ፈረንሳይ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ የሚያግድ ሕግ አጸደቀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግደው ሕግ በፈረንሳይ ምክር ቤት ጸደቀ።

ሕጉ ከቀጣይ ዓመት ታኅሣሥ ጀምሮ የሚተገበር ሲሆን፤ እርምጃውን በመውሰድ ፈረንሳይ በአውሮፓ የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች።

በሕጉ መሠረት ፈረንሳይ ውስጥ ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም የዕድሜ ማረጋገጫ ማስገባት አስፈላጊ ይሆናል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አውሮፓ ኅብረት የታዳጊዎችን አእምሯዊ ጤና ለመጠበቅ ተመሳሳይ ውሳኔዎች አሳልፈዋል።

የሥልጣን ዘመናቸው እየተገባደደ ያለው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሕጉን መጽደቅ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የሕጉ ተግባራዊነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ቢኖሩም የተጠቃሚዎችን ዕድሜ ለማረጋገጥ የተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ መንግሥት ገልጿል።

ከፊታችን መስከረም ጀምሮ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች የዕድሜ ማረጋገጫ ሳይሰጡ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ መክፈት አይችሉም። ከታኅሣሥ በኋላ ደግሞ ሁሉም ፈረንሳውያን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ መሆኑን የግድ ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

ሕጉ መተግበር ሲጀምር የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የፈረንሳይ መንግሥት ያስቀመጠውን የዕድሜ ማረጋገጫ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፤ ከግል መረጃ ጥበቃ እና ከዕድሜ ማረጋገጫው አስተማማኝነት አንጻር ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ ታዳጊዎች ክልከላውን በቀላሉ ማለፍ እንደሚችሉም እየተገለጸ ነው።

የፈረንሳይ ዲጂታል ሚኒስትር አን ለ ሄናንፍ "የዕድሜ ማረጋገጫ መንገዶች አሁንም አሉ" በማለት የሕጉ ትግበራ ላይ የተነሱ ትችቶችን አስተባብለዋል።

ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ በማገድ የመጀመሪያዋ አገር አውስትራሊያ ናት።

ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ላይ ክልከላ ቢጣልም አሁንም ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም መቀጠላቸውን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

የአውስትራሊያ የበይነ መረብ ደኅንነት ኮሚሽን እንዳለው፤ ከክልከላው በፊት ከ16 ዓመት በታች ከሆኑ 10 ታዳጊዎች ሰባቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ይጠቀሙ ነበር። አሁንም "የተወሰነ የማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሽነት" እንዳለ ገልጿል።

በከርቲን ዩኒቨርስቲ የበይነ መረብ ጥናት ባለሙያ ታማ ሌቨር ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የአውስትራሊያ ዕግድ ከቴክኒክ አንጻር "የከሸፈ" ነው።

ሆኖም ግን የተለያዩ መንገዶች በመሞከር ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ታዳጊዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ክልከላ ውይይት "በማሳተፍ" የተሻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ይናገራሉ።

ፈረንሳይ የዕድሜ ማረጋገጫውን ለሁሉም ዜጎች ለመተግበር ማሰቧ የክልከላውን ውጤታማነት ሊያረጋግጥ ቢችልም፤ ከግል መረጃ ጥበቃ አንጻር ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በሌላ በኩል ክልከላው ታዳጊዎችን እምብዛም ወደማይታወቁ እና የበለጠ አደገኛ ወደሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ሊገፋቸው ይችላል የሚል ስጋት አለ።