አንድ ሰው በዴንቨር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአውሮፕላን ተገጭቶ ሕይወቱ አለፈ

ንብረትነቱ የፍሮንቲየር የሆነ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አርብ ምሽት በዴንቨር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አጥር ዘሎ ወደ ማኮብኮቢያ የገባ ሰው ሕይወቱ ያለፈበት አጋጣሚ በአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ መቀረጹ ተነገረ።

"አንድን ሰው ገጭተናል" ሲል አብራሪው የበረራ ቁጥር 4345 ​​ሊነሳ የሚያደርገውን ዝግጅት ካቋረጠ በኋላ ለመቆጣጠሪያ ማማው ተናግሯል። "ሞተሩ ላይ እሳት አጋጥሞናል።"

በኤርባስ A321 ካቢን ውስጥ ጭስ የታየ ሲሆን የዴንቨር የእሳት አደጋ መከላከያ አባላት እሳቱን በፍጥነት ተቆጣጥረውታል። በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 224 ተሳፋሪዎች በሙሉ ለጥንቃቄ ሲባል በአየር በሚሞሉ የአደጋ ጊዜ መንሸራተቻዎች መውጣታቸው ፍሮንቲየር አስታውቋል።

"በዚህ ክስተት በጣም አዝነናል" ሲል አየር መንገዱ አክሏል። በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት አስራ ሁለት ተሳፋሪዎች በተከሰተው አደጋ ምክንያት ቀላል ጉዳቶችን አስተናግደዋል ሲል አየር ማረፊያው ተናግሯል።

ከቆሰሉት ተሳፋሪዎች አምስቱ በአቅራቢያው ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደዋል ሲሉ የአየር ማረፊያ ባለሥልጣናት ቢገልጹም ስላሉበት ሁኔታ ግልጽ አልተደረገም።

የፍሮንቲየር አየር መንገድ በረራ ወደ ሎስ አንጀለስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለማቅናት በሚነሳበት ወቅት ግለሰቡን መግጨቱን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብ አደጋው ከመድረሱ ሁለት ደቂቃዎች በፊት በአየር መንገዱ አጥር ዘሎ መግባቱን አየር መንገዱ ገልጿል።

አንድ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ለፍሮንቲየር አብራሪው ለመነሳት ዝግጁ መሆናቸውን ነግሮት መልካም ምሽት ሲልም ተመኝቶላቸው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከአጭር ጊዜ ቆይታ በኋላ አብራሪው ወደ ተቆጣጣሪው መደወሉን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ድምጽ ቅጂ ያስረዳል።

"በማኮብኮቢያው ላይ ቆመናል" ሲል አብራሪው ለተቆጣጣሪው የነገረው ሲሆን አውሮፕላኑ አንድ ሰው እንደመታ አክሎ ተናግሯል።

"አንድ ግለሰብ በማኮብኮቢያው ሲያልፍ ነበር" ብሏል አብራሪው።

ሰባት የአውሮፕላን ሠራተኞችን ጨምሮ "በአውሮፕላኑ ላይ 231 ሰዎች ጭነናል" ሲል አክሎ ተናግሯል።

አውሮፕላኑ በወቅቱ "በከፍተኛ ፍጥነት" እየተንቀሳቀሰ ነበር ሲሉ የትራንስፖርት ሚንስትሩ ሾን ደፊ ገልጸዋል።

"ትናንት ማታ አንድ ግለሰብ በዴንቨር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአውሮፕላን ማረፊያ ደህንነትን ጥሷል። ሆን ብሎ አጥሩን ዘሎ በመግባት ወደ ማኮብኮቢያ ሮጧል" ሲሉ በፊ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

"ማንም ሰው በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ዘልቆ መግባት የለበትም" ሲሉም አክለዋል።

የንግድ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ለመሳት በተለምዶ ከ240 እስከ 290 ኪሜ በሰዓት ባለው ፍጥነት ያኮበኩባሉ።

ግለሰቡ የአየር ማረፊያው ሠራተኛ እንዳልሆነ ይታመናል ሲል የዴንቨር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ (ዲኤይኤ) አስታውቋል።

"አየር ማረፊያው አጥሩን መርምሮ ምንም ብልሽት እንዳላገኘ አረጋግጧል" ሲል ዲኤይኤ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለው ጭስ ከተሳፋሪዎቹ በአንዱ በተጋትሩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ላይ ይታያል።

መንገደኛው ሆሴ ሰርቫንቴስ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገረው ጩኸት እንደሰማ እና "የቀኝ ክንፉ በእሳት ተያይዞ ሊፈነዳ የተቃረበ መስሎ ታየኝ" ብሏል።

"ተቃጥዬ ልሞት እንደሆነ አስቤ ነበር" ሲልም አክሏል። "ታውቃላችሁ እሳቱንና ጭሱን ገና ሳየው ልቃጠል እንደሆነ አስቤ ነበር።"

መንገደኞች ከአውሮፕላኑ ከወጣሁ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ተርሚናል ተመልሰዋል ሲል ዲኤይኤ አስታውቋል።

በኋላም አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች ከዴንቨር በአዲስ የፍሮንተር በረራ ወጥተዋል ሲል አየር ማረፊያው ገልጿል።

የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እና የብሔራዊ ትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ምርመራ በመጀመራቸው ማኮብኮቢያው ተዘግቷል።