አሜሪካ በኢራን ላይ ባካሄደችው ጦርነት ምን ያህል ቢሊዮን ዶላሮች አወጣች?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ማለዳ ቅዳሜ እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እና ቁልፍ የአመራር እና ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ ነበር ጦርነቱን የጀመሩት።

በመጀመሪያው ዕለት በኢራን ላይ በተፈጸሙት የተቀናጁ የአውሮፕላን እና የሚሳዔል ጥቃቶች የእስላማዊቷን አብዮታዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የበላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

ይህንን ተከትሎም ለወራት በሕዝባዊ ተቃውሞ ሲናጥ የነበረው የኢራን መንግሥት እንዳበቃለት በስፋት እየተነገረ የነበረ ቢሆንም፣ እጇን ያልሰጠችው ኢራን የአጸፋ ምላሽ መስጠት የጀመረችው ወዲያው ነበረ።

ለዘመናት የገነባቻቸው ዘመናዊ የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎቿን በመጠቀም በእስራኤል እና በዙሪያዋ ባሉ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ለቀናት አዝንባለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን ጋር የሚካሄደው ጦርነት ከሳምንታት የማያልፍ አጭር ጦርነት እንደሆነ እና ኢራንም በቶሎ እጅ እንድትሰጥ በመጠየቅ ሠራዊታቸው ለድል መቃረቡን አሳውቀው ነበር።

ነገር ግን በጦርነት እና በድርድር ውስጥ ሳትበገር የቆየችው ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በአሜሪካ እና በአካባቢው አገራት እንዲሁም በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከባድ ተጽእኖን ማሳደር ችላለች።

ግዙፍ የጦር መርከቦቿን በማሰማራት ቀደም ብላ ቬንዙዌላ ላይ የወሰደችውን እርምጃ በኢራን ላይ ለመድረገም የተነሳችው አሜሪካ የገጠማት ምላሽ ከጠበቀችው በላይ ነበር።

በሳምንታት ይጠናቀቃል የተባለው ጦርነት እየተራዘመ ሲሄድ ለድርድር በሯን በመክፈት ቅድመ ሁኔታዎችን ብታቀርብም በኢራን በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቶ ነበር። በፓኪስታን አሸማጋይነት ለወራት የተካሄደው ንግግር አሁን ወደ መግባባት እንዳደረሳቸው የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ይህ ዓለምን ለወራት ያስጨነቀው ጦርነት ወደ መቋጫው የደረሰው ግን በቀላል ዋጋ አይደለም።

እስካሁን በኢራን በኩል ለጦርነቱ የወጣው የገንዘብ መጠን ባይታወቅም አሜሪካ ግን ባለፉት ሦስት ወራት ቢሊዮኖችን ለጦርነቱ ከስክሳለች። በተጨማሪም የጦርነቱ ዳፋ ሌሎች ቢሊዮኖችን እንዳከሰራት ይነገራል።

ባለፉት ወራት ከተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት ይፋዊ ምንጮች የወጡ አሃዞች እንዳመለከቱት በኢራን ላይ ለተካሄደው ጦርነት በቀጥታ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲባል አሜሪካ በየወሩ ከ6 አስከ 8 ቢሊየን ዶላር ድረስ ስታወጣ ቆይታለች።

ገለልተኛ የምጣኔ ሀብት ትንተናዎች ደግሞ አገሪቱ ባለፉት ወራት በተካሄደው ጦርነት ለወታደራዊ የወጣው ወጪ እና ጦርነቱ በሰፊው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከ15 አስከ 30 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ኪሳራን አስከትሏል ብለው ያምናሉ።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ለጦርነቱ ያስቀመጠው መነሻ ወጪ በወር በአማካኝ 6.8 ቢሊየን ዶላር ነው። ከፍተኛውን ወጪ የሚይዘው ደግሞ አሜሪካ በኢራን ላይ በስፋት የተጠቀመቻቸው እጅግ ዘመናዊ የሆኑትን የሚሳዔል አረሮችን ለመተካት የወጣው ነው።

ለምሳሌም ቶምሀውክ የሚባለውን ተወንጫፊ ሚሳዔል ለማምረት እና ለመተኮስ እያንዳንዱ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ይጠይቃል።

እንደ ሐርቫርድ የኬኔዲ የምጣኔ ሀብት ኮሌጅ ግምት ደግሞ እስካሁን ለጦርነቱ የወጣውን ገንዘብ በእጅጉ ያንረዋል። በዚህም መሠረት ጦርነቱ በተጀመረባቸው ቀናት ውስጥ እና በተባባሰባቸው ጊዜያት የአሜሪካ የጦርነት ወጪ በቀን ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ እንደሆነ ጠቅሷል።

አስካሁን በተጨባጭ በኢራን ላይ የተካሄደው ጦርነት ያስወጣው ወጪ ይህ ነው ተብሎ በትክክል ባይረጋገጥም የተለያዩ ተቋማት ግን ከተጠቀው ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ እያመለከቱ ነው።

ለሳምንታት ብቻ ይቆያል የተባለው ጦርነት እየተራዘመ መሄዱን ተከትሎ የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት በወጪው ላይ ጫና ስለተፈጠረበት የአገሪቱ ምክር ቤት ተጨማሪ የ98 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ በጀት እንዲለቅለት ጥኣቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

እስካሁን እየተጠቀሱ ያሉት በቢሊዮን ዶላሮች የሚገለጹት የጦርነቱ ወጪዎች ለተተኳሾች፣ ለአየር ጥቃት መከላከያ ሚሳዔሎች፣ ለጦር መሳኢያዎች ጥገና እና ለዕለት ለዕለት ወታደራዊ ዘመቻዎች የሚውሉ ወጪዎች መሆናቸው ይታመናል።

በይፋ ያልተገለጹ ውስጣዊ የአሜሪካ መከላከያ ግምቶች በኢራን ጥቃት እና በጦርነቱ ሂደት ውስጥ የወደሙ አውሮፕላኖች እንዲሁም በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ ያሉ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የደረሱ ጉዳቶች ከወጪው ውስጥ ሲካተቱ ገንዘቡ ወደ 50 ቢሊየን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል።

ከወታደራዊው ወጪ ባሻገር አሜሪካ በኢራን ላይ ያካሄደችው ጦርነት በአሜሪካውያን የዕለት ከዕለት ሕይወት ላይም ከፍተኛ ጫናን ማሳደሩ እየተነገረ ነው።

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ውስጥ በተፈጠረው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ዜጎች 27.8 ቢሊዮን ዶላር ያህል ለነዳጅ እና ጋዝ ጨማሪ ገንዘብ አውጥተዋል። በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በአማካኝ በ40 በመቶ አሜሪካ ውስጥ ጭማሪ አሳይቷል።

አሁን አሜሪካ እና ኢራን ቢሊዮኖችን ያስወጣውን ጦርነት ለማቆም ከስምምነት ደርሰዋል። ምንም እንኳን ጦርነቱ ቢቆምም የጦርነቱ ዳፋ የወጪ ግን ቀጣይነት እንደሚኖረው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ገለልተኛ የምጣኔ ሀብት እና የገንዘብ ባለሙያዎች የተጓደሉ የጦር መሳሪያ እና የተተኳሾች ክምችትን መልሶ ማሟላትን እና በጦርነቱ የተጎዱ የሠራዊት አባላትን መንከባከብን ጨምሮ የአሜሪካ ጦር ዘላቂ ወጪዎች ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚፈልጉ ይገምታሉ።

በኢራን በኩል በአሜሪካ እና በእስራኤል በመሠረተ ልማቶቿ ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ውድመት የደረሰባት ከመሆኑ አንጻር እና ከተጠቀመቻቸው ረጅም ርቀት ሚሳዔሎች እና ድሮኖች አንጻር ለጦርነቱ ከፍተኛ ወጪ እንዳወጣች ቢገመትም ተጨማባጭ መንግሥታዊም ሆነ የባለሙያዎች ግምት አልተገኘም።