የአፋር ግመሎችን ጨምሮ የአፍሪካ 'የበረሃ መርከቦች' እየጨመረ ያለውን ሙቀት መቋቋም አልቻሉም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግመሎች በተለምዶ 'የበረሃ መርከቦች' በሚል ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ ሙቀት ተቋቋሚዎቹ እንስሳት በአፍሪካ እየጨመረ ያለው ሙቀት ከአቅማቸው በላይ ሆኗል ።
የኢትዮጵያው አፋር ክልል በዓለም እጅግ ሞቃታማ እና ደረቀ ከሚባሉ ሥፍራዎች መካከል አንዱ ነው።
በአካባቢው ያሉ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን በአብዛኛው ጨው ለማጓጓዝ ይጠቀሙባቸዋል። የምግብ ምንጫቸውም ናቸው፤ የግመል ወተት በአፋር እጅግ ተወዳጅ ነው።
ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታየው ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር አርብቶ አደሮቹን ስጋት ላይ ጥሏል።
500 ገደማ የሚሆኑ ግመሎች ያሏቸው የሰመራ ነዋሪው አቶ አሊ ዑመር "በከፍተኛ ሙቀቱ ግመሎቼ ሲሰቃዩ እያየሁ ነው" ብለዋል ለቢቢሲ።
"እግራቸው ውሃ ይቋጥራል፤ ዓይናቸው እንባ ያዝላል። መሬት ላይ ቁጭ በሚሉበት ጊዜም ሞቃታማው አሸዋ ቆዳቸውን ያቃጥለዋል፤ ፀጉራቸው ይላጣል።" ሲሉ ግመሎቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
በከፍተኛ ሙቀቱ ሳቢያ ባለፈው አንድ ወር ብቻ ስምንት የግመል ግልገሎችን ማጣታቸውን እና ሁኔታው አስቸጋሪ መሆኑን አቶ አሊ ተናግረዋል።
"ቀዝቃዛ አየር ያመጣ የነበረው ነፋስ እንኳ አሁን ሙቀት ይዞ ነው የሚመጣው" ብለዋል።
እንዲህ ዓይነቶችን ለውጦች የተመለከቱት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የ40 ዓመቱ አሊ እንዲህ ዓይነት ከባድ የአየር ንብረት ለውጦችን የተመለከቱ ብቸኛው ሰው አይደሉም።
ተመራማሪዎች፣ የእንስሳት ደኅንነት ሠራተኞች እና በርካታ ጥናቶች፣ ከፍተኛ ሙቀቱ እንደ ጭንቀት፣ ድካም፣ የውሃ እጦት፣ በሽታ አለመቋቋም ያሉ ቀጥተኛ ተፅዕኖዎችን አስከትሏል ይላሉ።
በተዘዋዋሪ መልኩ ደግሞ ግመሎች ውሃ እና እፅዋት እንዲሁም የሚጠለሉባቸው ቦታዎች እንዳያገኙ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images
ሰሜን አፍሪካ እና ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ 80 በመቶው የዓለም ግመል መገኛ ናቸው።
በዚህ ቀጣና የሚኖሩ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ከረዥም ዓመታት በፊት ነበር በእንስሳቱ ሙቀት ቻይነት እና በድርቅ ምክንያት ግመሎችን ወደ ማርባት የተሸጋገሩት።
ይሁን እንጂ እ.አ.አ.በ2025 በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ግመል አርቢዎች ምልከታ ላይ ተመስርቶ የተሠራ ጥናት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ከፍተኛ ሙቀት እና የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭነት በግመሎች ጤና ላይ ተፅዕኖ ማድረሱን አመልክቷል።
"ተሳታፊዎች [ግመል አርቢዎች] የአየር ንብረት ለውጥ እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በግመሎች ጤና፣ ምርታማነት እና ሥነ ተዋልዶ ላይ ተፅዕኖ እንዳደረሰ ሪፖርት አድርገዋል" ብሏል።
የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሶማሊያ ሁኔታው የከፋ ይመስላል።
ባለፈው ሰኔ የታተመ አንድ ጥናት ከድርቅ ጋር በተያያዘ የሚከሰት የግመሎች ሞት በአገሪቷ መጠነ ሰፊ ቀውስ ማስከተሉን እና 46 በመቶ የሚሆኑ የግመል ባለቤቶች ተጎጂ መሆናቸውን አመልክቷል።
6 ሺህ የሚጠጉ የግመል ባለቤቶችን ያሳተፈው እና አብዛኛው የግመል ሞት የተመዘገበው በሰሜን ግዛቶች መሆኑን የጠቀሰው ጥናቱ፣ "73 በመቶ አስደንጋጭ የሞት ምጣኔ ታይቷል" ብሏል።
በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ሙቀት ዋነኛው ምክንያት ድርቅ ቢሆንም በቂ የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት አለመኖር እና የእንስሳት አስተዳደር ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል ይላሉ ባለሙያዎች።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት በቀጣናው ያለው ከፍተኛ ሙቀት ከ2021 እስከ 2022 ለነበረው ድርቅ ዋነኛ ምክንያት ነው።
ከፍተኛ ሙቀት ከመሬት እና ከረግረጋማ ቦታዎች ውሃ እንዲተን እና እፅዋት የሚለቁት ውሃ እንዲተን ያደርጋል።
የእንስሳት ሐኪሞች የታመሙ ግመሎች ቁጥር እንደጨመረ እና በከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ሞት እያዩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያን በሚጎራበተው የኬንያ መርሳቤት ግዛት የእንስሳት ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ሀሰን ኑያ ጉዮ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በግመሎች ከባድ ሙቀት (ሀይፐርተርሚያ) በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እያየን ነው። በዚህ ምክንያት ለተለያዩ ኢንፌክሺኖች [በሽታዎች] ይዳረጋሉ።"
"ባለፉት ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ በአገራችን የግመሎች ሞት ከ15 በመቶ በላይ መጨመሩን አይተናል።" ብለዋል ባለሙያው።
በአፍሪካ ቀንድ የተሰራ ሌላ ጥናትም በግመሎች የበሽታ ሥርጭት እና የወተት ምርት መቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች መሆናቸውን አመልክቷል ።
በሰሜን አፍሪካም ተመሳሳይ ሁኔታ እየታየ ነው።
በአልጄሪያ ባለፈው ዓመት የተሰራ አንድ ጥናት በበጋ የሙቀት ማዕበሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግመሎች እንደሚሞቱ አሳይቷል።
"በተመሳሳይ ወቅቶች በተከታታይ የተሰሩ ትንታኔዎች፣ በተወሰኑ ወቅቶች የግመሎች ሞት እንደሚጨምር አሳይተዋል። ስለዚህም ከፍተኛ ስጋት ያለባቸውንና እንደ በጋ ያሉ ወቅቶችን ታሳቢ ያደረገ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የውሃ አቅርቦት፣ የምግባ ድጋፍ እና የሽታዎችን ቅኝት መጨመር" ሲል ጥናቱ መክሯል።
የዓለም የሚትዮሮሎጂ ኤጄንሲ፣ ከፍተኛ ሙቀት በበርካታ የሰሜን አፍሪካ አገራት የተለመደ ሆኗል ይላል። የሙቀት ሞገድ ከአውሮፓውያኑ 1981 ወዲህ እያሻቀበ ነው።
በ2024 በቀጣናው እና በመካከለኛው ምሥራቅ በርካታ አገራት ከ50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ሙቀት ሪፖርት አድርገዋል ብሏል።
ባለሙያዎች ግመሎች ለ40 ዲግሪ ገደማ ሙቀት ተስማሚ እንደሆኑ ይገልጻሉ።
እንስሳቱ ውጫዊ ሙቀትን ለመከላከል የሰውነታቸውን ሙቀት በተለያዩ ዲግሪዎች መለዋወጥ ይችላሉ።
ይህን በማድረግ ላብ እንዳይፈጠር ያደርጋሉ። ይህም ከተጠራቀመ ሽንት እና ሰገራ ጋር ተዳምሮ የውሃ ብክነትን ለመቀነስ ይረዳቸዋል። ወፍራም የቆዳ መሸፈኛቸው ደግሞ የፀሐይ ጨረርን ለመከላከል ይረዳቸዋል።
የዓለም የምግብ እና ግብርና ድርጅት ተመራማሪ ዶ/ር ሞሐመድ ብንጉሚ በግመል ጤና ላይ አተኩረው ይሰራሉ።
ተመራማሪው " ግመሎች ሙቀቱ ከሚችሉት በላይ ሲጨምር ድካም ያሳያሉ" ይላሉ።
"በበርካታ የሰሃራ አካባቢዎች የበጋ ሙቀት አሁን ከ50 ድግሪ በላይ አልፏል፤ ይህም የከፍተኛ ሙቀት የድካም ስጋትን ጨምሯል። በዋናነት የእፅዋት ሽፋን መቀነስ፣ የውሃ እጥረት እና የጥላ እጦት ሲጨመርበት ስጋቱ ከፍ ይላል" ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Hassan Nuya Guyo
በአልጄሪያ ጋራዳይ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አብደልመጂድ ቸማም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያላቸው።
"ምርምራቸውን እንደሚያሳየው ከ41 እስከ 45 ድግሪ የሚደርሰው ረጅም የቀን እና የምሽት ሙቀት በቀጥታ ህዋሳቸውን ይጎዳል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ይጎዳል። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት የሙቀት ደረጃ ቀይ የደም ህዋሳቸውን እና ሌሎችንም ይጎዳል። የደም ህዋሶች ራሳቸውን ለማደስ ይቸገራሉ እና ራሳቸውን ይጎዳሉ።"
ግመሎች ሙቀቱ ሲበረታባቸው ሰውነታቸው ውስጣዊ ሙቀት ማመንጨቱን ይቀንሳል። ይህ ደግሞ ምግብ አወሳሰዳቸውን በመቀነስ አደገኛ ሁኔታ እና አጠቃላይ ድካም እንዲሰማቸው ያደርጋል።
ይህ ደግሞ የወተት ምርታቸው እንዲቀንስ እና የሥነ-ተዋልዶ መዛባት እንዲከሰት ያደርጋል።
በሞሮኮ ካዛብላንካ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ሃይድሮባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሞሐመድ ኤል ካሲሚ፣ የሙቀት ጫና በርካታ ተፅዕኖዎችን እንደሚያስከትሉ ይገልጻሉ።
የክብደት መቀነስ፣ እብጠት፣ ጡንቻ እና የአጥንት ህመም፣ ኩላሊት በአግባቡ አለመስራት የኬሚካል ሚዛን መዛባት፣ በተህዋሲያን የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች ከእነዚህ መካከል ይገኙበታል ይላሉ።
የዚህ ሁሉ መንስዔ ከፍተኛ ሙቀት ቢሆንም እንደ የእፅዋት እና ውሃ እጦት፣ ጥላ ቦታዎች ማጣት እና በቂ የሕክምና አገልግሎት አለማግኘት ሲጨመሩበት ተፅዕኖው እጅግ ከባድ ይሆናል ይላሉ ባለሙያው።
ለዚህም ነው በርካታ የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን ከታሪካዊ መገኛቸው ከሰሜን ኢትዮጵያ ውሃ እና እፅዋት በተሻለ መልኩ ወደሚያገኙበት ደቡብ ኢትዮጵያ ለማዘዋወር የተገደዱት።
ምንም እንኳን አቶ አሊ ግመሎቻቸውን ወደ ሌላ አካባቢ ባይወስዱም፤ ውሃ እና ምግብ ፍለጋ ወደ አዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የወሰዱ እንዳሉ ገልጸዋል።
" እኔ ውሃ በቦቲ መኪና እየቀዳሁ፣ ሳር እየገዛሁ ልንከባከባቸው እየሞከርኩ ነው። ሙቀቱ ሲበረታም ውሃ እያርከፈከፍኩ እንዲቀዘቅዙ እያደረኩ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ali Umer
የቪዢን ዩኒቨርስቲ የአርብቶ አደሮች ልማት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳንኤል ገላን "የአርብቶ አደሮች ዝውውር ወቅታዊ አይደለም" ይላሉ።
"ሰሜናዊ ክልሉን ለመጨረሻ ጊዜ እየለቀቁ ነው። ምክንያቱም በከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ በአካባቢው ግመልን ማርባት ከዚህ በኋላ ባለመቻላቸው ነው" ብለዋል ለቢቢሲ።
የአፍሪካ ቀንድ ከ2020 እስከ 2023 ከተከሰተው ረጅም እና በጣም ከባድ ድርቅ እያገገመ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ሌላ ዙር ከባድ ሁኔታ እያጋጠመው መሆኑን ረድኤት ድርጅቱ ኦክስፋም ገልጿል።
እንደ ደርጅቱ ከሆነ በድርቁ ምክንያት በአንዳንድ የሶማሊያ ክፍሎች የውሃ ዋጋ በ2 ሺህ በመቶ ከፍ ብሏል።
የአፋሩ አርብቶ አደር አሊ ዑመርም የሆነ ጊዜ በሽታ ተቀስቅሶ ግመሎቻቸውን ይገድልብኛል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ቸካ ከሆነ ስጋታቸው ተጨባጭ ነው።
ግመሎች በተፈጥሮ ባላቸው ሙቀት የመቋቋም ችሎታ ለበረሃማ አካባቢዎች ተፈላጊ ቢያደርጋቸውም አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ እየሆኑ ነው ብለዋል።















