በምርጫው ብልፅግና ዕጩ ባላቀረበባቸው ክልሎች የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ ተፎካካሪዎች አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 10/2018 ዓ.ም. ለአራተኛ ጊዜ ያፀደቃቸውን የምርጫ ውጤቶች ይፋ ሲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ገዢው ፓርቲ ብልፅግና አብዛኞቹን መቀመጫዎች አሸንፏል።
ብልፅግናን ጨምሮ ሦስት ፓርቲዎች በተወዳደሩበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አማሮ ኬሌ ምርጫ ክልል ኢዜማ አሸንፏል።
በዚህ የምርጫ ክልል የኢዜማ ዕጩ ሆነው የቀረቡት አቶ አወቀ አምዛዬ በ40.6 በመቶ ድምፅ ተፎካካሪዎቻውን ማሸነፍ ችለዋል።
አወቀ አምዛዬ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫም በዚሁ የምርጫ ክልል ያሸነፉ ሲሆን፤ የአካባቢውን ሕዝብ ለሁለተኛ ጊዜ በእንደራሴዎች ምክር ቤት ይወክላሉ።
የምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ 40 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 35 ለክልል ምክር ቤት አሸናፊዎችን ይፋ አድርጓል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምጽ ካገኙባቸው 17 የምርጫ ክልሎች መካከል በ16ቱ ብልጽግና ፓርቲ ዕጩ አላቀረበም።
በኦሮሚያ ክልል ጎማ 2 ምርጫ ክልል የተወዳደሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 97.5 በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል።
ከእርሳቸው ጋር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ (ኢዜማ) እና የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ዕጩዎች ተወዳድረው ነበር።
ብቻቸውን በኦሮሚያ ክልል ያለ ተፎካካሪ የተወዳደሩት የቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ዲማ ኖጎ እና አራርሶ ቢቂላ አሸንፈዋል።
ሰኔ10 ይፋ በሆነው የምርጫ ውጤት በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል አምስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች አሸናፊዎች ተለይተዋል።
በኮፈሌ 2 ምርጫ ክልል ብቻቸውን የተወዳደሩት የአዲስ ትውልድ ፓርቲ እጩ ሰለሞን ታፈሰ አሸንፈዋል።
ብልፅግና ፓርቲን ወክለው በነቀምቴ የተወዳደሩት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ በ92 በመቶ ድምፅ አሸንፈዋል።
የዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸናፊዎች የተለዩበት አማራ ክልል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወዳደሩበትን ባሕር ዳር ምርጫ ክልልን ጨምሮ አራቱን ብልፅግና ሲያሸንፍ ሦስቱን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አሸንፏል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ በገርጨጭ እና የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ደግሞ በሳይንት 2 አንድ አንድ መቀመጫ አሸናፊ ሆነዋል።
ባለፈው ሣምንት ይፋ በተደረገ የምርጫ ውጤት በአማራ ክልል ጎንደር ዙሪያ 4 የተወዳደሩት የአብኑ ጣሂር መሐመድ አሸንፈዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ምርጫ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ አላቀረበም ነበር።
በእስቴ 1 ከአብን ፓርቲ ጋሻው መርሻ 76.5 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል። በዚህ የምርጫ ክልል አራት ፓርቲዎች የተወዳደሩ ሲሆን፤ ብልፅግና ግን አልተወዳደረም።
የአብን ዕጩ የሆኑት መልካሙ ፀጋዬም እንዲሁ በላይጋይንት 1 የምርጫ ክልል ሲያሸንፉ ከብልፅግና ፉክክር አልገጠማቸውም።
በኩታ በር የምርጫ ክልልም እንዲሁ ብልፅግና ሳይወዳደር የአብኑ የሱፍ ኢብራሂ በ70 በመቶ ድምፅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኝት ችለዋል።
በሳይንት 2 ምርጫ ክልል ብቻቸውን የተወዳደሩት የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እጩ ሙሐሙድ ቡሽራ ምንም እንኳ ለመምረጥ 35,924 መራጮች ቢመዘገቡም 9,577 ድምፅ አግኝተው ማሸነፋቸውን ቦርዱ አውጇል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስድስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤቶች የፀደቁ ሲሆን፤ ሦስቱን ብልፅግና ቀሪዎችን ሦስት መቀመጫዎች ደግሞ ኢዜማ በአማሮ ኬሌ፣ የጌዲዮ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት በወናጎ እንዲሁም የወላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በሶዶ ዙሪያ አሸንፈዋል።
አራት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውጤቶች የፀደቁበት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሁለቱን ብልፅግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፤ ኢዜማ እና ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ደግሞ አንድ አንድ ወንበሮችን ማግኘት ችለዋል።
ተፈራ ጀበሮ በሎማ ቦሳ ምርጫ ክልል ካለ ብልፅግና ዕጩ ከስድሰት ፓርቲዎች ጋር ተፎካክረው በ33.5 በመቶ ድምፅ ነው ያሸነፉት።
በማጀት መደበኛ የምርጫ ክልል ደግሞ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እና የወሎ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቱ ብቻ ተወዳድረው የነእፓ እጩ ብርሃኑ ሚስል በ34 በመቶ ድምፅ አሸንፈዋል።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23 መቀመጫዎች ያሏት አዲስ አበባ እስካሁን በምርጫ ቦርድ ፀድቆ ይፋ የሆኑ ሁለት ወንበሮች ብቻ ናቸው።
ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ባላቀረበበት በምርጫ ክልል 11 የግል ተወዳዳሪ የሆኑት አበበ ገመቹ 17.6 በመቶ ድምፅ አሸንፈዋል። ምንም እንኳ በዚህ ምርጫ ክልል ገዢው ብልፅግና ዕጩ ባያቀርብም አሸናፊውን የግል ተወዳዳሪ ጨምሮ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ተወዳድረዋል።
በምርጫ ክልል 25 ከብልፅግና ጋር ስምንት ፓርቲዎች የተፎካከሩ ሲሆን የብልፅግና ዕጩ የሆኑት የሺመቤት ነጋሽ በ51 በመቶ አሸንፈዋል።
ሠኞ ይፋ በሆኑ ሁለት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእንደራሴዎች ምክር ቤት የምርጫ ውጤቶች ኢዜማ በእነሞርና ኢነር ምርጫ ክልል፤ ነእፓ ደግሞ በቅበት ምርጫ ክልል ሁለቱም በ51 በመቶ ገደማ ድምፅ አሸንፈዋል።
በድሬዳዋ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማው ከንቲባ እና ብልፅግና ዕጩው ከድር ጁሃር ሲያሸንፉ፤ በሐረሪ ይፋ የሆኑትን ሁለቱንም መቀመጫዎች ብልፅግና በሰፊ ድምፅ አሸንፏል።
በሶማሌ ክልልም እንዲሁ በቀብሪደሃር እና በቦዶኖት ምርጫ ክልሎች ሁለቱንም መቀመጫዎች ብልፅግና አሸንፏል።
አፋር ክልል ከፀደቁ ሁለት ውጤቶች ውስጥ አንደኛውን የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ዕጩ ሙሳ አደም በ88.8 በመቶ ሲያሸንፉ፤ የብልፅግናው ዕጩ ኢማሊ አሕሙድ 90.1 በመቶ ማሸነፍ ችለዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ በሽናሻ ልዩ ምርጫ ክልል ብልፅግና አብላጫ ድምፅ ሲያገኝ፤ ዕጩዋ ፍሬሕይወት አበበ በ50.8 በመቶ አሸንፈዋል።
ባለፈው ሳምንት በወጡ ውጤቶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስት ተፎካካሪዎች ብቻ ማሸነፍ ችለዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ክልሎች የክልል ምክር ቤት የምርጫ ውጤቶች ይፋ የሆኑ ሲሆን፤ አብዛኞቹን ብልፅግና ሲያሸንፍ እንደ ኢዜማ፣ ነእፓ፣ ኦብነግ፣ ሶማሌ ፌደራሊስት፣ አዲስ ትውልድ፣ ወሎ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ፣ አብን፣ የወላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ያሉ ፓርቲዎችም የተወሰኑ ወንበሮችን አሸንፈዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. ምርጫ ካሰናዳባቸው 1,139 ምርጫ ክልሎች ውስጥ የ723ቱን ማፅደቁን አስታውቋል።
ቦርዱ በድምፅ አሰጣጥ፣ በአቆጣጠር እና በአደማመር ላይ እስካሁን በ129 የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታዎች እንደቀረቡለት ገልጿል።
እስካሁን ግን ውሳኔ ያላገኙት 43 ምርጫ ክልሎች ብቻ ናቸው ብሏል።
ቦርዱ ትናንት ሰኔ 10 2018 ዓ.ም. ዕለት በሰጠው መግለጫ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይፋዊ ውጤት ሰኔ 14/2018 ዓ.ም እንደሚገለጽ አስታውቋል።















