ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ትምህርት ቤት ውስጥ በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ20 በላይ ልጆች ሞቱ
በምሥራቃዊው የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በአማጺያን ቁጥጥር ሥር ባለችው ቡካቩ ከተማ ውስጥ ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ የእሳት አደጋ ከተነሳ በኋላ ከእሳቱ ለማምለጥ በተፈጠረ መረጋገጥ ቢያንስ 24 ተማሪዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ።
በተከሰተው የእሳት አደጋ ምክንያት ከተማሪ ልጆች በተጨማሪ አዋቂዎችም ሕይወታቸውን ማጣታቸው የተመዘገበ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችልም ስጋት አለ።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች በአቅራቢያ ወደ ሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደዋል፤ ከቦታው የተቀረጹ ምሥሎችም ጉዳት የደረሰባቸው ልጆች እየተሰቃዩ በሆስፒታል ወለል ላይ ተኝተው ያሳያሉ።
በእሳቱ ምክንያት 300 ያህል ቤቶችም ወድመዋል፤ የእሳቱ መንስኤ ግን እስካሁን አልታወቀም።
በአማጺያኑ የተሾሙ ባለሥልጣናት ሐሙስ ምሽት 24 ሰዎች መሞታቸውን በመግለጽ ቀደም ሲል የወጡ ሪፖርቶችን አረጋግጠዋል፤ ሆኖም ከዚህ በላይ ሰዎች ሞተው ሊሆን እንደሚችል ስጋት አለ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ፎቶዎች ትንንሽ ልጆች መሬት ላይ ራሳቸውን ስተው ወድቀው ያሳያሉ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሰው አንድ ምስክር እንዳለው፣ እሳቱ ከሰዓታት በኋላ ቢጠፋም ከፍርስራሹ እና ከቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ አሁንም ጭስ እየወጣ ነበር።
ቡካቩ የደቡብ ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ስትሆን በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ ከሚገኙ በሕዝብ ብዛት በጣም ከተጨናነቁ ኮረብታማ ከተሞች አንዷ ናት። ከተማዋ ኤም23 አማጺያን ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ተቆጣጥረዋታል።
አደጋውን ተከትሎ በኪንሻሳ ያለው የዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት በኤክስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መግለጫ አውጥቷል፤ ሆኖም የተጎጂዎችን ቁጥር በግልጽ አልጠቀሰም።
መግለጫው የአገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር የበርካቶችን ሕይወት ባጠፋው የእሳት አደጋ በማዘን ጥልቅ ሐዘኑን ገልጿል።
የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱን እና ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውንም ጠቅሶ "የጉዳቱን መጠን ለማወቅ አሁንም ግምገማ ላይ ይገኛል። ሚኒስትሩ ለተጎጂዎች ቤተሰቦች ሐዘኑናቸውን ገልጸዋል" በተጨማሪም የተጎዱት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ግምገማ እንዲደረግ አዝዘዋል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት ያጋጠመው ባለፈው ሳምንት በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በተደረገ የሰርግ ሥነ ሥርዓት አዳራሽ ውስጥ በተነሳ እሳት እና መጨናነቅ በርካታ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሳምንት ሳይሞላ ነው።
በርካታ ሕዝብ በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ የደረሱ አደጋዎችን በተመለከተም መንግሥቱ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ጥብቅ የደኅንነት ጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲተገበሩ አዝዟል፤ እንዲሁም የደኅንነት አጠባበቅ መስፈርቶች እየተከበሩ መሆናቸውን ለመቆጣጠር ቡድኖችን በመላ አገሪቱ አሰማርቷል።