በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ስደተኞች የተቃውሞ ሠልፍ በሚካሄድበት ወቅት ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ ተነገራቸው

ማክሰኞ ዕለት በፕሪቶሪያ ስደተኞችን በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, BBC / Thuthuka Zondi

የምስሉ መግለጫ, ማክሰኞ ዕለት በፕሪቶሪያ ስደተኞችን በመቃወም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የሚኖሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ፀረ ስደተኛ ሠልፍ በሚካሄድበት ወቅት ጥቃት እዳይደርስባቸው "ከፍተኛ ጥንቃቄ" እንዲያደርጉ ተነገራቸው።

በደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል የሆኑ ግለሰቦች በሚያደርሱት ጥቃት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መገደላቸው ተዘግቧል።

የጋና ከፍተኛ ኮሚሽን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎቹ ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ እና "ትኩረት ላለመሳብ እንዲሞክሩ" አስጠንቅቋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ናይጄሪያውያን ማኅበር ደግሞ አባላቱ ቤታቸው እንዲቀመጡ የሚገልጽ መልዕክት አስተላልፏል።

በጆሃንስበርግ ረቡዕ ዕለት በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን የሚቃወሙ ሠልፎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በደቡብ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕገ ወጥ ስደተኞች ጉዳይ የፖለቲካ መሣሪያ እየሆነ መጥቷል።

የተወሰኑ ተቃዋሚዎች የውጭ አገራት ዜጎች ሥራዎችን እያሳጣን ነው እንዲሁም ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ ከሕዝብ አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ሲሉ ይወነጅላሉ።

ነገር ግን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ዜጎች "ፍርሃታቸው እና ጭንቀታቸው ሌሎች አፍሪካዊ ወንዶሞቻቸውን ወደመጥላት እንዳያድግ" አስጠንቅቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሲሪል ራማፎሳ በአገሪቱ የነጻነት ቀን ላይ ባደረጉት ንግግር በቅርቡ በውጪ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘው ሌሎች አፍሪካውያን በአፓርታይድ ትግል ወቅት ያደረጉልንን ድጋፍ መርሳት የለብንም ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ተቃዋሚ ሠልፈኞች በፕሪቶሪያ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የተወሰኑ ሰልፈኞች መፈክሮች የተጻፉባቸው ቲሸርት የለበሱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በእጃቸው መፈለክር ይዘው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

አንድ የተቃውሞ ሠልፈኛ ለቢቢሲ "የሕገወጥ ስደተኞች መጨመር" አደባባይ እንዲወጣ እንዳደረገው ገልጾ ፖለቲከኞች ይህንን በሚመለከት ምንም እያደረጉ አይደለም ብሏል።

"አሁን ሁልጊዜም ስንናገር የነበረውን በማኅበረሰባችን ውስጥ ሕገወጥ ስደተኞች ትልቁ ችግር ናቸው እያልን የምንናገረውን የሚደግፍ ድምጽ ስላለ እናመሰግናለን" በማለት ሠልፉን ያዘጋቸውን ማርች ኤንድ ማርች አመስግኗል።

ከዚህ ቀደም ሕገወጥ ስደተኞችን በመቃወም የተደረጉ ሠልፎች ወደ አመጽ አምርተው በርካታ ስደተኞች ተጎድተዋል።

በዚህም የተነሳ ሠልፈኞቹ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች እንዲከላከሉ እና ሰላማዊ እንዲሆኑ ተጠይቋል።

ደቡብ አፍሪካ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረገችው የሕዝብ ቆጠራ መሠረት ቢያንስ 2.4 ሚሊዮን ከሌሎች አገራት የመጡ ስደተኞች አሏት።

ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከጎረቤት አገር ዚምባብዌ ቢሆኑም ከኢትዮጵያ፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከሶማሊያ፣ ከባንግላዴሽ እና ከሌሴቶም የመጡ ስደተኞች ቁጥር በርካታ ነው።

ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተሻለ ሥራ እና ኑሮ ፈልገው የሄዱት ስደተኞች 62 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት ደቡብ አፍሪካ አንጻር ሲሰላ 3 በመቶ ብቻ ናቸው።

ሆኖም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ስደተኞች ሥራ እና የተለያዩ ዕድሎችን ተሻምተውናል በሚሉ መጤ ጠል (ዜኖፎቢክ) የአገሪቱ ዜጎች ጥቃቶች ያጋጥማቸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞች ግድያ፣ ዝርፊያ እና የንብረት ውድመቶች አጋጥሟቸዋል።

የጋና ዲፕሎማቲክ ሚሽን ለዜጎቹ የተቃውሞ ሠልፎች በሚካሄዱበት ወቅት "ለደህንነታቸው ከፍተኛ ቅድሚያ እንዲሰጡ እና . . . የጥንቃቄ እርምጃ" እንዲወስዱ መክሯል።

ማክሰኞ ዕለት የወጣው ይህ ማሳሰቢያ ሱቅ ያላቸው ግለሰቦች ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ፣ ሠልፎች ከሚካሄዱባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ እና "ግጭቶችን ሊያባብሱ ስለሚችሉ" በአደባባይ ከመሰብሰብ እንዲታቀቡ ይገልጻል።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ናይጄሪያውያን ማኅበርም በተመሳሳይ ለአባላቱ "ሱቃቸውን አንዲዘጉ . . .በቤታቸው እችዲቀመጡ፤ ወደ ውጭ እነዳይወጡ" አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ በደቡብ አፍሪካ የታየውን መጤ ጠል እንቅስቃሴ አውግዘው "አመፅን ለማነሳሳት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በሚጠቀሙ ግለሰቦች የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች"ሲሉ ገልጸውታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ "በመጤ ጠሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ትንኮሳዎች እና የማስፈራራት ድርጊቶች" በሚመለከቱ የሚወጡ ዘገባዎች እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

"አመፅ፣ ጥቃት እና ሁሉም የጥላቻ ቅስቀሳዎች ሁሉን አቀፍ በሆነ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ቦታ የላቸውም" ሲሉም ተናግረዋል።

33 በመቶ የሆነ ስራ አጥ ዜጎች ባሏት በደቡብ አፍሪካ ከአስርት ዓመታት በላይ መጤ ጠል የሆነ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በቅርብ ዓመታት ወዲህ ማርች ኤንድ ማርቸ እና ኦፕሬሽን ዱዱላ የተሰኘዑ ቡድኖች በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን በመቃወም ሠልፎችን አካሄደዋል።