ትራምፕ ኢራን እስከምትስማማ ድረስ በሆርሙዝ ላይ የጣሉትን እገዳ እንደማያነሱ አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካ ከቴህራን ጋር ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ እንደማታነሳ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ጦርነቱን ለማስቆም ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሁለተኛ ዙር ድርድር ስለመካሄዱ እርግጠኛ መሆን ባልተቻለበት ወቅት ነው።

ትራምፕ ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጉት እገዳ "ኢራንን ሙሉ በሙሉ እያወደመ ነው" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ትራምፕ አክለውም አገራቸው ጦርነቱን "በብዙ መልኩ እያሸነፈች ነው" ብለዋል።

ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት የተሰማው አሜሪካ እና ኢራን ያደረጉት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ብቻ በቀሩበት ወቅት ነው።

ነገር ግን በፓኪስታን ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ስለመካሄዱ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።

በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ ድርድሩ ሊካሄድ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ የተጠናከረ የጸጥታ ሁኔታ ይታያል። ነገር ግን የአሜሪካውን ልዑክ የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ ዋሺንግተንን ለቅቀው ያልሄዱ ሲሆን ኢራንም በድርደሩ ላይ ለመሳተፍ አለመወሰኗን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንቲኮም) እገዳው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካ ባሕር ኃይል 27 መርከቦች ወደ ኢራን ወደብ እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካ እሁድ ዕለት እገዳውን ለማለፍ የሞከረ የኢራን ባንዲራ የሚያውለበልብን የጭነት መርከብን ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር አውላለች ።

ሴንቴኮም ያጋራቸው ቪዲዮዎች የአሜሪካ ወታደሮች ወደ መርከቡ ከመግባታቸው በፊት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ያሳያሉ።

ቴህራን ይህንን "የባህር ውንብድና ተግባር" እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት መሆኑን ተናግራለች።

ኢራን ለሁለት ወራት ያህል ለዓለም የነዳጅ አቅርበት ቁልፍ የሆነውን ሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የዘጋች ሲሆን ይህም የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል።

ወሽመጡ ቅዳሜ ዕለት ለአጭር ጊዜ ዳግም ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም ፣ በባሕሩ ዳርቻ ወይም አቅራቢያ መርከቦች በቴህራን ዒላማ መሆናቸው ከተዘገበ በኋላ በፍጥነት እንደገና ተዘግቷል።

ትራምፕ ኢራን "ጥይት ለመተኮስ ወስናለች" ካሉ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነቱን "ሙሉ በሙሉ መጣስ" ነው ሲሉ ኮንነውታል።

ኢራን አሜሪካ ወደቦቿን መዘጋት እስክታቆም ድረስ መተላለፊያውን እንደምትዘጋ አስታውቃለች።

ቴህራን ልዑካኗን እንደምትልክ ለማረጋገጥ ፈቃደኛ ባትሆንም፣ አሜሪካ እና ኢራን ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር እንደሚካሄዱ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከተደረገው የመጀመሪያ ዙር ውይይት በኋላ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ "ኢራናውያን የኛን ነጥቦች ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም" ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ዋሽንግተን "የተለጠጡ ፍላጎቶች እና ሕገወጥ ጥያቄዎችን" ከማቅረብ እንድትቆጠብ አሳስበዋል።

ሁለተኛው ዙር ድርድር የሚካሄደው ወሳኝ በሆነ ወቅት እንደሆነ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ምንጮች የአሜሪካ ልዑካን ቡድን "በቅርቡ" ወደ ኢዝላማባድ እንደሚያቀና ቢገልጹም የጊዜ ገደብ ግን አላሳወቁም፤ ሌሎች ባለሥልጣናት ግን ለኒውዮርክ ታይምስ ማክሰኞ ዕለት እንደሚነሱ ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ "እስካሁን ድረስ" ቴህራን "ለመሳተፍ ምንም ዕቅድ" እንደሌላት ተናግረዋል።

ቫንስ ከልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች እና አማካሪ ከሆነው ጄሬድ ኩሽነር ጋር በመሆን በድርደሩ ላይ አንደሚሳተፉ ታውቋል።

ኢራን በድርድሩ ላይ የምትሳተፉ ከሆነ እነማን እንደሚገኙ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ በኢዝላማባድ ለውይይቱ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

ቀደም ሲል የተደረገው ድርድር በተካሄደበት ሴሬና ሆቴል ውስጥ የነበሩ እንግዶች ለስብሰባዎች ዝግጅት እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። ፖሊስ ደግሞ የውጭ ልዑካን ቡድን ስለሚመጡ ቁልፍ መንገዶች መዘጋታቸውን አስታውቋል።

አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ፓኪስታን ኢራን በውይይቱ ላይ እንድትገኝ ማድረግ እንደምትችል እርግጠኛ ነች።

ንግግሩ ይደረግበታል ተብሎ ወደሚታሰበው ሆቴል የሚወስዱ መንገዶች ዝግ ተድርገዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ንግግሩ ይደረግበታል ተብሎ ወደሚታሰበው ሆቴል የሚወስዱ መንገዶች ዝግ ተድርገዋል

በቴህራን የምትገኘው የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ዘጋቢ ሊሴ ዱሴት ለሬዲዮ 4 ፕሮግራም ሁኔታው ​​ሊተነብይ የማይችል ቢሆንም፣ ውይይቱ የመካሄድ ዕድሉ አለ ብላለች።

"በዲፕሎማሲ ውስጥ አንድ ሕግ አለ [ይህም] የሆነ ነገር ለመፍረሱ ተጠያቂ የምትሆነው አንተ መሆን የለብህም" የሚል ነው።

"ጄዲ ቫንስ ኢዝላማባድ የሚገኝ ከሆነ ኢራናውያን አለመገኘታቸው በጣም ከባድ ይሆናል።"

"እናም ፓኪስታናውያን ሁለቱም ወገኖች እዚያ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ደጋግመው ስልክ እየደወሉ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ቦታው ዝግጁ ነው፣ የጸጥታ ሁኔታዎች ተሟልተዋል፤ የተደራዳሪ ቡድኖች መምጣት ብቻ ነው የሚጠበቀው።"