ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነትን ያስቆማል የተባለው ስምምነት ምን ምን ይዟል?
የአሜሪካ ባለሥልጣናት አገራቸው ከኢራን ጋር ከመግባባት ላይ የደረሰችበትን ሰነድ ይፋ አድርገዋል።
ስምምነቱ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እንደሚያደርግ እንዲሁም አራት ወራት የሚሞላውን የሁለቱን አገር ጦርነት ያስቆማል የሚል እምነት አሳድረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ባለ 14 ነጥቡ ስምምነት "በአፈጻጸም ላይ የተመሠረተ" መሆኑን ተናግረው ኢራን ልትጠቀም የምትችለው ስምምነቱን የምታከብር ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ስምምነቱን ሲፈርሙ የኢራኑ ፕሬዚዳንትም ፊርማቸውን ማኖራቸውን ቴህራን አስታውቃለች።
የስምምነቱ ነጥቦች ምን ምን ይዘዋል?
1: 'በሁሉም ግንባሮች" ጦርነትን ማቆም
የስምምነቱ የመጀመርያ አንቀጽ አሜሪካ፣ ኢራን እንዲሁም አጋሮቻቸው ወታደራዊ ዘመቻዎችን "አሁኑኑ እና በቋሚነት" ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ያቆማሉ ይላል።
ከአሜሪካ አንጻር ትራምፕ የእስራኤል ጦር በሄዝቦላህ ላይ በሚያካሄደው ዘመቻ ኣሌእ ኣላቸው ስጋት እየጨመረ የመጣ ሲሆን ከኢራን ጋር ያላቸውን ስምምነት ያበላሸዋል ብለው ይሰጋሉ።
ቴህራን በበኩሏ በተደጋጋሚ በስምምነቱ ውስጥ ሊባኖስ መካተቷን በማንሳት እርሱ እነዲከበር ጠይቃለች።
የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በሊባኖስ መቀጠሉ "የመግባቢያ ሰነዱ ጥሰትን" የሚያመለክት ሲሆን "አስፈላጊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ" ሲሉ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።
ስምምነቱ "ከአሁን በኋላ" ሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ ዘመቻዎችን እንደማይጀምሩ ወይም እርስ በእርሳቸው እንደማይታኮሱ እንዲሁም የሊባኖስን "የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት" እንደሚያረጋግጡ ይደነግጋል።
የመጨረሻው ስምምነት ግጭቱ በዘለቄታው እንዲቆም ያደርጋል የሚል ሃሳብ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
እስራኤል ለዚህ ጉዳይ ምን ምላሽ እንደምትሰጥ ግልፅ አይደለም።
2: 'የውስጥ ጉዳይን' ማክበር
በሰነዱ ላይ የሰፈረው ሁለተኛው ሃሳብ አሜሪካ እና ኢራን "የአንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ያከብራሉ" እንዲሁም እያንዳንዳቸው በሌላኛቸው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ይቆጠባሉ።
ይህ በኢራን ተቃዋሚ ቡድኖች ዘንድ ቅሬታ ሊፈጥር ይችላል።
በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ትራምፕ በኢራን ከተሞች በተቀጣጠለው የመንግሥት ተቃውሞ ወቅት ለሠልፈኞቹ "እርዳታ እየመጣ ነው" ሲሉ ቃል ገብተው ነበር።
3: የሚራዘም የ60 ቀን የጊዜ ገደብ
በሰነዱ ውስጥ በሦስተኛነት የተቀመጠው አሜሪካ እና ኢራን ቢበዛ በ60 ቀናት ውስጥ ምንም እንኳን ይህ የጊዜ ገደብ በጋራ ስምምነት ሊራዘም ቢችልም፣ ለመደራደር እና የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ይጥራሉ ይላል።
የ60 ቀናት የጊዜ ገደቡ የሚጀምረው የሁለቱ አገራት መሪዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ በጄኔቫ ሊካሄድ በታቀደው ሥነ ሥርዓት የመግባቢያ ሰነዱን በይፋ ሲፈርሙ ነው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጌይ "እስካሁን ድረስ የጄኔቫ ስብሰባ ዕቅዳችን አልተለወጠም" ብለዋል።
"የመግባቢያ ስምምነቱን በተመለከተ፣ የሁለቱ አገራት ፕሬዚዳንቶች እንዲፈርሙት ፍላጎት ያለ ሲሆን ይህም በአሁኑ ወቅት ግምገማ እየተደረገበት ነው።"
ሚኒስቴሩ በተጨማሪም በስምምነቱ መሠረት በ60 ቀናት ውስጥ "የመጨረሻ መግባባት" ላይ እንደሚደርስ አረጋግጧል።
4: አሜሪካ የጣለችውን እገዳ ታነሳለች
መግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ የአሜሪካ የባህር ኃይል በኢራን ወደቦች ላይ የጣለውን እገዳ "ማንኛውንም ሁከት ወይም እንቅፋቶች" ማስወገድ እንደሚጀምር አራተኛው ነጥብ ያስረዳል።
በስምምነቱ እና በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሠረት እገዳው ሙሉ በሙሉ በ30 ቀናት ውስጥ ያበቃል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች እንዲገቡ እና እንዲወጡ የምትፈቅዳቸው መርከቦች ብዛት ቴህራን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ውስጥ እንዲኖር በምትፈቅደው የትራፊክ ፍሰት መጠን ላይ ይወሰናል።
የመጨረሻው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ የአሜሪካን ኃይሎች ከኢራን አቅራቢያ ለማስወጣት ዋሺንግተን ገብቷል።
ይህም ማለት የአሜሪካ ጦር እንዲሁም መሣሪያዎቹ ከየካቲት 21 በፊት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወደ ነበሩበት ይመለሳሉ።
5: የሆርሙዝ ወሽመጥ
የስምምነቱ አካል እንደሚያመለክተው ስምምነቱ ሲፈረም ኢራን የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ውስጥ ያለምንም ክፍያ በሰላም እንዲያልፉ "የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ" ዝግጅት ታደርጋለች።
ይህ ጦርነት ከተጀመረበት እና የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ከተዘጋበት ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ በይፋ ስትናገረው የነበረው ግብ ሲሆን ይህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።
ሰነዱ እንደሚያመለክተው የመርከቦች እንቅስቃሴ "ወዲያውኑ" ይጀምራል፣ ይህም የቴክኒክ እና ወታደራዊ "እንቅፋቶችን" ማስወገድ እና የፈንጂ ማምከን ስራዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
ባለሥልጣናቱ ቀደም ሲል በሰጡት አጭር መግለጫ መርከቦች በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል ለሚያደርጉት ጉዞ ክፍያ እንደማይጠየቁ በተደጋጋሚ ግልጽ ለማድረግ ሞክረዋል።
በረጅም ጊዜ ውስጥ ሰነዱ እንደሚያመለክተው ኢራን ከኦማን እና ከሌሎች የባህረ ሰላጤ አገሮች ጋር የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል "ሰፊ" ስምምነት በማዘጋጀት ኣለይ ትሳተፋለች።
አሜሪካ ኢራን መብቷን "በኃይል" እንደምታረጋግጥ ታምናለች። ነገር ግን የባህረ ሰላጤው አገራት የክፍያ ስርዓት የሚኖርበትን መጪ ጊዜ "በፍፁም" እንደማይቀበሉት ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
6: ለኢራን መልሶ ግንባታ ገንዘብ
የስምምነቱ ስድስተኛ ነጥብ እንደሚያሳየው አሜሪካ እና ቀጣናዊ አጋሮች ቢያንስ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ለኢራን መልሶ ግንባታ እና የምጣኔ ሃብት ልማት የሚያገለግል"ግልጽ፣ በጋራ ስምምነት የተደረሰበትን" ዕቅድ ያዘጋጃሉ።
ሁለቱም አካላት ዝርዝሮቹን ከመጨረሻው ስምምነት በኋላ ባሉት 60 ቀናት ውስጥ ኣዘጋጃሉ። አሜሪካ ስምምነቱ ተግባራዊ አንዲሆን ይፋዊ የሆነ ማረጋገጫ ትሰጣለች።
ሆኖም ይህ ማለት አሜሪካ በገንዘብ ረገድ ትሳተፋለች ማለት አይደለም።
አንድ ባለሥልጣን አሜሪካ ለኢራን "ሰባራ ሳንቲም ገንዘብ" መክፈል ወይም ለገንዘቡ መዋጮ እንደማታደርግ ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ ለምሳሌ በማለት፣ ኢራን "ባህሪዋን ተገቢ ባህሪ የምታሳይ ከሆነ" የኤሚሬትስ ባለሥልጣናት በአሜሪካ ይሁንታ የተሰጠው በኢራን የኃይል ማመንጫ መገንባት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ሕዝብ ለኢራን በቀጥታ የሚከፈል ነገር እንደማይኖር ግልፅ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርገዋል።
7: ማዕቀቦች ያበቃሉ
አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን ማንኛውንም የኢኮኖሚ ማዕቀብ ታቋርጣለች፤ ይህም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች ውስጥ የተካተቱትን እና አሜሪካ ብቻዋን ተግባራዊ ያደረገቻቸውን ውሳኔዎችን ያካትታል።
የጊዜ ሰሌዳው ግን ግልጽ አይደለም።
ሰነዱ የጊዜ ሰሌዳው የመጨረሻው ስምምነት አካል ሆኖ ስምምነት እንደሚደረስበት ይገልጻል፤ ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች በቀጣይ ድርድሮች ጉዳዩን "ወዲያውኑ" ለመፍታት ያላቸውን ፍላጎት ይፋ አድርገዋል።
ኢራን በማዕቀቦች ክፉኛ ተጎድታለች፤ እናም አሜሪካ ኦፕሬሽን ኢኮኖሚክ ፊውሪ በሚል ባካሄደችው ዘመቻ ቴህራንን ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት ለማቆራረጥ ጥረት አድርጋለች።
8: የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች አይኖሩም
ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ላለመግዛት ወይም እንደማይኖራት ተስማምታለች። ሁለቱም ወገኖች ቴህራን አስቀድሞ ባላት የበለፀገ ዩራኒየም ላይ ለመደራደር ተስማምተዋል።
የተብላላውን ዩራኒየም የማስተዳደሪያ መንገዱ ግን ግልጽ አይደለም። ሰነዱ በቀጣዮቹ ውይይቶች ይህ "በጋራ ስምምነት ላይ እንደሚደርስበት" ይጠቅሳል። ነገር ግን ቢያንስ በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቁጥጥር እንደሚደረግበት እና ደረጃው ዝቅ እንደሚደረግ ይገልጻል።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ይህንን "ዝቅተኛ መስፈርት" እና ለአሜሪካ "ትልቅ ድል" ሲሉ ገልጸውታል።
ትራምፕ በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ዘመቻ ኤፒክ ፊውሪን እነደተጀመረ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳትታጠቅ መከላከል ከሚፈልጉት ነገር "99 በመቶ" እንደሆነ ተናግረዋል።
አሜሪካ ስምምነቱን በአፈጻጸም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ስለገለጸች፣ በአንቀጽ 7 ላይ የተገለጸው የማዕቀብ እፎይታ ከ8ኛው ነጥብ ጋር የተቆራኘ ነው።
9 እና10: ባለበት የሚቆመው የኒውክሌር ፕሮግራም
አሜሪካ እና ኢራን የኒውክሌር ጉዳይን ለአሁኑ "ባለበት ለማቆየት" ተስማምተዋል። ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ባለበት ለማቆየት የተስማማች ሲሆን ሁለቱም ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ የተብላላው ዩራኒየም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ወደፊት የሚነጋገሩበት ይሆናል።
በተግባር ይህ ማለት አሜሪካ አዲስ ማዕቀቦችን አትጥልም ማለት ነው። እስከዚያው ድረስ፣ እንደ የባንክ ግብይቶች እና ትራንስፖርት ያሉ የነዳጅ፣ የነዳጅ ምርቶች እና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ለኤክስፖርት ይሁንታዋን ትሰጣለች።
11: እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ ሃብቶች
ይህ ነጥብ ለድርድሩ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
ኢራን እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ ሃብቶቿ እንዲለቀቁ ለረዥም ጊዜ አጥብቃ ስትጠይቅ ቆይታለች፤ ይህም ለአገሪቱ ሌላ የኢኮኖሚ ኅልውና ይሰጣል።
የሰነዱ አስራ አንደኛው ነጥብ እንደሚያመለክተው የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ እና በድርድሩ ወቅት በሂደቶቹ ላይ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ አሜሪካ "የተከለከሉ ወይም የታገዱ ሃብቶችን ሙሉ በሙሉ ትለቅቃለች"።
አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከስምምነቱ በኋላ በሚደረጉ ውይይቶች ኢራን ያበለፀገችውን ዩራኒየምን በሚመለከት ስትስማማ እንደማበረታቻ ሃብቶቿ ቀስ በቀስ እንደሚለቀቁ ተናግረዋል።
12-14 : ቁጥጥር እና የመጨረሻው ድርድር
የሰነዱ የመጨረሻዎቹ ጥቂት ነጥቦች ስምምነቱ እንዴት እንደሚካሄድ የሎጂስቲክ ዝርዝር ያቀርባሉ።
አሜሪካ እና ኢራን የስምምነቱ ተግባራዊነት እና አፈጻጸም ለመከታተል፣ ምንም እንኳን ይህ በተግባር ምን እንደሚመስል ግልጽ ባይሆንም "ስርዓቶችን" እንደሚያደራጁ ይጠቅሳሉ።
ከዚያም ስምምነቱ ከተፈረመ እና ተግባራዊነቱ ከተጀመረ በኋላ አሜሪካ እና ኢራን የመጨረሻ ስምምነት ለማድረግ ድርድር ይጀምራሉ።
በመጨረሻም የመጨረሻው የስምምነት ሰነድ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚጸድቅ ይገልጻል።