ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው ዕውቅና ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ባላት ሚና ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?
የእስራኤል እና የሶማሊላንድ ግንኙነት ባለፉት ወራት ከዕውቅና ባሻገር እየተጠናከረ ነው። እስራኤል ኤምባሲዋን ሐርጌሳ ውስጥ ወዲያውኑ የከፈተች ሲሆን፣ ሶማሊላንድ ደግሞ በዚህ ሳምንት ኢምባሲዋን ኢየሩሳሌም ውስጥ ከፍታለች።
እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው ዕውቅና ሶማሊያን ያስቆጣ ሲሆን፣ በአፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያላት ቻይናንም አሳስቧታል። ቻይና እንደተገንጣይ ግዛቷ ከምትቆጥራት ታይዋን ጋር ግንኙነት ያላት ሶማሊላንድ የሶማሊያ አካል እንደሆነች ነው የምታምነው።
ይህ የእስራኤል ዕውቅና ለታይዋን የልብ ልብ ይሰጣታል የሚል ስጋት ያላት ቻይና፤ ሶማሊላንድ እንደ አገር መታወቋ ቻይና በአፍሪካ ባላት እንቅስቃሴ እና ጥቅም ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል በማሰብ በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተነስታ ነበር።
እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ አገር ከሆነች ከአጭር ጊዜ በኋላ፤ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፤ ጥር ላይ ወደ ሶማሊያ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ በድንገት ማራዘማቸው በአፍሪካ ቀንድ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት እና የደኅንነት ስጋት ፈጥሯል።
ይህንን ተከትሎ የቻይና፣ የሶማሊላንድ፣ የታይዋን እና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች፤ ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ላይ ውዝግብ ውስጥ ቆይተዋል።
የቻይና ኤምባሲ የኤክስ ገጽ፤ ቤይጂንግ ሶማሊያ ውስጥ ለተካሄደው ሶማሊላንድን የሚቃወም ሰልፍ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን የሰረዙት ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው መባሉን ሲያስተባብል ተስተውሏል።
ቻይና፤ ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ ሶማሊላንድ ላይ ለምታነሳው የባለቤትነት ጥያቄ ድጋፏን ስትገልጽ ቆይታለች።
በአንጻሩ ደግሞ ሶማሊላንድ እና ታይዋን የሚያደርጉትን "የጥምረት" እንቅስቃሴ ትቃወማለች። ቻይና ተቃውሞዋን ብትገልጽም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእስራኤል፣ በታይዋን እና በሶማሊላንድ መካከል ያለው ግንኙነት እየጠበቀ መጥቷል።
እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው እውቅና እንዲሁም አሜሪካን ከጎኗ በማሰለፍ እያሳደገች የመጣችው በቀጣናው የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በቻይና መገናኛ ብዙኃን እና ጦማሪዎች ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ይህ የእስራኤል እንቅስቃሴ ወሳኝ ለሆነው የቻይና የቀይ ባሕር ስዊዝ ቦይ የመርከብ ንግድ መስመር እንዲሁም በጂቡቲ ለሚገኘው የቻይና የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ስጋት ሊፈጥር ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ቻይና ታይዋን ላይ ለምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ ፈተና አድርጋ ልትመለከተው ትችላለች።
ቻይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ጉዞ ስለመራዘሙ ምን አለች?
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከታኅሣሥ 29 እስከ ጥር 12/2018 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያን፣ ታንዛኒያን እና ሌሶቶን እንደሚጎበኙ መሥሪያ ቤታቸው አስታውቆ ነበር። ላለፉት 36 ተከታታይ ዓመታት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት የሚያደርጉት የመጀመሪያ የውጭ ጉዞ መዳረሻ አፍሪካ ሆና እንደምትቀጥል በዚህ መግለጫ ላይ ተጠቅሶ ነበር።
"ጓንቻ" የተሰኘው በከፊል ከመንግሥት ጋር የተገናኘው የዜና ምንጭ በወቅቱ ባወጣው ዘገባ ዋንግ ወደ ሶማሊያ የሚጓዙት "አሳሳቢ በሆነ ወቅት" እንደሆነ ጠቁሞ ነበር። እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና የሰጠችው በዚያው ታኅሣሥ ወር ነበር።
የዜና ምንጩ ዘገባ፤ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሞቃዲሾ ጉዞ "ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር" ያለመ እንደሆነ አድርጎ ነበር ያቀረበው።
በመንግሥት የሚመራው 'ቤይጂንግ ዴይሊ' ጋዜጣ ደግሞ ማ ሃንዚን የተባሉ ምሁን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፤ የዋንግ ጉብኝት "ቻይና የሶማሊያን ሉዓላዊነት፣ ደኅንነት እና የልማት ጥቅምን ለማስከበር የምታደርገውን ጽኑ ድጋፍ በተመለከተ... ዋነኛ እና ወሳኝ ፖለቲካዊ መልዕት" እንደሚያስተላልፍ አስነብቦ ነበር።
ቻይና "ማንኛውም ዓለም አቀፍ ኃይል የሶማሊላንድን ጉዳይ ወይም ሌሎች መንገዶችን ተጠቅሞ በአፍሪካ አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደርገውን ሙከራ በግልጽ እንደምትቃወምም" ያሳያል ብሎ ነበር ዘገባው።
ይሁን እንጂ ዋንግ ወደ ሶማሊያ ሳይጓዙ ቀርተዋል። በሶማሊያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ጥር ባወጣው መግለጫ፤ ጉብኝቱ የተራዘመው "በፕሮግራም ለውጥ" ምክንያት እንደሆነ ገልጿል። መግለጫው ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።
የቻይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችም የኤምባሲውን መግለጫ የተከተሉ ነበሩ። ቻይና የደኅንነት ስጋት ምክንያት ስለመሆኑ ጉዳዮች ጥያቄ ቢቀርብላትም የሰጠችው ምላሽ ተመሳሳይ ነው።
ያልተረጋገጡ ምንጮችን የጠቀሱት የታይዋን መገናኛ ብዙኃን በአንጻሩ፤ ጉብኝቱ የተሰረዘው በእስራኤል የሚደገፍ ገለልተኛ ታጣቂ ቡድን ሞቃዲሾ ውስጥ በፈጠረው የቦምብ ጥቃት ስጋት ምክንያት እንደሆነ ዘግበዋል።
የኤምባሲው መግለጫ በበኩሉ ቻይና ከሶማሊያ ጋር ላላት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ እንዲሁም "ሉዓላዊነቷን፣ አንድነቷን እና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ የምታቀርበውን ትክክለኛ ጥያቄ" እንደምትደግፍ በአፅንዖት አስረድቷል።
በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃን፤ ዋንግ እና የሶማሊያ አቻቸው ጥር 3 ቀን ያደረጉትን የስልክ ውይይት እና በጋራ ያወጡትን መረጃም በዘገባቸው አንስተዋል። በዚህ የስልክ ንግግር፤ ቻይና እና ሶማሊያ ጋር ያላቸው ስትራቴጂያዊ አጋርነት "በጊዜያዊ ኹነቶች" ተጽዕኖ እንደማይደርስበት እና ሶማሊላንድ እና ታይዋን "ነጻነትን ፍለጋ" የሚያደርጉትን "ጥምረት" እንደሚቃወሙ አስረግጠዋል።
የዲፕሎማቶች የማኅበራዊ ሚዲያ ውዝግብ ምን ነበር?
ቻይና እና ታይዋን እንዲሁም ቻይና እና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ባላንጣነት እየታየ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ የዋንግ ዪ በአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሊያደርጉት የነበረው የሶማሊያ ጉብኝት በድንገት መራዘም የኤክስ ተጠቃሚ የሆኑ የቻይና፣ የታይዋን፣ የሶማሊላንድ እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አነታርኳል።
ውዝግቡ የጀመረው የሶማሊላንድ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ከድር ሁሴን አብዲ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝታቸውን እንዲያራዝሙ ስላደረጋቸው ጉዳይ በገጻቸው ሲለጥፉ ነው። የሶማሊላንዱ ሚኒስትር ያጋሩት የቻይና "ኦፊሴላዊ ጋዜጣዊ መግለጫ" የሚመስል ምሥል፤ ዋንግ ጉብኝታቸውን ያራዘሙት "በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት" ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል።
የሶማሊላንዱ ባለሥልጣን፤ "ሶማሊያ የራሷን እንግዳ ደኅንነት እንኳ ማረጋገጥ አትችልም" ሲሉ ተሳልቀዋል። ሶማሊያ ዋና ከተማዋን እና አገሪቱን በማረጋጋት ላይ ማተኮር አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሶማሊላንድ "ደኅንነቷ የተጠበቀ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሁን ደግሞ በመጨረሻም ዕውቅና ያገኘች" እንዲሁም "ጠንካራ ወዳጆች እና አጋሮች" ያሏት መሆኗን ገልጸዋል።
በሶማሊያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በፍጥነት ባወጣው የምላሽ መግለጫ፤ ልጥፉ "ሐሰተኛ"መሆኑን አስታውቋል። "የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻ አካል የሆነ አሳፋሪ ፈጠራ" ብሎታል።
በተጨማሪም ኤምባሲው፤ የሶማሊላንድ እና የእስራኤል ግንኙነትን በተመለከተ "ሕዝባዊ ተቃውሞ" እንዳለ ለማሳየት በማሰብ የሚደረጉ ፀረ ሶማሊላንድ ተቃውሞዎችን በገንዘብ ሲደግፍ ነበር በሚል የቀረበውን ውንጀላ ተቃውሟል። "አስነዋሪ የሐሰት መረጃ" ሲልም አጣጥሎታል።
ታይዋን፣ ሶማሊላንድ እና እስራኤል እንዴት ተቀራረቡ?
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ውሱን ዕውቅና ያላት ታይዋን፤ በተመሳሳይ መልኩ የዕውቅና ጉዳይ ከሚያሳስባት ሶማሊላንድ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መሥርታለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሁለቱ ግዛቶች ይበልጥ ወደ እስራኤል እና አሜሪካ እየተጠጉ ነው።
ታይዋን እና ሶማሊላንድ በአውሮፓውያኑ 2020 አንዳቸው በሌላኛቸው ዋና ከተማ ዲፕሎማሲያዊ ተወካይ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍተዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ እንደ ጤና፣ ግብርና እና ደኅንነት ባሉ የተለያዩ ዘርፎች ትብብራቸውን አጠናክረዋል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህማን ዳሂር አደም ባካል በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2025 ወደ ታይዋንን በተጓዙበት ወቅት የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ፤ የሰው ኃይል ልውውጥን፣ ሥልጠናን እና የባሕር ላይ ነፍስ አድን አቅምን ለማጠናከር ያለመ ነው። "ተመሳሳይ ምልከታ ያላቸውን ሁለቱን ዲሞክራሲያዊ አጋሮች" ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የማስፋት ግብ እንዳለውን ተገልጿል።
የታይዋን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ላይ ቺንግ ቴ በበኩላቸው፤ እንደ አሜሪካ ካሉ ተመሳሳይ ምልከታ ካላቸው አገራት ጋር በመሆን "ከቻይና ነጻ የሆነ የሶማሊላንድ የባሕር ዳርቻ " በጋራ የመፍጠር ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጨምረውም "አምባገነኑ" ያሉት የቻይና መንግሥት ታይዋን እና ሶማሊላንድን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለመገደብ የሚያደርገውን ጫና አጠናክሯል ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በተለይም የጋዛ ጦርነትን ተከትሎ እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ መገለል እየጨመረ ከመጣ በኋላ ታይዋን እና እስራኤል ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ነው።
በእስራኤል የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ፤ ባለፉት ዓመታት በርካታ ልዑካንን ይዘው ወደ ታይዋን የተጓዙትን የእስራኤል የፓርላማ አባል ቦአዝ ቶፖሮቭስኪን በብርቱ ተችቷል። የፓርላማ አባሉ ጉብኝት በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች፣ በዲጂታል ደኅንነት እንዲሁም በአዳዲስ የመከላከያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነበር።
የታይዋን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዉ ቺህ ቹንግም በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2025 በምሥጢር ወደ እስራኤል በመጓዝ፤ "ቲ-ዶም" ስለተባለው የአየር መከላከያ ፕሮጀክት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያዩ ተዘግቧል።
የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዞ የተሰማው፤ የታይዋን ፕሬዝዳንት ከእስራኤሉ 'አይረን ዶም' ጋር የሚመሳሰል የመከላከያ ሥርዓት ታይዋን የመሥራት ዕቅድ መንደፏን ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።
ውጥረቶች ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ፍላጎት ላይ እንዴት ተጽዕኖ ያሳድራል?
እስራኤል እና ታይዋን ከሶማሊላንድ ጋር ጥልቅ ግንኙነት እየመሠረቱ እንዲሁም አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማሳደግ ማሳደሯን ተከትሎ፤ ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ይበልጥ ውስብስብ ሁኔታ እየገጠማት ነው።
'ጓንቻ' የቻይና መገናኛ ብዙኃን ባወጣው ዘገባ፤ የአደን ባሕረ ሰላጤ ቀይ ባሕር እና የስዊዝ ቦይን በማገናኘት ረገድ ያለውን ወሳኝ የባሕር መተላለፊነት ጠቅሷል። በቻይና እና በአውሮፓ መካከል "ቁልፍ የንግድ ኮሪደር" መሆኑን አክሏል።
ከመንግሥት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ጦማሪዎች በበኩላቸው፤ ቻይና ከሱዳን ሰሊጥ እና ጥጥ ለማስገባት እንዲሁም ማሽነሪዎችን እና መሣሪያዎችን ወደ አፍሪካ ለመላክ በዚህ የንግድ መስመር ላይ በከፍተኛ መጠን ጥገኛ መሆኗን አንስተዋል።
ቤይጂንግ ዴይሊ ጋዜጣ ደግሞ ባለሙያዎችን ተቅሶ ባወጣው ዘገባ፤ እስራኤል ሶማሊላንድ ውስጥ የጦር ሠፈሮችን በማቋቋም፤ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ወታደራዊ አቅም በእጅጉ ለማሳደግ ማቀዷን ገልጿል።
ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የሚተነትኑ የቻይና ጦማሪዎች ደግሞ፤ በውጭ አገር ያለ ብቸኛው የቻይና የጦር ሠፈር በሆነው እና የቀይ ባሕር-ስዊዝ ቦይ የመርከብ መስመር ላይ ቁጥጥር በሚያደርገው በጂቡቲ የሚገኘው የኔጂንግ ባሕር ኃይል ሰፈር ላይ ሊደቀን የሚችለውን ስጋት አመልክተዋል።
እስራኤል፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ብሪታንያ እና ምናልባትም አሜሪካ፤ በጂቡቲ ከሚገኘው የቻይና ጦር ሰፈር 306 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሶማሊላንድ በርበራ ወደብ ላይ የሚያደርጉትን ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሊያሳድጉ እንደሚችሉ አብራርተዋል።
ወደቡ የአሜሪካን ወታደራዊ ካምፕም ሊይዝ እና በዚህ አማካኝነትም ዋሽንግተን የቻይናን የባሕር ኃይል እንቅስቃሴ በክትትሏ ስር ልታደርግ እንደምትችል ገልጸዋል። ይህ እርምጃ ወሳኝ በሆነው በዚህ የባሕር መስመር ላይ ቻይና ያላትን መተላለፊያ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችልም አክለዋል።
በተጨማሪም ከምዕራባውያን የሚገኝ ገንዘብን በመጠቀም በርበራ ሊለማ እና ጂቡቲ ሊተካ ይችላል የሚል ስጋት አንስተዋል። ይህም ቻይና በምሥራቅ አፍሪካ የያዘቸውን የሎጂስቲክስ ማዕከልነት ስፍራ እንደሚያዳክመው ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ማዕከል የሆነችውን ኢትዮጵያን ከአደን ባሕረ ሰላጤ ጋር የሚያገናኘው እና በቻይና የተገነባው የአዲስ አበባ-ጅቡቲ ባቡር መስመር በአውሮፓውያኑ 2018 መጠናቀቁ የቻይናን በቀጣናው ያላትን አቋም አጠናክሮ ማቆየቱንም አስታውሰዋል።
ተንታኞቹ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ ኹነቶችን የሚመለከቷቸው በአሜሪካ እንደሚካሄድ ስትራቴጂክ እርምጃዎች አድርገው ነው። አሜሪካ፤ እስራኤል ለሶማሊላንድን የመጀመሪያውን ዕውቅና እንድትሰጥ በማድረግ ሐርጌሳን የፀረ-ቻይና እና የፀረ-ሩሲያ ስትራቴጂ አካል ለማድረግ እየጣረች እንደሆነ ያምናሉ።
በተጨማሪም ሁለቱ አገርነታቸውን ያወጁ ተገንጣይ ግዛቶች አንዳቸው ለሌላኛቸው የሚሰጡትን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በመጠቀም ቻይና ታይዋን ላይ የምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ ላይ ፈተና ለመደቀን እየሞከረች ነው የሚል ትንተናቸውን አቅርበዋል።