ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ተዓምራዊ" በተባለ ሕክምና ማሕጸን ውስጥ ቀዶ ጥገና የተደረገለት ጽንስ
አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ዶክተሮች ፈር ቀዳጅ በተባለው ቀዶ ሕክምና፤ ያልተወለደ ልጅ ላይ የተፈጠረን የጤና እክል ጽንሱ ማህጸን ውስጥ እያለ በተሳካ ሁኔታ ሕክምና አካሄዱ።
የለንደን ነዋሪ የሆነችው የሕጻኑ እናት ሜሲ ሳቬጅ የ26 ሳምንት ነፍሰ ጡር እያለች አሜሪካ ውስጥ ባለ ዶክተሮች ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል።
አሁን ተወልዶ አምስት ወሩን የያዘው ሕጻኑ ቲዮ፤ ማሕጸን ውስጥ እያለ እምብርቱ በትክክል ባለመፈጠሩ አንጀቱ ከሰውነቱ ውጭ ሆኖ እያደገ ነበር።
ዶክተሮች ሕክምናው ያደረጉት የእናትየውን ማጽሐን በከፊል በመክፈት ነው። ትንሽ ቀዳዳን በመጠቀም ቀዶ ሕክምና የሚደረግበትን ዘዴ የተጠቀሙት ዶክተሮቹ፣ የሕጻኑን አንጀት በቀስታ በመግፋት መልሰው ወደ ሆዱ አስገብተውታል።
ቲዮ፣ በዚህ በዓይነቱ ልዩ የተባለ ክሊኒካል ሙከራ ሕክምና የተደረገለት በዓለም ሦስተኛው ሕጻን ነው።
በሙያቸው መምህራን የሆኑት የ29 ዓመቷ ሜሲ እና የ36 ዓመቱ የሕጻኑ አባት ጆሽ ፍራንስ፣ በዚህ ፈር ቀዳጅ ቀዶ ሕክምና ስኬት ይሄ ነው የማይባል እፎይታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ሕጻኑ ይህንን ሕክምና ባያገኝ ኖሮ ሁኔታዎች እጅግ የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉም መገንዘባቸውንም ይገልጻሉ።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በየዓመቱ 3,000 ሕጻናት አብሮቸው ከሚፈጠር የጤና እክል ጋር ይወለዳሉ።
የተሻለ ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሕጻናት ለሳምንታት ፅኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚቆዩ ሲሆን ምግብ የሚሰጣቸውም በቱቦ ወይም በደም ስር በሚገባ መርፌ ይሆናል። የማስተካከያ ቀዶ ሕክምናም ይደረግላቸዋል።
እንደ ቲዮ ባሉት አብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ግን ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ይሆናል። ሕጻናቱ እስከ ስድስት ወር ፅኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ ይቆያሉ፤ በርካታ ቀዶ ሕክምናዎችም ይደረጉላቸዋል።
እስከ ሁለት ዓመታቸው ድረስ ምግብ የሚያገኙት በደም ስር በሚገባ መርፌ ሲሆን የአንጀት ቀዶ ሕክምናም ሊደረግላቸው ይችላል።
ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ተደርጎም እንኳ ከ10 ሕጻናት ውስጥ አንዱ ሕይወቱ ያልፋል።
የቲዮ ወላጆች ያልተወለደው ልጃቸው ላይ ይህ አይነት ጤና እክል መኖሩን አላወቁም ነበር።
አባትየው ጆሽ፤ "በ20ኛው ሳምንት የስካን ምርመራ የልጃችንን ምስል በማግኘታችን ብቻ ደስተኛ ነበርን" ሲል ሁኔታውን አለመገመታቸውን ያስረዳል።
ጆሽ እንደሚናገረው ቲዮ የአንጀት ከሰውነት መውጣት (ጋስትሮስኪሲስ) እንዳለበት ማወቅ አስደንጋጭ እና "እጅግ አስፈሪ" ነበር።
የሁኔታውን ውስብስብነት የተረዱት በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን የሚገኙ ዶክተሮች በአሜሪካ ሂውስተን ከተማ ወዳለው ቴክሳስ የሕጻናት ሆስፒታል መርተዋቸዋል።
በዚያ ሆስፒታል የሚገኘው በዶ/ር ማይክል ቤልፎርት የሚመራ የፅንስ እና የህፃናት ቀዶ ጥገና ሐኪሞች ቡድን፣ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ከወሊድ በፊት የሚከሰት የአንጀት መውጣትን የሚያክም ክሊኒካዊ ሙከራ ያደርጋል።
የቡድኑ መሪ የሆኑት ዶ/ር ቤልፎርት ከዚህ ቀደምም የአከርካሪ ዘንግ ክፍተት (ስፓይና ቢፊዳ) ያጋጠማቸው ሕጻናት ማሕጸን ውስጥ እያሉ ቀዶ ሕክምና አድርገዋል።
ሜሲ ቀዶ ሕክምናው የተደረገላት ባለፈው ህዳር ላይ የ26 ሳምንት ነፍሰ ጡር እያለች ነው። ህክምናው የተደረገው ማሕጸኗ እና ፅንሱ በከፊል እንዲከፈት ተደርጎ ነው።
ማሕጸን ውስጥ የሚገኘው የአምኒዮቲክ ፈሳሽም እንዲወጣ ተደርጎ የቀዶ ጥገና የሚደረግበትን ቦታ ለማስፋት በሚያስችው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ ተተክቷል።
ቀጥሎም በአነስተኛ ክፍተት ቀዶ ሕክምና የሚደረግበትን ዘዴ በመጠቀም በቀስታ የቲዮ አንጀት ወደ ሆዱ ተገፍቷል። ከዚያም በስፌት ሆዱ ተዘግቷል።
ይህ ሂደት ሜሲ በቀዶ ሕክምና ልጅ ሲወለድ (ሲ-ሴክሽን) ከሚፈጠረው የበለጠ ጠባሳ ሰውነቷ ላይ እንዲኖር አድርጓል። የእርሷን ሁኔታ ከሌሎች ሴቶች የሚለየው ግን፣ በሲ-ሴክሽን ከወለዱ ሴቶች በተቃራኒ ለተጨማሪ 14 ሳምንታት ልጁን በማሕጸኗ ማሳደግ መቀጠል ነበረባት።
ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ቲዮ ማሕጸኗ ውስጥ ሆኖ በሚማታበት ጊዜ ቁስሉን ስለሚመታው ሕመም ይፈጥርባት እንደነበር ታስታውሳለች። "የማገገም ሂደቱ ከባድ ነበር። ቢሆንም ግን ዋጋ ያለው ነገር ነው" ብለላች።
ቀዶ ሕክምናው ስኬታማ ሆኗል። ቲዮም ባለፈው የካቲት ላይ በምጥ ተወልዷል። በአሁኑ ሰዓት ወደ መኖሪያቸው ለንደን ተመልሰዋል፤ ሕጻኑም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
የሕክምና ቡድኑን የሚመሩት ዶ/ር ቤልፎርት፣ እርሳቸው እና ቡድናቸው በውጤቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"እናትየው፣ ሕፃኑ፣ ቀዶ ጥገናው፣ ቀዶ ጥገናው የተካሄደበት ጊዜ እንዲሁም በፅንስ ቀዶ ጥገናው ወቅት እና ከቀዶ ጥገናው በኋላ ምንም ዓይነት ውስብስብ ችግር አለመከሰቱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው" ብለዋል።
"በአሁኑ ሰዓት የማህጸን አዲሱ የቀዶ ጥገና ቦታ ሆኗል" የሚሉት ዶ/ር ቤልፎርት፣ ከአንጀት መውጣት እና ከአከርካሪ ዘንግ መውጣት ውጪ ያሉ የጤና እክሎችም ከወሊድ በፊት ሕክምና የሚያገኙበት ዕድል እንደሚኖር እምነታቸውን ገልጸዋል።