በአሜሪካ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ባለበት ወቅት ትራምፕ "የዋጋ ግሽበቱን ወድጄዋለሁ" አሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የዋጋ ጭማሪ ባለፈው ሦስት ዓመት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በናረበት ወቅት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "የዋጋ ግሽበቱን እወደዋለሁ" አሉ።

የአሜሪካ መንግሥት ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በግንቦት ወር 4.2 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።

በሚያዚያ ወር የኢራን ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ በመታየቱ የዋጋ ጭማሪው 3.8 በመቶ ከፍ ብሎ ነበር።

ትራምፕ በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች "እወደዋለሁ። ቁጥሮቹ በጣም አሪፍ ነበሩ። ለምን እንደምወደው ታውቃለህ? የዋጋ ግሽበት እወዳለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከኢራን ጋር የተጀመረው ጦርነት ሲቆም ዋጋው በፍጥነት እንደሚቀንስ ቃል ገብተዋል።

የአሜሪካ ጦር በኢራን የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን ቀጥሏል።

ረቡዕ ዕለት በዋጋ ግሽበቱ ላይ አስተየየት የሰጡት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ መከላከያ ኃይል "በሚሊዮን በርሜሎች የሚቆጠሩ የኢራን ነዳጅ ዘይት" ለመውሰድ በምሽት ዘመቻ ማካሄዱን ተናግረው፤ ይህም ዋጋ በተወሰነ መልኩ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አብራርተዋል።

"ይህ ግጭት ሲያቆም . . . የነዳጅ ዋጋ ከዚህ ቀደም ወደነበረበት ሲቀንስ ታያላችሁ" ሲሉ በዋይት ሐውስ ለተሰበሰቡ ጋዘዜጠኞች ተናግረዋል።

የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት አሁንም ከኢራን ጦርነት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጠ ነው።

ትራምፕ በኋላ ላይ ለኒውዮርክ ታይምስ በሰጡት አስተያየት ንግግራቸው ከአውድ ውጪ መወሰዱን ተናግረው ማለት የፈለጉት የዋጋ ግሽበቱ "ከተጠበቀው በጣም ዝቅ ያለ" እንደሆነ አብራርተዋል።

ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ የሸማቾች ዋጋ ጠቋሚ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን የመዘገበ ሲሆን ይህም ከኢራን ጦርነት በኋላ የዋጋ ንረቱ የእያንዳንዱን ኪስ የበለጠ እንዲያንኳኳ ማድረጉን ያሳየ ነው ተብሏል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም የዋጋ ግሽበቱ ጊዚያዊ መሆኑን ተናግረው ጦርነቱ እንደቆመ እንደሚቀንስ ቃል ገብተው ነበር።

የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት በጆ ባይደን ሥልጣን ዘመን ከነበረው 9.1 በመቶ ዝቅ ያለ ነው።

ነገር ግን አሜሪካ የማሟያ ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት ትራምፕ ላይ ፖለቲካዊ ጦስ ይዞ መምጣቱ አይቀርም።

ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሲኖር የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት ለሚገዛቸው ሰነዶች ከፍተኛ ወለድ እንዲከፍል ስለሚገደድ በምጣኔ ሃብቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ይህም የመንግሥትን ወጪ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ኢኮኖሚው ላይም ጫና ይፈጥራል።

በአሜሪካ የነዳጅ እና ኢነርጂ ዋጋ ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በግንቦት ወር ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ፔትሮሊየም ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

ሁለቱ አገራት ወደ ሰላም የመምጣት ዕድላቸው ዕለት በዕለት እየተመናመነ መምጣቱን በመጥቀስ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል።