ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል በአርኪኦሎጂ ቅርሶች ሰበብ የመሬት ወረራ እየፈጸመች ነው በሚል ተወነጀለች
በወረራ በተያዘው ዌስት ባንክ በሚገኘው ታሪካዊው የሴባስቲያ ኮረብታ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ለዓመታት የወይራ ዛፍ ሲያለሙ ኖረዋል።
በአካባቢው እርሻ ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው አቡ ሙዲፍ እስራኤል በአካባቢው ብሔራዊ ፓርክ ለመገንባት ስለምትፈልግ እንዲነሳ እንደተነገረው ያስረዳል።
ከዚህ በፊት እንደታየው ከመሬታቸው የሚነሱ ፍልስጤማውያን የሚሰጣቸው ጥቂት የካሳ ገንዘብ ሲሆን አንዳንዶቹም ያለምንም ክፍያ ባዶ እጃቸውን ተሰናብተዋል።
አንዳንዶች የገንዘብ ካሳ መቀበል ከወላጆቻቸው በውርስ ያገኙት ንብረት እንዲወሰድ ይሁንታ የሰጡ ስለሚመስላቸው ፈቃደኛ አይሆኑም።
ለአቡ ሙዲፍ የወይራ ዛፎቹ የገቢ ምንጩ ብቻ ሳይሆኑ ከዚያም ባለፈ ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው።
"መግለጽ ካለብኝ ማለት የምችለው ከስጋዬ ላይ ተቦጭቆ እንደሄደ ያህል ነው የተሰማኝ። ሕይወቴን ከዚህ መሬት ውጪ ማሰብ አልችልም" ብሏል።
ናሄድ ሳካ በአካባቢው የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት ምግብ ቤት ባለቤት ናቸው።
እስራኤል ከአርኪኦሎጂ ሥፍራው ፍልስጤማውያን ነዋሪዎችን ለማራቅ ሆነ ብላ እየሰራች ነው ይላሉ።
ይህ ታሪካዊ የአርኪዎሎጂ ሥፍራ ሺህዎች ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአይሁዶች ጥንታዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ነው።
"የቁፋሮ እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እየተካሄዱ ነው" የሚሉት ናሄድ "በአካባቢው እርሻ ያላቸው ማረስም ሆነ መጠቀም እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል" ይላሉ።
የሴባስቲያ መንደር ነዋሪዎችን ያሳሰባቸው ነገር የመንግሥታቱ ድርጅት የባሕል እና ትምህርት ኤጀንሲ፣ ዩኔስኮም የሚጋራው ነው።
ቦታው የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሶ አካባቢው አደጋ ላይ መሆኑን ገልጿል።
ዩኔስኮ የቅርስ ሥፍራው በዋናነት አደጋ የተደቀነበት "የ'ሳማሪያ' (ሾምሮን) ብሔራዊ ፓርክን ለማቋቋም ታቅዶ የሚከናወነው የመሬት መንጠቅ ሂደት ሲሆን፣ ይህም ቦታውን ለሁለት ሊከፍለው ይችላል"።
የአካባቢው ከንቲባ መሐመድ አዜም በአንድ በኩል በሴባስቲያ መግቢያ ላይ በሚገኘውና ቀደም ሲል የሮማውያን ዘመን የሕዝብ መሰብሰቢያ ሥፍራ በነበረበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ እምነቱ ዓምዶች መካከል በሚገኝ መንገድ ላይ ቆመው ከፍርስራሹ መካከል የተጣለ ቆሻሻን ይመለከታሉ።
ከእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች እና ከሰፋሪዎች ጋር ችግር ሊፈጥር ስለሚችል፣ አካባቢውን ለማጽዳት ወደ ታች መውረድ ነዋሪዎችን እንደሚያሳስብ ይናገራሉ።
የቆሙበት መንገድ ቦታውን በሁለት ይከፍለዋል፤ እነሱም በሲቪል ጉዳዮች ረገድ በፍልስጤማውያን፣ በደኅንነት ረገድ ደግሞ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የዌስት ባንክ 'አካባቢ ለ' (Area B)፣ እንዲሁም በሲቪል እና በደኅንነት ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር የሚገኘው 'አካባቢ ሐ' (Area C) ናቸው።
ባለፈው ሳምንት እስራኤል በዌስት ባንክ በሚገኙ የአርኪኦሎጂ ቦታዎች ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማስፋት ወደ 27.8 ሚሊዮን ፓውንድ የሚጠጋ በጀት መድባለች። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አንዳንዶቹ በፍልስጤም አስተዳደር ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ቦታዎችን ያካትታሉ።
በቅርቡ እዚህም እስራኤል፣ ለቦታው "ጥበቃና ልማት" በሚል ሰበብ ወደ 80 ኤከር (32 ሔክታር) የሚጠጋ መሬት መውሰድ ጀምራለች።
የእስራኤልን ሰፈራዎች የሚከታተለው "ፒስ ናው" የተባለው የእስራኤል ድርጅት "በዓለም አቀፍ ሕግ እንዲሁም በእስራኤል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎች መሠረት፣ እስራኤል ለሰፈራ ዓላማዎች ወይም ለእስራኤል ዜጎች ብቻ ጥቅም ሲባል መሬትን መውሰድ የተከለከለ ነው።"
"በመሆኑም፣ የመሬት ይዞታን በግዴታ የመውሰድ እርምጃው ሕጋዊ እንደሆነ እንዲቆጠር፣ መንግሥት ቦታው ለፍልስጤማውያንም ሆነ ለእስራኤላውያን ሕዝቦች አገልግሎት ለመስጠት የታሰበ መሆኑን በመከራከሪያነት ሊያቀርብ ይችላል፤ ምንም እንኳን ዋናው ምክንያትና ዓላማው ከሰፈራ ማስፋፋት እና ከእስራኤል ቁጥጥር ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም" ብሏል።
ሴባስቲያ ውስጥ የሚገኙት እስራኤላዊው አክቲቪስት አሎን አራድ ይህ ሕግ መኖሩ በዌስት ባንክ ውስጥ የአርኪኦሎጂ ጥናት እንዴት ለመሬት ወረራነት ጥቅም ላይ እንደዋለ ያሳያል ሲሉ ይከራከራሉ።
"አሰራሩ በትክክል የሚከናወነው በዚህ መንገድ ነው። የአርኪኦሎጂ ጥናትን ለቁፋሮ እና ታሪክን እንደገና ለመጻፍ ይጠቀሙበታል፤ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ መሬትን ከፍልስጤማውያን እጅ ወደ እስራኤላውያን ለማዛወር ወይም አሰፋፈርን ለመለወጥ ይጠቀሙበታል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የሴባስቲያ ነዋሪ የሆኑ ፍልስጤማውያን፣ ከእነዚህ ጥንታዊ ፍርስራሾች ጋር ያላቸው ጥልቅ ትስስር የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ስጋት እያደረባቸው ነው።