የዩክሬን ግጭት 'እየተጠናቀቀ ነው' ብለው እንደሚያስቡ ፑቲን ተናገሩ

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው ከዩክሬን ጋር እያካሄደች ያለችው ጦርነት እያበቃ ነው ብለው እንደሚያስቡ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ሶቪየት ኅብረት ናዚ ጀርመንን ድል ያደረገችበትን በዓል ካከበረች በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ነው።

"ጉዳዩ እየተጠናቀቀ ነው ብዬ አስባለሁ" ሲሉ በዩክሬን እየተካሄደ ስለሚገኘው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ተናግረው ምዕራባውያን ለኪዬቭ መንግሥትን የሚያደርጉትን ድጋፍ ኮንነዋል።

የሩሲያ ዓመታዊ የድል በዓል ዩክሬን በቀዩ አደባባይ በድሮኖች ጥቃት ልታደርስ ትችላለች በሚል ስጋት የተለመደውን የታንክ እና የሚሳኤል ሠልፍ አላካሄዱም።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጨረሻ ደቂቃ ባደራደሩት እና በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል በተደረገ የተኩስ አቁም ስምምነት የጥቃት ስጋቱ ቀንሶ ሠልፉ ያለ ምንም አደጋ ተጠናቋል።

ፑቲን አስተያየትቱን የሰጡት የድል ቀን ንግግራቸውን ጦርነቱን ምክንያታዊነት ለማረጋገጥ ከተጠቀሙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

በንግግራቸውም ሩሲያ "ፍትሃዊ" ጦርነት እየተዋጋች እንደሆነ እና ዩክሬንን "በኔቶ የሚታጠቀ እና የሚደገፍ ጠበኛ ኃይል" ብለው ጠርተዋታል።

ምዕራባውያን ዩክሬንን ስለመርዳታቸው በተመለከተ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የተጠየቁት ፑቲን "እርዳታ ቃል ገብተው እስከ ዛሬ ድረስም ከሩሲያ ጋር ግጭቱን ማቀጣጠል ጀመሩ። ጉዳዩ እያበቃ ነው ብዬ ባስብም ግን ከባድ ጉዳይ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሩሲያ ኃይሎች በ2014 ክሬሚያን እና የምሥራቅ ዩክሬን ክፍሎችን የተቆጣጠሩ ሲሆን እአአ በየካቲት 2022 የዩክሬን ሙሉ ወረራን ጀመሩ።

ፑቲን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን የሚያገኙት ዘላቂ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

"በሦስተኛ አገር መገናኘትም ቢቻልም ግን በዚህ ዝግጅት ላይ ለመሳተፍ እና ለመፈረም የረዥም ጊዜ ታሪካዊ እይታን ለመፍጠር የሰላም ስምምነት ላይ የመጨረሻ ስምምነቶች ከተደረሱ በኋላ ብቻ ነው። ይህም የመጨረሻ እርምጃ መሆን አለበት" ሲሉ አክለዋል።

ዜሌንስኪ በግል ሊያገኟቸው ዝግጁ መሆናቸውን ቢሰሙም "እንዲህ አይነት መግለጫዎችን ስንሰማ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም" ብለዋል ፑቲን።

የሩሲያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፑቲን ለአውሮፓ አዲስ የደህንነት ስምምነቶችን ለመደራደር ፈቃደኛ እንደሆኑ እና የሚመርጡት የድርድር አጋር የጀርመን የቀድሞ ቻንስለር ጄርሃርድ ሽሮደር እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

የቀድሞው ቻንስለር የፑቲን የረዠም ጊዜ ወዳጅ ሲሆኑ በሩሲያ መንግሥት ባለቤትነት ስር ላሉ የኤነርጂ ኩባንያዎች ላይ በመሥራታቸው ምክንያት አወዛጋቢ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ የአውሮፓ ኅብረት ከሩሲያ ጋር ለመደራደር "ተስፋ" እንዳለው እና ዜሌንስኪ እንዲህ ዓይነት እርምጃን እንደሚደግፉ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። በፋይናንሺያል ታይምስ በተጠቀሰው የኮስታ ንግግር መሠረት የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች "ይህንን ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜ ሲመጣ ከሩሲያ ጋር በብቃት ለመወያየት ምን እንደሚያስፈልገን" እየተማከሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአሜሪካ በተመራው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ኪዬቭ እና ሞስኮ አንድ ሺህ እስረኞችን ለመለዋወጥም ተስማምተዋል። ፑቲን ቅዳሜ ዕለት ሩሲያ ስለልውውጡ ምንም ዓይነት መረጃ ከዩክሬን በኩል እስካሁን እንዳልሰማች ተናግረዋል።

በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በ'ቀዩ አደባባይ' ሠልፍ ላይ ምንም ዓይነት ወታደራዊ መሳሪያ ያልታየ ሲሆን ክሪምሊን በተለምዶ የሩሲያን ወታደራዊ ኃይል ለዓለም አቀፍ መድረክ የምታሳይበት ሰልፍ ነው።

በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉት ጋዜጠኞች በጣም ጥቂት የነበሩ ሲሆን ብዙ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ፈቃድ አልተሰጣቸውም።