ካንሰር ተመልሶ እንዳይመጣ ማድረግ የሚችል አዲስ ክትባት ሙከራ ላይ መሆኑ ተገለጸ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከመድኃኒት ጋር የተቀላቀለ ክትባት የቆዳ ካንሰር ሕሙማን ላይ በድጋሚ እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚችል በሙከራ ተረጋገጠ።

ክትባቱ፣ የሰዎች በሽታን የመከላከል አቅም በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኙ የተጎዱ ሕዋሳትን መዋጋት እንዲችል የሚያደርግ ነው። ከመድኃኒት ጋር ተደባልቆ በተደረገ ሙከራ የተገኘው ይህ ውጤት በካንሰር ሕክምና ትልቅ ስኬት ነው ተብሏል።

ክትባቱ የቆዳ ካንሰር ተመልሶ በሕሙማን ላይ እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

መርክ እና ሞደርና የተባሉት መድኃኒት አምራቾች የሠሩት ክትባት ሜላኖሚያ በተባለው የቆዳ ካንሰር ለተያዙ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ሕሙማኑ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ክትባቱን እንዲወስዱ ተደርጓል።

ክትባቱ ሕሙማኑ ከካንሰር ነጻ ሆነው የሚቆዩበትን ጊዜ እንደሚያራዝም የሙከራው የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ያሳያል። ሕሙማኑ ለምን ያህል ጊዜ ከካንሰር ነጻ ሆነው እንደቆዩ ግን ግልጽ አይደለም።

የካንሰር ተመራማሪዎች ክትባቱ ትልቅ ግኝት ቢሆንም ሙሉ የጥናቱ ውጤት ይፋ እስከሚደረግ እና በገለልተኛ ባለሙያዎች እስከሚገመገም ድረስ በጥንቃቄ መታየት አለበት ብለዋል።

ክትባቱ ላይ የሚደረግ ሙከራ ቢጠናቀቅም ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በመድኃኒት ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል።

ኢንቲስሜራን የተባለው ክትባት ሙከራ የተደረገበት ኬይትሩዳ ከተባለ መድኃኒት ጋር ተደባልቆ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኬይትሩዳ መድኃኒትን ለብቻው ከመውሰድ በበለጠ ከክትባት ጋር አዋህዶ መጠቀም ሕሙማን ከካንሰር ነጻ ሆነው የሚቆዩበትን ጊዜ እንደሚያራዝመው ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም ካንሰሩ ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሚስፋፋበትን መጠን ይቀንሳል።

በክትባቱ ሦስተኛ ዙር ሙከራ ላይ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝ የቆዳ ካንሰር የተጠቁ ከ1,000 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በአንድ ቦታ ብቻ ተወስኖ የሚገኝ ካንሰር ያለባቸው እንዲሁም ካንሰር በሰውነታቸው ውስጥ የተሰራጨ ሕሙማንም በሙከራው ተሳትፈዋል።

መድኃኒት አምራቾቹ መርክ እና ሞደርና እንዳስታወቁት፤ ክትባቱ የእያንዳንዱን ታካሚ ካንሰር ለይቶ ዒላማ ማድረግ የሚችል ነው።

ክትባቱ የተዘጋጀው ለኮሮናቫይረስ ክትባት በተሠራበት የኤምአርኤንኤ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው።

ምርምሩ የካንሰር ሕሙማንን ሕዋስ የተወሰነ ክፍል ወስዶ የዘረ መሉን ቅደም ተከተል ማጥናትን ያካትታል። በዚህም ካንሰሩ እንዳይስፋፋ ማድረግ ይቻላል።

ለእያንዳንዱ የካንሰር ታማሚ ተስማሚ በሆነ መንገድ የሚሠራው ይህ ክትባት፣ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም ካንሰር ያለባቸውን ሕዋሳት ለይቶ እንዲያጠቃ ያስችላል።

መድኃኒት አምራቾቹ ኩባንያዎች ለሳምባ፣ ለሽንት ፊኛ እና ለኩላሊት ካንሰሮች ክትባት ለመሥራት ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።

የሞደርና ዋና ኃላፊ ስቴፋኒ ባንሲል እንዳሉት ግኝታቸው በካንሰር ምርምር "ታሪክ ለዋጭ" ነው።

ግኝቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ የመርክ እና ሞደርና የገበያ ድርሻ ጨምሯል።

በዩናይትድ ኪንግደም የካንሰር ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ታሊሲያ ኩዋሎ፤ ክትባቱ "ተስፋ ሰጪ" ቢሆንም ውጤቱ ገና ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

"ለእያንዳንዱ የካንሰር ታማሚ የሚሆን ክትባት ለመሥራት የሚረዱ ምርምሮች በገንዘብ እየተደገፉ መቀጠል አለባቸው። እነዚህ ክትባቶች ሕሙማን የተሻለ እና ረዥም ሕይወት እንዲኖራቸው ይረዳሉ" ብለዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የካንሰር ተመራማሪ እና መምህር የሆኑት ዶ/ር ሌናርድ ሊ "ግኝቱ ሜላኖሚያ ላለባቸው ሰዎች ትልቅ ዜና መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ለእያንዳንዱን ሕሙማን ተስማሚ ሆኖ የሚሠራ ክትባት ውጤታማነት ላይ ተጨማሪ ምርምሮች ያስፈልጋሉ" ሲሉ አስረድተዋል።