እስራኤላውያን ሠፋሪዎች በዌስት ባንክ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ላይ ከበባ ፈጸሙ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እስራኤላውያን ሠፋሪዎች በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ የሁለት ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ቤት ላይ ከእሁድ ዕለት አንስቶ ከበባ አደረጉ።

ላለፉት አራት ቀናት ከበባ ውስጥ ያሉት ቤተሰቦች ቤታቸው ውስጥ ያለው ምግብ እና ውሃ እያለቀ መሆኑን ገልጸዋል። የመብት ተሟጋች ቡድኖች በበኩላቸው ባለሥልጣናት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

ፍልስጤማውያን ነዋሪዎች ስላጋጠማቸው ጉዳይ ለእስራኤል ጦር ካመለከቱ በኋላ ወደ ስፍራው የመጡት ወታደሮች ከመንደሩ ከሚገኙት ሠፋሪዎች ጋር ሲጸልዩ ታይተዋል።

የውሃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት የተቋረጠባቸው እንዲሁም የነበራቸው ምግብ ያለቀባቸው የአቡ ሪዲ እና የሐሰን ቤተሰቦች፣ እርዳታ ለማግኘት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ቤተሰቦቹ ላይ ከበባ የፈጸሙት ሠፋሪዎች ምን እንደሚፈልጉ በትክክል አልታወቀም። ከዚህ ቀደም ግን እስራኤላውያን ሠፋሪዎች ፍልስጤማውያንን ከቤታቸው በማፈናቀል ንብረቶቻቸውን ወርሰዋል።

ሠፋሪዎቹ ስፍራውን ፍልስጤማውያን የማይኖሩበት የማድረግ ግብ አላቸው።

የአሁኑ ከበባ የተሰማው የተባበሩት መንግሥታት ከተፍኛ ኃላፊ ማክሰኞ ዕለት ኒውዮርክ ውስጥ በተካሄደ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የዌስት ባንክ ጉዳይ "ጫፍ ላይ መድረሱን" በተናገሩበት ወቅት ነው።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ዌስት ባንክ ግዛት ውስጥ የተደረጉት የእስራኤል ሠፈራዎች ሕገ ወጥ ናቸው። እነዚህ መንደሮች የተቋቋሙት ያለ እስራኤል ይፋዊ ፈቃድ ነው።

እሁድ ምሽት በፍስልጤማውያኑ የደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ምስል፣ ሠፋሪዎቹ በአቡ ሪዲ ቤተሰብ መኖሪያ የሚገኝ ግድግዳን ሲያፈርሱ ያሳያል። ከፈረሰው ግድግዳ የተገኘ ድንጋይ በመጠቀምም መንገድ ሲዘጉ ይታያል።

ይህ የሠፋሪዎቹ ድርጊት፣ ሁለት ታዳጊ ሴት ልጆችን ጨምሮ በቤቶቹ ውስጥ የሚገኙት ሰባት ሰዎች መውጣት እንዳይችሉም ሆነ ሌሎች ፍልስጤማውያን እንዳይደርሱላቸው አድርጓል።

ቤተሰቦቹ የሚኖሩበትን 'ኤሪያ ቢ' የተባለ የዌስት ባንክ ስፍራ አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚመሩት በፍልስጤም አስተዳደር ሲሆን ደኅነትን የሚቆጣጠረው ግን የእስራኤል መንግሥት ነው።

የቤተሰቡ አባል የሆነው ቁሳይ አቡ ሪዲ፣ "በተለይም ሙሉ በሙሉ እንዲነጠሉ" መደረጉ ሁኔታውን አሳሳቢ እንዳደረገው ፌስቡክ ላይ ባጋራው ልጥፍ ገልጿል።

"በራሳችን ቤት፣ በራሳችን መሬት ላይ እየኖርን ነው፤ በሰላም እና በክብር ከመኖር መብት በዘለለ እየጠየቅን አይደለም" ብሏል።

ከበባ ከተደረገባቸው ቤቶች በአንዱ ነዋሪ የሆነችው አይሻ ሀሰን በበኩሏ፣ የቤቱን "በር ለመስበር እንደሞከሩ" እንዲሁም "ድንጋይ እንደወረወሩባቸው፤ መራገም እና መስደብ" መጀመራቸውን ለዜና ወኪሉ ሮይተርስ ተናግራለች።

በሰኞ ዕለት እስራኤላውን ሠፋሪዎቹ ጋዜጠኞች ከበባ ወደተፈጸመባቸው ፍልስጤማውያን እንዳይደርሱ አግደዋል።

በማግሥቱ "የስ ዲን" የተሰኘው የእስራኤል የሰብአዊ መብቶች ቡድን፣ ከበባ የተፈጸመባቸው ነዋሪዎች በአገሪቱ ጦር ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ሠፋሪዎቹ ስፍራውን እንዲለቅቁ እንዲሁም ተጠያቂ እንዲደረጉ ለእስራኤል ጦር ማዕከላዊ አዛዥ አቤቱታ አቅርቧል።

ማክሰኞ ምሽት ላይ አንድ የፍልስጤም አምቡላንስ ወደ ተከበቡት ቤቶች ተጉዞ ምግብ እንዲያደርስ እና ሕክምና የሚያስፈልገው አንድ ልጅን እንዲወስድ ተፈቅዶለታል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በዚያው ሰዓት ባወጣው መግለጫ፣ አዲስ የሠፈራ መንደሮችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት አውግዟል። ወደ ፍልስጤማውያን ቤቶች መግባት እና መኖሪያዎቹን መቆጣጠር መያዝ "ሕገ-ወጥ" እና "ተቀባይነት የሌለው" ድርጊት መሆኑን ገልጿል።

ረቡዕ ዕለት ወደ አካባቢው የገቡት የእስራኤል የጸጥታ አካላት፣ ከአክራሪ ሰፋሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ፣ ቁስራ የተባለ መንደር ውስጥ የአይሁድ ሠፋሪዎች አካባቢ ለቅቀው መውጣታቸው ተዘግቧል። በርካታ ሠፋሪዎች ግን አሁንም ቦታው ላይ ናቸው።