ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዴሞክራቲክ ኮንጎ ለአስርት ዓመታት ከዘለቀው ግጭት ጋር በተያያዘ ሩዋንዳን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከሰሰች
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ጥሳለች ባለቻት ጎረቤቷ ሩዋንዳ ላይ በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት (ICJ) ክስ መሠረተች።
ዴሞክራቲክ ኮንጎ ባወጣችው መግለጫ፤ በአውሮፓውያኑ 1994 ከተፈጸመው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት በኋላ አገሪቱ በኮንጎ ግዛት ውስጥ ሕገ ወጥ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ለማካሄድ ስትል ኃይሎችን እንዳሰማራች እና የታጠቁ ቡድኖችን እንደደገፈች ገልጻለች።
የኮንጎ የፍሕት ሚኒስቴር ጊዮም አንዳሊ፤ አገራቸው ዘር ማጥፋትን ለመከላከል፣ የዘር መድልዎ፣ የሴቶች መብት እና ስቅይትን የሚመለከቱ ስምምነቶች ላይ ተፈጽሟል ላሉት ጥሰት ተጠያቂነት እንዲሰፍን እየጠየቀች መሆኑን አርብ ዕለት ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ ሩዋንዳ ዴሞክተቲክ ኮንጎ ለመሠረተችው ክስ ምላሽ አልሰጠችም፤ ይሁን እንጂ አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አማጺ ቡድኖችን ትደግፋለች በሚል ለረጅም ጊዜ የሚቀርቡባትን ማስረጃዎች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
ሩዋንዳ፤ በምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰውን ኤም23 የተባለውን ዋነኛ ታጣቂ ቡድን ትደግፋለች የሚል ክስ ከሚያሰሙ አካላት መካከል የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች እና የምዕራባውያን መንግሥታት ይገኙበታል።
ኮንጎ ኔዘርላንድስ ውስጥ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ባቀረበችው ክስ፤ ሩዋንዳ እየፈጸመች ነው ያለቻቸውን ወንጀሎች እንድታቆም ትዕዛዝ እንዲሰጥ እና ለኮንጎ ባለሥልጣናት እንዲሁም ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፈል የሚያደርግ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍም ጠይቃለች።
ፍርድ ቤቱ አሁን የቀረበውን ክስ ይመረምራል። ኮንጎ በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ሩዋንዳ ላይ ክስ ስትመሠርት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።
በአውሮፓውያኑ 2001 የቀረበው የመጀመሪያውን ክስ ራሳቸው የኮንጎ ባለሥልጣናት አቋርጠውታል። 2006 ላይ የተመሠረተውን ክስ ደግሞ ሩዋንዳ ለፍርድ ቤቱ ሥልጣን ዕውቅና ስለማትሰጥ መቀጠል እንደማይችል ተገልጾ ውድቅ ተደርጓል።
ለአስር ዓመታት የቀጠለው የዴሞክራቲክ ኮንጎ ግጭት መነሻ በ1994 ከተፈጸመው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት የሚመዘዝ ነው።
በወቅቱ 800 ሺህ ገደማ በአብዛኛው ከቱትሲ ማኅበረሰብ የተገኙ ሩዋንዳውያን በሁቱ ጎሳ ጽንፈኞች ተጨፍጭፈዋል።
በቀል እንዳይፈጸምባቸው የፈሩ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሁቱዎች ድንበር ተሻግረው አሁን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተብሎ ወደሚጠራው ግዛት ገብተዋል። በዚህም በአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት የሚገኙት 'ባንያሙሊንጌ' የተባሉ የቱትሲ ቡድኖች ስጋት ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ይህም የጎሳ ውጥረቱ እንዲካረር አድርጓል።
የሩዋንዳ ጦር ለዘር ማጥፋት ወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑትን የተወሰኑ ግለሰቦችን ለመያዝ በሚል ሁለት ጊዜ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ወርሯል። ከባንያሙሊንጌ አባላት እና ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋርም ተባብሯል።
ከሁቱ ቡድኖች አንዱ የሆነው 'ዴሞክራቲክ ፎርስስ ፎር ዘ ሊብሬሽን ኦፍ ሩዋንዳ' የተሰኘ ቡድን አሁንም በምሥራቃዊ ኮንጎ ይንቀሳቀሳል። ከቡድኑ አባል መከካል የተወሰኑት በሩዋንዳው ዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ተጠያቂ ናቸው።
ሩዋንዳ ይህንን ቡድን "የዘር ማጥፋት ሚሊሻ" በማለት የምትገልጸው ሲሆን፣ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል መንቀሳቀስ መቀጠሉ ለግዛቷ አደጋ መሆኑን ትገልጻለች።
የኮንጎ ባለሥልጣናት ከዚህ ቡድን ጋር እየሠሩ እንደሆነ በመግለጽም ትከስሳለች። ኮንጎ ግን ይህንን ክስ ውድቅ አድርጋለች።
ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ታጣቂው ቡድን ኤም23 የምሥራቃዊ ኮንጎ ዋና ከተማ የሆነችውን ጎማን ጨምሮ በማዕድን የተበለጸጉትን በርካታ የአካባቢው ስፍራዎችን በተቆጣጠረበት ወቅት ግጭቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።
ሩዋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአሜሪካ አሸማጋይነት ታኅሣሥ ላይ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም አሁንም ውጊያ ቀጥሏል።