦማን ነው። የጥቃት ዒላማ የሆኑት ማዕከላት ትክክለኛው አሃዝ ከፍተኛ ሊሆን የሚችል ቢሆንም፣ አንዳንድ ተንታኞች ቁጥሩን አስከ 28 ያደርሱታል።
ጉዳት ከደረሰባቸው ውድ ወታደራዊ መሳሪያዎች መካከል በአረብ ኤምሬትስ ውስጥ በሚገኙት አል ሩዋይስ እና አል ሳድር አየር ኃይል ሰፈሮች ውስጥ እንዲሁም ዮርዳኖስ በሚገኘው ሙዋፋቅ ሳልቲ አየር ኃይል ሰፈር ውስጥ የነበሩ እጅግ ዘመናዊ የፀረ ባለስቲክ ሚሳዔል መከላከያ መሳሪያዎች ይገኙበታል።
አሜሪካ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የጦር ሰፈሮች ውስጥ የተተከሉ ስምንት ታድ የሚባሉ የሚሳዔል መከላከያዎች ሲኖሯት እያንዳንዱን ለማምረት 1 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል።
እነዚህ የፀረ ሚሳዔል መከላከያዎች እያንዳንዳቸው 100 የሚሆኑ ወታደሮች ባለው ቡድን የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ በአንድ ዙር የሚተኩሷቸው ፀረ ሚሳዔሎች 12.7 ሚሊዮን ዶላር ያስወጣሉ።
የአየርላንድ ጦር ኃይሎች የቀድሞ አዛዥ ምክትል አድሚራል ማርክ ሜሌት ለቢቢሲ ቬሪፍይ እንደተናገሩት የሚሳዔል ጥቃት መከላከያዎቹ "እጅግ ውስብስብ" የሆነ ቀጣናዊ የመከላከያ ሥርዓት አካል በመሆናቸው "በፍጥነት ወይም በቀላሉ ሊተኩ የማይችሉ" ናቸው ብለዋል።
የኢራን ጥቃቶች በሳዑዲ አረቢያ በሚገኘው የልዑል ሱልጣን አየር ኃይል ሰፈር ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ አየር ላይ ነዳጅ በሚሞሉ እና የቅኝት አውሮፕላኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የሳተላይት ምሥሎችን የተነተኑ ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
ውድመት የደረሰበት አንደኛው አውሮፕላን ኢ-3 ሴንትሪ የተባለ የቅኝት አውሮፕላን መሆኑን በተንታኞች ተለይቷል። ይህንን ወታደራዊ አውሮፕላን ለመተካት እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ እንደሚችል የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የኢራን ጥቃት በሌሎች ቦታዎችም የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ አድርጓል። በኩዌት ውስጥ የሚገኙት የአሊ አል ሳሌም የአየር ኃይል ሰፈርን እና የካምፕ አሪፍጃን ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
በጦርነቱ ወቅት በተደጋጋሚ ጥቃት በተፈጸመበት በአንደኛው ጦር ሰፈር ውስጥ የሚገኙ የነዳጅ ማከማቻዎች፣ የአውሮፕላን መጠለያዎች እና የወታደሮች መኖሪያዎች መውደማቸውን ተንታኞች ከሳተላይት ምሥሎች ተመልክተዋል።
በተጨማሪም ካምፕ አሪፍጃን በተባለው ወታደራዊ ሰፈር ውስጥ በሚገኝ የሳተላይት ግንኙነት መሳሪያ ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን የመከላከያ ደኅንነት መረጃ ኩባንያ የሆነው የንስ ያገኘው መረጃ አሳይቷል።
በአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከሳምንታት በፊት በፔንታገን ያወጣው ግምት ለኢራን ጦርነት አጠቃላይ 29 ቢሊዮን ዶላር መውጣቱን አስቀምጧል።
ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ወጪ በጦርነቱ ለወደሙ መሳሪያዎች "ጥገና ወይም መተኪያ" እንደሚውል ይጠበቃል። ነገር ግን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ተቃዋሚ የሆኑት ዲሞክራቶች ይህ አሃዝ ምናልባት ዝቅተኛ ግምት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
ሪፖርቱ ጨምሮም ጦርነቱ ከጀመረበት ከየካቲት ወር አንስቶ ኤፍ-15 እና ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶችን፣ 24 ኤምኪው-9 ሪፐር ድሮኖችን እንዲሁም ኤ-10 አጥቂ አውሮፕላን ጨምሮ ቢያንስ 42 አውሮፕላኖች ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል ሲል አረጋግጧል።
የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ከሚጠቀምባቸው ውድ የጦር መሳሪያዎች ጋር ሲነጻጸር፣ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ በፈጸመችው ጥቃት ርካሽ እና በቀላሉ የሚተኩ ድሮኖችን እንደምትጠቀም ተዘግቧል ።
ባለሙያዎች ለቢቢሲ ቬሪፋይ እንደተናገሩት በጦርነቱ ወቅት የኢራን የጥቃት ስልቶች ተሻሽለዋል፣ ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ከተሞችን እና የጦር ሰፈሮችን ዒላማ ካደረጉት ሰፊ የጅምላ የሚሳዔል ውርጅብኞች ዒላማቸውን ወደለዩ ይበልጥ ትክክለኛ እና ቀጥተኛ ጥቃቶች ተሸጋግሯል።
"የኢራን የመጀመሪያዎቹ የሚሳዔል ጥቃቶች በከፍተኛ ቁጥር ላይ አተኩረው የአየር እና የሚሳዔል መከላከያዎችን በከፍተኛ መጠን በመሸፈን ከአቅማቸው በላይ እንዲሆኑ ለማድረግ የተነደፉ የጅምላ ሚሳዔል ማዕበሎች ናቸው" ሲሉ በአሜሪካው ስቲምሰን ሴንትራል የባለሙያዎች ቡድን ውስጥ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ኬሊ ግሪዬኮ ተናግረዋል።
"ሆኖም ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ኢራን ወደ ትናንሽ፣ ይበልጥ ዒላማቸውን ወደለዩ ጥቃቶች ተሸጋግራለች፣ የቀሩትን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ለተወሰኑ ከፍተኛ ጉዳት ለሚያደርሱ ዒላማዎች በማቆየት ትኩረቷን ዒላማቸውን ለጥቂት የሳቱ ጥቃቶቿ እንኳን ከፍተኛ ጉዳት በሚያደርሱ ዒላማዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው።"
አንድ ተንታኝ ለቢቢሲ ቬሪፍይ እንደተናገሩት የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የኢራን የጦር ስልት እየተሻሻለ በሚሄድበት ጊዜ አውሮፕላኖቹን ከኢራን የድሮን እና የሚሳዔ ጥቃት ክልል ለማስወጣት ባለመቻሉ "በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ቸልተኝነትን በመፈጸሙ ጥፋት ፈጽሟል" ብለዋል።
የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል ሰፈርን በተመለከተ አውሮፕላኑ ከመውደሙ በፊት የጦር ሰፈሩ ቀደም ሲል ጥቃት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ "የቀጣናው መሬት እና አገራት ከዚህ በኋላ ለአሜሪካ ጦር ሰፈሮች መጠለያ ሆነው አያገለግሉም" በማለት "አሜሪካ በቀጣናው ችግር ለመፍጠር እና ወታደራዊ ሰፈር ለመክፈት የሚሆናት አስተማማኝ ቦታ አታገኝም፤ አሜሪካ ከዕለት ወደ ዕለት ቀድሞ ከነበራት ቦታ ላይ እየተንሸራተተች ነው" ብለዋል።
ይህ የጠቅላይ መሪው አስተያየት የተሰማው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ሲያደርጉት የነበረው ንግግር መልሶ ውጥረት ውስጥ ከመግባቱ ከቀናት በፊት ነው።
አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን አዲስ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ሐሙስ ዕለት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በቀጣናው ያለ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈርን ዒላማ ማድረጉን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ አስታውቆ ነበር።
ዶ/ር ግሬይኮ የአሜሪካ እና የኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ እና ውጊያው እንደገና ከተጀመረ፣ በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በባሕረ ሰላጤው ያሉ ተቋማት ለአደጋ የተጋለጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
"አሁን እየተካሄደ ያለው ግጭት የአሜሪካን እና የአጋሮቿን የአየር መከላከያ መሳሪያዎች ክምችትን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶባቸዋል" ብለዋል።
"የጦር መሳሪያዎቹን ለመተካት የሚያስችል ፈጣን አማራጭ የለም፣ ስለዚህ አዲስ ዙር የኢራን ጥቃት የሚጀመር ከሆነ ለመከላከያ የሚውለው መሳሪያ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት ከነበረው ጥቂቱ ብቻ ነው የሚሆነው።"