ትራምፕ የጣልያኗ ጠ/ሚኒስትር ፎቶ እንድንነሳ 'ለምናኛለች' ማለታቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ፎቶ ለመነሳት "እንደለመኗቸው" ለጣሊያን ቴሌቪዥን ከተናገሩ በኋላ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ ሰረዙ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፎቶ ለመነሳት "ለመኑ" ብለው የተናገሩት ሙሉ በሙሉ "ፈጠራ" ነው በማለት አጣጥለውታል።
ትራምፕ እና ሜሎኒ በዚህ ሳምንት ፈረንሳይ ውስጥ በተካሄደው የቡድን 7 ጉባኤ ላይ በቅርበት ሲነጋገሩ የታዩ ሲሆን፣ የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ኋላ ላይ ለጋዜጠኞች ግንኙነታቸው ላይ ለውጥ እንደሌለ እና "ምንም ዓይነት መወቃቀስ እንዳልተፈጠረ" ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ትራምፕ ከአንድ ጣሊያኑ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ "ፎቶ እንድነሳ ስትለምነኝ አሳዝናኛለሁ" ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች በፈረንሳይ ስብሰባ ወቅት ጎን ለጎን ተቀምጠው ፈገግ እያሉ የተነጋገሩበትን ጨምሮ በርካታ ጊዜ አብረው የሚታዩባቸው ምሥሎች ተሠራጭተዋል።
ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትሯ "ስላናገርኳት ምናልባት ደስ ብሏት ይሆናል" ማለታቸውን የገለጸው ቴሌቪዥን ጣቢያው፤ ፕሬዝዳንቱ እንዲህ ያሉበትን የራሳቸውን የእንግሊዝኛ ንግግር ሳሰያማ በጣልያንኛ የተተረጎመውን አቅርቧል።
ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ትራምፕ ያሉትን ሙሉ በሙሉ ባለማመን መገረማቸውን በኢንስታግራም ላይ ለሰባት ሚሊዮን ተከታዮቻቸው ባስተለላፉት አጭር የቪዲዮ መልዕክት ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ ክስተት ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ አለመሆኑን በመግለጽም "የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለአጋሮቻቸው እንዲህ ዓይነት ባህሪ ለምን እንደሚያሳዩ አላውቅም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ።
"ማለት የምችለው ፕሬዝዳንቱ ለምዕራባውያን እና ለአሜሪካ ጠላቶች ተመሳሳይ ቁርጠኝነት የላቸውም፤ እንዲያውም የበለጠ አክብሮት ያላቸው መሆኑ የሚየሳዝን ነው" ብለዋል።
"ነገር ግን ግን ማስታወስ ያለባቸው አንድ ነገር አለ፤ እኔም ሆንኩ ጣልያን ፍጽሞ ለምነን አናውቅም።"
ቢቢሲ ከትራምፕ ጽህፈት ቤት፣ ከዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቋል።
በ2022 የጣልያንን ጠቅላይ ሚኒስትርነትን የያዙት ሜሎኒ በጥር 2025 በትራምፕ ሲመተ በዓል ላይ የተገኙ ብቸኛዋ የአውሮፓ አገር መሪ ሲሆኑ፣ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት መካከል ድልድይ እንደሚሆኑ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።
ሜሎኒ አሜሪካ ከኢራን ጋር ያደረገችውን ጦርነት በግልጽ የተቃወሙ ሲሆን፣ ትራምፕ ሚያዝያ ላይ ከጣልያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ 'ኮሪየር ዴላ ሴራ' ጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ "[ሜሎኒ] ደፋር ትመስለኝ ነበር፤ ነገር ግን ተሳስቻለሁ" ብለዋል።
ትራምፕ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን "በወንጀል ላይ ደካማ እንዲሁም በውጭ ፖሊሲ ረገድ መጥፎ ናቸው" በማለት ሲወቅሷቸው፣ ሜሎኒ ተቃውመዋቸው ነበር።
የትራምፕ ቃለ ምልልስ ከተሰማ በኋላ የጣልያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ወዲያውኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ደውለው ድጋፋቸውን የገለጹላቸው ሲሆን፣ በርካታ የጣልያን ፖለቲከኞች ከጠቅላይ ሚኒስትሯ ጎን መቆማቸውን ገልጸዋል።
"ማንም ሰው እንዲህ ባለ ትዕቢት እና ቃና የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትርን መናገር የለበትም" ሲሉ የተቃዋሚው ዴሞክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ፊሊፖ ሴንሲ ተናግረዋል።
ጣልያን እንዲህ ዓይነት ውርደት አይገባትም ያሉት ደግሞ 'ፋይቭ ስታር ሙቭመንት' የተባለው ፓርቲ መሪ ጁሴፔ ኮንቴ፤ ከዋሽንግተን ውለታ መፈለግ ብሔራዊ ክብርን እና ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥል መሆን የለበትም ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ የራሳቸው ፓርቲ የሆነው 'ብራዘርስ ኦፍ ኢታጣሊ' ፓርቲ የምክር ቤት ቡድን መሪ ሉቺዮ ማላን የትራምፕ አስተያየት በተለያዩ በአውሮፓ መሪዎች ላይ የተሰነዘሩ ሰፊ የጥቃት ንግግሮች አካል መሆኑን እና ከሁሉም በላይ የትራምፕን ገጽታ እና ሥልጣንን የሚጎዳ ነው ብለዋል።
ማላን ጨምረውም ከቡድን 7 ስብሰባ የወጣው ቪዲዮ ትራምፕ ከገለጹት በጣም የተለየ መሆኑን በማንሳት፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በእውነት ያበሳጨው ሜሎኒ አስፈላጊ በሆኑበት ጊዜ ለዋሽንግተን እምቢ ማለታቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።















