የአማካይ ዘመን ምርጫን ሪፐብሊካኖች ካሸነፉ እያንዳንዱ አዋቂ አሜሪካዊ 5,000 ዶላር እንደሚያገኝ ትራምፕ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በኅዳር ወር በሚካሄዱት የአማካይ ዘመን ምርጫዎች ሪፐብሊካኖች ሁለቱንም ምክር ቤቶች ካሸነፉ፣ እያንዳንዱ አዋቂ አሜሪካዊ 5,000 ዶላር እንዲያገኝ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

ይህ ዕቅድ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚያስወጣ መሆኑ ተገልጿል።

ትራምፕ አከራካሪ የሆነውን ይህን ቃል የገቡት በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ዘመን አማካይ ላይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ዕቅዱ እንዴት እንደሚተገበር እና ገንዘቡ ከየት እንደሚመጣ ግን ምንም ዝርዝር አልሰጡም። ሆኖም ገንዘቡ አሜሪካ ውስጥ ብቻ መዋል እንዳለበት ተናግረዋል።

ዴሞክራቶች በፍጥነት በሰጡት ምላሽ ይህንን የትራምፕ ቃል "ባዶ ተስፋ" ብለው ሲተቹት፣ ሌሎች ደግሞ እንዲህ ያለ ቃል ኪዳን በሕግ የሚፈቀድ ስለመሆኑ ጥያቄ አቅርበዋል።

በአሜሪካ የሚገኙ አዋቂ ዜጎች ቁጥር 270 ሚሊዮን እንደሚጠጋ የሚገመት ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ 5,000 ዶላር መስጠት የአሜሪካ መንግሥትን 1.3 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ያስወጣል።

የትራምፕ እቅድ በተግባር ሊፈጸም ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጥያቄ እያስነሳ ነው። በተለይም አሜሪካና እስራኤል በየካቲት ወር ከኢራን ጋር የገቡበት ጦርነት በአሜሪካ ያስከተለው የሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ ባለበት ተፈጻሚነቱ አጠያያቂ ሆኗል።

በጦርነቱ ለሚፈፀምባት ጥቃት ኢራን እየወሰደች ባለችው አፀፋዊ እርምጃ የሆርሙዝ ሰርጥን መዝጋቷ፣ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ መዋዠቅ አስከትሏል። ይህም ትራምፕ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ከፓርቲያቸው ጭምር ጫና እንዲደረግባቸው አድርጓል።

ጦርነቱ ከአማካይ ዘመን ምርጫ በኋላም እንደማያበቃ እና የነዳጅ ዋጋም እስከዚያው ድረስ እንደማይቀንስ ፕሬዝደንቱ ረቡዕ ዕለት ለደጋፊዎቻቸው አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዝደንቱ አስተያየታቸውን የሰጡት በቴክሳስ ካደረጉት ንግግር በፊት ነው።

ትራምፕ በቴክሳስ ዳላስ ከተማ በተካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባኤ ላይ ያደረጉት ረጅም ንግግር፣ ግጭቱ በአሜሪካውያን የኑሮ ደረጃ ላይ እያሳደረ ባለው ተፅዕኖ ላይ ያተኮረ ነበር። የዜጎችን የመግዛት አቅም ለማሳደግ የገቡት ቃል ኪዳንም በአዳራሹ ውስጥ ከፍተኛ ጭብጨባና ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።

"ሪፐብሊካኖች የተወካዮች ምክር ቤቱንና የአሜሪካ ሴኔትን ካሸነፉ" አሉ ትራምፕ፣ "በዩናይትድ ስቴትስ ያለ እያንዳንዱ አዋቂ ዜጋ 5,000 ዶላር እንዲያገኝ አደርጋለሁ።"

"ገንዘቡን ወጪ ለማድረግ ወደ ካናዳ እንድትሄዱ አንፈልግም። ወደ ቻይና ወይም ወደ ጀርመን እንድትሄዱም አንፈልግም። ገንዘቡን በአሜሪካ ውስጥ ማውጣት አለባችሁ" ብለዋል። ሆኖም፣ ገንዘቡ አሜሪካ ውስጥ ብቻ ወጪ ስለመደረጉ እንዴት ቁጥጥር እንደሚደረግ አይታወቅም።

ትራምፕ እንዲህ ያለ የገንዘብ ክፍያ ለመፈፀም ቃል ሲገቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከዚህ ቀደም ከቀረጥ ገቢዎች የሚሸፈን 2,000 ዶላር ቼክ ለአሜሪካውያን ለመስጠት ሀሳብ አቅርበው ነበር።

ሌሎች የአሜሪካ ፖለቲከኞችም በምርጫ ካሸነፉ ገንዘብ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ያውቃሉ።

ለአብነትም በኮቪድ 19 ወቅት ዲሞክራቶች በጆርጂያ የሴኔት መቀመጫን ካሸነፉ 2,000 ዶላር የማገገሚያ ገንዘብ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ነበር።

በአሜሪካ የመንግሥት ወጪዎች በኮንግረስ መፅደቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ትራምፕ በዳላስ ባደረጉት ንግግር ጉዳዩን ወደ ኮንግረስ ይወስዱ እንደሆን ያሉት ነገር የለም።

ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት ይህ አዲስ ሐሳብ የሕግ ጥያቄዎችንም ሊያስነሳ ይችላል።

የፌዴራል ሕጎች የመራጮችን ድምፅ ለማግኘት ወይም በምርጫ ሂደት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረጉ የገንዘብ ክፍያዎችን ይከለክላሉ።

ሆኖም የትራምፕ ቃል እንደ ግብር ቅነሳ ባሉ እርምጃዎች ሊፈጠም እንደሚችል እና ይህም በሕግ የተፈቀደ መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስተያየት የሰጡ አንድ የምርጫ ሕግ ባለሙያ፣ ትራምፕ የገቡት ቃል በአሜሪካ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያ ማሻሻያ የተረጋገጠው የመናገር ነፃነት አካል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ገልፀዋል።