በሜክሲኮ ለዓለም ዋንጫ በሚል ትምህርት ቀድሞ በመዘጋቱ ወላጆች ቁጣቸውን ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜክሲኳውያን ወላጆች በዚህ ዓመት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ አገሪቱ ተጨማሪ እንግዶችን ማስተናገድ እንድትችል በሚል ትምህርት ቤቶችን አንድ ወር ቀደም ብሎ ለመዝጋት የተያዘውን ዕቅድ ተቃወሙ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ማሪዮ ዴልጋዶ እንዳሉት የዚህ ዓመት የትምህርት ዘመን ግንቦት 28 2018 ዓ.ም. ላይ ያበቃል። በዚህም የተነሳ በመላ አገሪቱ ያሉ ወላጆች ለልጆቻቸው ማቆያ ለማግኘት የቀራቸው ከአራት ሳምንታት ያነሰ ጊዜ ነው።
የወላጆችና የአሠሪዎች ማኅበራት የሚኒስቴሩን ውሳኔ ከተቃወሙ በኋላ፣ የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሼንባም የቀረበው "ምክረ ሃሳብ" መሆኑን በመግለጽ ቁጣውን ለማብረድ ሞክረዋል።
ሜክሲኮ ከአሜሪካ እና ካናዳ ጋር በመሆን ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 12 2018 ዓ.ም. ድረስ የሚካሄደውን የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድርን ታስተናግዳለች።
ዴልጋዶ ሐሙስ ዕለት ይፋ ያደረጉት የመንግሥት ዕቅድ የዓለም ዋንጫን ተከትሎ የሚፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ እና የላቲን አሜሪካን አገራት በከፍተኛ ሙቀት እንደሚጠቁ የሚተነብየው የአየር ሁኔታ የትምህርት ዓመቱን ቀደም ብሎ ለማጠናቀቅ በተደረገው ውሳኔ ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ውሳኔው እያንዳንዱ ግዛት ያለምንም ተቃውሞ መቀበላቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።
የሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በይፋ የሚጀመረው እአአ ነሐሴ 31 መሆኑ ቢገለጽም ተማሪዎች ወደኋላ እንዳይቀሩ የሁለት ሳምንታት "የማጠናከሪያ" ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ነገር ግን ድንገተኛ የጊዜ ሰሌዳ ለውጥ ከወላጆች ወዲያውኑ ቁጣን ቀስቅሷል።
"ልጆቹ በአሁኑ ጊዜ ፈተና እየወሰዱ ነው፤ እና በተማሩት ነገር ላይ በመመስረት ፈተናው እንደሚዘጋጅ ተነግሯቸዋል። ይህ ምን ዓይነት ምላሽ ነው?" ሲሉ አንድ ግለሰብ ለሜክሲኮ ጋዜጣ ኤል ዩኒቨርሳል ተናግረዋል።
ሌላ ወላጅ ደግሞ የመጪውን የበጋ ወራት ወጪ በማሰብ "ከተማዋ ለቱሪስቶች ባዶ እንድትሆን ይፈልጋሉ፣ እናም ምን እንደምንበላ እያሰብን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የአገር አቀፉ የወላጆች ኅብረት የትምህርት ሚኒስቴርን ዕቅድ "የአንድ ወገን ውሳኔ" በማለት አውግዟል። አክሎም የዓለም ዋንጫ ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት እንደምክንያት መቅረቡ "ይቅር የማይባል ጥፋት ነው" ሲል ገልጾታል።
"ጨዋታዎቹ የሚካሄዱት በሦስት ከተሞች ብቻ ነው" ያለው ኅብረቱ "በዚህ ሰበብ ወደ 23 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ለምን ይጎዳሉ?" ሲል ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮፓርሜክስ የተባለው የንግድ ባለቤቶች ማኅበር የመንግሥት ድንገተኛ ውሳኔ ለሠራተኞችም ሆነ ለአሠሪዎች አለመረጋጋት እንደሚፈጥር ተናግሯል።
እያንዳንዱ ግዛት የሙቀት መጨመርን እና የጉዞ መቆራረጥን ለማስተናገድ የራሳቸውን ዝግጅት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፤ ይህም በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ይቀንሳል ሲል ገልጿል።
የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱት ሦስት የሜክሲኮ ግዛት አስተዳዳሪዎች ዕቅዱን የተቃወሙ ሲሆን አንደኛው ግዛት በመጀመርያው የትምህርት ዘመን ዕቅድ መሠረት እንደሚሄድ አስታውቋል።
ሼንባም ለወላጆቹ ቅሬታ እና ትችት ምላሽ ለመስጠት አርብ ዕለት በነበራቸው ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዕቅዱ ዳግመኛ እንደሚታይ ተናግረዋል።
"ብዙ ሜክሲኳዊያን እግር ኳስን ስለሚወዱ እና የዓለም ዋንጫን ስለሚከታተሉ፣ ይህ ሀሳብ የቀረበው የእረፍት ጊዜውን ቀረብ ለማድረግ ነው" ሲሉ ፕሬዝዳንቷ አብራርተዋል። "ነገር ግን የሴቶችና የወንዶች የትምህርት ቀናትም ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው።" ብለዋል።
"ስለዚህ ዕቅድ ነው። ሙሉው የጊዜ ሰሌዳ ገና ዝግጁ አልሆነም፤ እና ሙሉ በሙሉ እስኪወሰን ድረስ እንጠብቃለን።"
አክለውም ሀሳቡ የመጣው ከፌደራል መንግሥቱ ሳእሆን ከመምህራን ማኅበራት እና ከአንዳንድ ግዛቶች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች መሆኑን ተናግረዋል።














