ትራምፕ ከኔቶ ጉባዔ በኋላ ሊኖር በሚችል ስጋት ምክንያት አውሮፕላን መቀየራቸውን ተናገሩ

ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ አውሮፕላናቸው እየተጓዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር በቱርክ ከተካሄደው የኔቶ ጉባዔ ሲወጡ፣ ሊኖር በሚችል ስጋት ምክንያት በምስጢር አውሮፕላን መቀየራቸውን አረጋገጡ።

"እኔ የምመራው በምስጢር አገልግሎቱ (ሴክሬት ሰርቪስ) እና በወታደራዊው ክፍል ነው። በሌላ አውሮፕላን፣ በሌላ በረራ እንድሔድ ፈልገው ነበር። እነርሱ ያሉኝን ማድረግ ብቻ ነው ያለብኝ" ሲሉ ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ይፋ ያደረጉት፣ እአአ ሐምሌ 2 በካሜራዎች ዕይታ ስር ሆነው ኤር ፎርስ ዋን ላይ ከተሳፈሩ በኋላ በምግብ ማመላለሻ መኪና ወደ ወታደራዊ አውሮፕላን መዛወራቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

ይህ በመጨረሻው ሰዓት የተደረገው ቅያሬ፣ በማታለያነት በተጠቀሙበት አውሮፕላን ውስጥ የቀሩት ሰዎች ለአደጋ ተጋልጠው እንዲጓዙ ተደርጎ ይሆን በሚል ጥያቄዎችን ቢያስነሳም፣ ትራምፕ ግን እንዲያውም እርሳቸው የተሳፈሩበት ወታደራዊ ጄት "የበለጠ አደጋ" ላይ እንደነበረ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጹት፣ ኢራን በአውሮፕላኑ ላይ ሚሳዔል ለመተኮስ ስለማቀዷ ተዓማኒነት ያለው ስጋት አግኝተው ነበር። ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ፣ በኔቶ ጉባዔ አቅራቢያ ከትከሻ የሚተኮስ ሚሳዔል የያዘ ሰው ስለመታየቱ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት መረጃ ነበረው።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ጋዜጠኞች እና አንዳንድ የዋይት ሐውስ ሠራተኞች፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን ሊኖር በሚችል ስጋት የተነሳ በምስጢር መውጣታቸውን አያውቁም ነበር።

ይህ ከመሆኑ አስቀድመው፣ የኢራን "ቁጥር አንድ ዒላማ" ስለመሆናቸው ትራምፕ በአንካራው ጉባኤ ላይ ተናግረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ማክሰኞ ዕለት በአንድ ዝግጅት ላይ ለመታደም ወደ ኦሃዮ ለማቅናት ኤር ፎርስ ዋንን በመሳፈር ላይ ባሉበት ወቅት "የሆነ ስጋት የነበረ ይመስለኛል" ሲሉ ስለ አንካራው ክስተት ተናግረዋል። "ብዙ ስጋቶች አሉብኝ። ስለ ጉዳዩ [ግን] ብዙም አልጠየቅኹም" ሲሉ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም "እናንተ የማታውቋቸው በርካታ ስጋቶች አሉብኝ" ብለዋል።

ባለፈው ወር ትራምፕ ምስጢራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተገደዱት፣ ጦርነቱን ለማቆም በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል የሚደረገው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃቶችን በድጋሚ በጀመረች ማግስት ነው።

ትራምፕ ወደ ቱርክ የተጓዙት በኳታር በተበረከተው አዲስ ቦይንግ 747-8 አውሮፕላን ነበር፤ ነገር ግን ሲመለሱ "ለቀድሞው ትዝታ ሲባል" አሮጌውን ኤር ፎርስ ዋን እንደሚጠቀሙ አስታውቀው ነበር።

ሐምሌ 2 የወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ በአንካራ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ፕሬዝዳንታዊው ጄት ሲገቡ ያሳዩ ነበር።

ነገር ግን ከገቡበት አቅጣጫ በተቃራኒ በኩል ወደ አውሮፕላኑ ከፍ ብሎ ተጠግቶ በነበረ የምግብ ማመላለሻ መኪና ላይ በመሳፈር ከኤር ፎርስ ዋን በምስጢር መውጣታቸውን የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያመለክታል።

ከኤር ፎርስ ዋን ወጥተው በምስጢር ወደ አነስተኛው ሲ-32ኤ ወታደራዊ አውሮፕላን ተወስደዋል። ይህ አውሮፕላን ብዙ ጊዜ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የሚገለገሉት እና ማሻሻያ የተደረገበት ቦይንግ 757 አውሮፕላን ነው።

ጋዜጣው እንደዘገበው ከሆነ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት በረራውን መደበኛ ለማስመሰል ሲሉ የውጭ ደረጃዎችን በመጠቀም ለብቻቸው ወደ ሲ-32ኤ አውሮፕላኑ ገብተዋል።

ጋዜጠኞች እና አንዳንዶቹ የዋይት ሐውስ ሰራተኞች ወደ ኤር ፎርስ ዋን የገቡ ሲሆን፣ የአውሮፕላኑን የመስኮት መጋረጃዎች እንዲዘጉ ተነግሯቸዋል። ፕሬዝዳንቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ ስለ አለመኖራቸው መረጃ አልነበራቸውም።

በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበተ የአንድ የሚዲያ ባለሞያ፣ የመስኮት መጋረጃዎችን ዝቅ አድርገው እንዲያቆዩ ሲነገራቸው ነገሩ እንግዳ እንደሆነባቸው ተናግሯል። አንድ ፎቶግራፍ አንሺ ለጥቂት ጊዜ መጋረጃውን ከፍ ቢያደርግም፣ ወዲያውኑ እንዲዘጋው እንደተነገረው ገልቷል።

ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፣ በመጀመሪያው አውሮፕላን ውስጥ ከቀሩት መካከል የትራምፕ የካቢኔ አባላት ይገናሉ። ሚዲያው ስማቸው ያልተጠቀሰ ሁለት ኃላፊዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ ስኮት ቤሰንትም በአውሮፕላኑ ውስጥ ነበሩ።

ትራምፕ በመቀጠል ወደ አሜሪካ ጉዞ ሲያደርጉ እግረ መንገዳቸውን ወደ ዩኬ የበረሩ ሲሆን፣ ከዚያም ወደ አሮጌው ኤር ፎርስ ዋን በድጋሚ የተሳፈሩ ሲሆን አውሮፕላኑ አርኤኤፍ ሚልደንሃል አየር ማረፊያ ካረፈ በኋላ ከውስጡ ሲወርዱ ታይተዋል።

ከሲ-32ኤ አውሮፕላን ወደ ቀደመው ጄት እንዴት እንደተዛወሩ ግን ግልጽ አይደለም።

ፕሬዝዳንቱ በመቀጠል ወደ ዋሽንግተን ለመመለስ በኳታር ወደተበረከተው አዲሱ ኤር ፎርስ ዋን ተዛውረዋል።

ወደ አዲሱ ኤር ፎርስ ዋን ከተዛወሩ በኋላ ትራምፕ በአውሮፕላኑ ውስጥ ለነበሩ ጋዜጠኞች ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ከኢራን የተደቀኑናቸው ስጋቶች መኖራቸውን ቢጠቅሱም ቀደም ሲል ስላደረጉት የአውሮፕላን ቅያሬ ግን ምንም አላሉም።