ኳታር በኢራን ለተፈጸመባት ጥቃት ካሳ እንዲከፈላት ጥያቄ አቀረበች
ኳታር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ኢራን በግዛቷ ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ሙሉ ተጠያቂ መሆኗን ገልጻ ለደረሰባት ውድመት የካሳ ጥያቄ አቀረበች።
ኳታር በደብዳቤዋ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የነዳጅ ጫኝ መርከቧን ዒላማ ማድረጓን እንዲሁም ከዚያ በኋላ በሁለት የተለያዩ ቀናት ደግሞ በግዛቷ ላይ የሚሳዔል ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች።
የኳታር ባለሥልጣናት ኢራን በአገራቸው ላይ ከሳምንት በፊት የፈጸመችውን የሚሳዔል ጥቃት ተከትሎ ለማክሸፍ በተደረገው ጥረት መካከል ፍንጣሪዎች በመኖሪያ ስፍራ በመውደቃቸው አንድ ሕጻንን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ተጎድተዋል ብለዋል።
ደብዳቤው ጨምሮም ኢራን በኳታር ግዛት ላይ የፈጸመችው “የጠብ ጫሪነት ጥቃት” የአገሪቱን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ እና ለደኅንነቷ እንዲሁም ለግዛት አንድነቷ ቀጥተኛ ስጋት ነው በማለት አውግዞታል።
ኳታር “ሉዓላዊነቷን፣ ደኅንነቷን እና የዜጎቿን ሕይወት ለመካከል ማንኛውንም ዓይነት አስፈላጊ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማትል” አሳውቃለች።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚካሄደው ጦርነት መልሶ ካገረሸ በኋላ ኢራን የሚፈጸምባትን ጥቃት ለመበቀል በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ ጥቃት እየፈጸመች ነው።
ኢራንም በአካባቢው አገራት የምትጽማቸው ጥቃቶች ዒላማ ያደረጉት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን እና በአገራቱ ውስጥ የሰፈሩ ኃይሎቿን ነው ብላለች።