"ጦርነት ሸሽተን ከትግራይ ብንወጣም የባንክ አካውንታችን በመዘጋቱ ተቸግረናል"

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ህወሓትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት መመስረታቸውን ካስታወቁ በኋላ በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት አንድ ሳምንት ሞልቶታል።

በእነዚህ ጊዜያት ወደ ትግራይ እና ላሊበላ የሚደረጉ በረራዎች ተቋርጠዋል። በትግራይ የኢትዮ ቴሌኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች ገልጸዋል።

በተጨማሪም የዓለምን የኢንተርኔት ነጻነት፣ የዲጂታል መብቶች የሚከታተለው ኔትብሎክ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ መስተጓጎሉን ይፋ አድርጓል።

ይህም በክልሉ ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ በባንኮች የሚደረግ የገንዘብ እንቅስቃሴ ውስን በነበረበት ወቅት በሞባይል ይደረጉ የነበሩ ግብይቶች እንዲቋረጡ በማድረጉ በርካቶችን ስጋት ላይ መጣሉን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ በትግራይ የባንክ ሂሳቦችን ከፍተው የነበሩ ግለሰቦች ደግሞ አካውንታቸው መዘጋቱን እና ገንዘብ ለማውጣት መቸገራቸውን ተናግረዋል።

የባንክ አካውንቶቹ የተዘጉት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ማለትም መስከረም 16/ 2019 ዓ.ም. መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።

ነዋሪዎቹ በዋናነት በሦስት ባንኮች የከፈቷቸውን አካውንቶች ማንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

የአካውንቶቹ መዘጋት በትግራይ የሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ብቻም ሳይሆን አካውንታቸውን በክልሉ ከፍተው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩትን ጭምር መጉዳቱን አስረድተዋል።

ቢቢሲ ይህንን ዘገባ እያጠናቀረ ባለበት ወቅት በአዲስ አበባ አንዳንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞችን ሒሳብ ለመክፈት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ቢቢሲ ከባንኮችም ሆነ ከመንግሥት ባለሥልጣናት አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን አልተሳካም።

ጦርነቱ ከመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት ከአድዋ ከተማ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናገረው ፍሬዘር ሲሳይ የንግድ ባንክ አካውንቱ እንደተዘጋ ያወቀው ለመስቀል እና ደመራ በዓል ለቤተሰቦቹ ገንዘብ ለመላክ ሲሞክር መሆኑን ይናገራል።

ፍሬዘር በትግራይ የሚገኙ ቤተሰቦቹን የሚያስተዳድረው እሱ እንደሆነ ገልጾ፣ የባንክ ሂሳቡ ሲዘጋም ወደ ብሔራዊ ባንክ አቅንቶ የተዘጋበትን ምክንያት ለመጠየቅ መሞከሩን አስረድቷል።

በብሄራዊ ባንክ ቅሬታ የሚሰሙ አካላትም "የደንበኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ነው" የሚል ምላሽ እንደሰጡት ይናገራል።

ፍሬዘር ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የግል ባንክ ሂሳብን መዝጋት ልክ አይደለም ይላል።

ይህ እኔ ላይ ብቻ የደረሰ ችግር አይደለም የሚለው ፍሬዘር፣ በትግራይ ከሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች የከፈቱ ሰዎች፣ በዚህ ምክንያት የዕለት ጉርስ ለማግኘት መቸገራቸውን ያስረዳል።

የንግድ ባንክ ሂሳባቸውን ለማስከፈት መጀመሪያ ሦስት ቅርንጫፎች ክፍት ሆነው እንደነበር የሚያስረዳው ፍሬዘር፣ ቅርንጫፎቹ አካውንታቸውን ለማስከፈት በሚጠባበቁ ረዣዥም ሠልፎች መሞላታቸውን ይናገራል።

በኋላ ላይም አገልግሎቱን የሚሰጡ ሌሎች አስራ ሁለት ቅርንጫፎች ላይ ደንበኞች እንዲያመለክቱ መደረጉን ፍሬዘር ያስረዳል።

ሌላው ቢቢሲ ያነጋገረው ገብረመድህን በበኩሉ በትግራይ ያለውን ሁኔታ በመስጋት ወደ አዲስ አበባ የሄደው ከሁለት ወር በፊት እንደነበር ያስታውሳል።

በክልሉ ያለውን ውጥረት ፈርቶ ወደ አዲስ አበባ ቢሸሽም የጦርነቱ ዳፋ ግን ተከትሎታል።

ለሥራ ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ ከተማ እየሄደ በነበረበት ወቅት ለሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት አቅራቢዎች በሞባይል ለመክፈል ሲሞክር በመቸገሩ ግራ መጋባቱን ተናግሯል።

"ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ የሕዝብ ትራንስፖርት ውስጥ ገብቼ በሞባይል ባንኪንግ ለመክፈል ስሞክር አልሰራ አለኝ። ምንም መረጃ ስላልነበረኝ ክው አልኩኝ" ሲል የተፈጠረበትን ግራ መጋባት ያስረዳል።

ነገሩ ድንገተኛ እንደሆነና ብዙ ሰዎች በምግብ ቤቶች እና በትራንስፖርት ውስጥ ሆነው በሞባይል ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻላቸው ችግር ውስጥ መውደቃቸው ተናግሯል።

በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ ጓደኞቹ ምግብ ቤት ውስጥ ተጠቅመው፣ ገንዘብ ማስተላለፍ ባለመቻላቸው ቤተሰቦቻቸው መጥተው እንዲከፍሉላቸው መጠየቃቸው እንደሚያውቅ ገ/መድህን ጨምሮ አስረድቷል።

"የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ድንገት ነው የተዘጋው። ምንም ዓይነት ማስጠንቀቅያ አልተሰጠም፤ እንደ እኔ ያሉ ትግራይ ውስጥ ያለውን አስፍሪ ሁኔታ ፈርተውና ሸሽተው የመጡ ብዙ ሰዎችን አሳዝኗል። አሁን በዚህ ምክንያት ብዙ የትግራይ ተወላጆች ችግር ውስጥ ናቸው።"

ገብረ መድህን በባንክ አካውንቱ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ለማውጣት ያለው አማራጭ አንድ ብቻ እንደነበር ይናገራል።

"በኤቲኤም አማካኝነት ገንዘብ ማውጣት ይቻል ነበር። በቀን እስከ 10,000 ብር ከኤቲኤም ማውጣት ይቻላል፤ ነገርግን አገልግሎቱ ካለፉት ስምንት ወራት ጀምሮ በትግራይ ውስጥ እየሰራ ስላልነበር የይለፍ ቁጥራችንን ረስተነዋል ወይም ደግሞ ካርዱ በእጃችን የለም።"

ገ/መድህን፣ በስልክ አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ከቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ጋር መገናኘት አለመቻሉን በመግለጽ፣ የሚጠቀምበት ገንዘብን ማንቀሳቀስ አለመቻሉ ደግሞ ተጨማሪ ስጋት እንደፈጠረበት ያስረዳል።

ቤተሰቦቹ እሁድ ዕለት ከመቀለ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ኮረብታ ላይ በመሆን እንደደወሉለት ለቢቢሲ ጨምሮ ተናግሯል።

"ከመቀለ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው አሸጐዳ ላይ ሆነው ደውለውልኛል፣ መደበኛ የስልክ መስመር አይሰራም። ትንሽ አውርተናል፤ ያሉበትን ሁኔታ ለመናገር ግን ያዳግታል" ብሏል።

ገብሩ ገብረዮሐንስ በ2012 ዓ.ም. በተካሄደው ጦርነት የትግራይ ኃይሎች አባል ነበር። ጦርነቱ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ ደጋግሞ ለሥራ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ይናገራል።

በተለይ ከመጋቢት 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በተደጋጋሚ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ መደረጉን ያስታውሳል።

ገብሩ ባደረበት ስጋት ከአገር ለመውጣት መወሰኑን ይናገራል፤ ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት ከአገር ውጭ ሆኖ በባንክ ያለው ገንዘቡን በኦንላይን ለማንቀሳቀስ ሲሞክር አልቻለም።

"ገንዘቤን ለመጠቀም አስቤ ነበር፤ አሁን ግን አካውንቴ ትግራይ ውስጥ በመከፈቱ ብቻ መጠቀም አልቻልኩም። በዚህ ምክንያት ሕይወቴ አደጋ ላይ ወድቋል" ይላል።

ፀደይ በበኩሏ ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ከሁለት ወራት በፊት መሆኑን ትናገራለች።

በአዲስ አበባ ረዥም ጊዜ የመቆየት ፍላጎት እንዳልነበራት የምታስረዳው ፀደይ፣ አሁን ድንገት የትራንስፖርትና የስልክ አገልግሎት ሲቋረጥ ድንጋጤ ውስጥ መውደቋን ታስረዳለች።

"መጀመሪያ የመጣሁት ለሕክምና ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታውን ሳይ ቤተሰቦቼን ወደዚህ ለማዛወር ወሰንኩ የአየር ትኬታቸው ለአርብ ነበር፤ በረራው በመቋረጡ ግን አልተሳካም።"

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ወደ ክልሉ የሚያደርገውን በረራ "ላልተወሰነ ጊዜ" አቋርጧል።

"መጀመርያ ራሳችንን ለማጽናናት ሞክረን ነበር፤ ይህ ሳይበቃ በሚቀጥለው ቀን የባንክ አካውንታችን እንደተዘጋ ተነገረን" ስትል ፀደይ የተፈጠረውን በቅደም ተከተል ትገልጻለች።

በትግራይ ክልል በሚገኙ የንግድ ባንክ፣ አንበሳና ወጋገን ባንኮች የተከፈቱ አካውንቶች መዘጋታቸውን ፀደይ ትናገራለች።

ሁለቱ የግል ባንኮች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀጠል በክልሉ ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥር ያሉዋቸው ናቸው።

"ተፅዕኖው ከባድ ነው፤ በጣም ከባድ፤ ምክንያቱም እዚህ ያለው ሰው [አዲስ አበባ] እየሆነ ያለውን ነገር አይረዳውም" ስትል ታብራራለች።

"ለምሳሌ በዕለቱ የቤት ኪራይ መክፈል የነበረበት ጎረቤቴ አለ። የተፈጠረውን በሚገባ ስላልተረዳ ለቤቱ ባለቤትም ምንም ነገር ማስረዳት አልቻለም። ስለዚህ ከየትም ፈልጎ መክፈል አልያም ቤቱን ለቆ መውጣት ይኖርበታል፤ ጭንቅ ውስጥ ነው ያለው።" ስትል የተፈጠረውን በምሳሌ አስረድታለች።

ፀደይ የራሷን ሁኔታ በማንሳትም "በቴሌ ብር መጠነኛ ገንዘብ አለኝ፤ ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት ያኖረኛል፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ምን እንደምሆን አላውቅም" ትላለች።

አክላም ኤቲኤም ለመጠቀም የይለፍ ቃሎች መጥፋታቸውን ወይም ጊዜያቸው ያለፈ እንደሚሆን ታስረዳለች።

ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት የምታስረዳው አገልግሎቱ ላለፉት ስምንት ወራት ያህል በትግራይ ውስጥ እየሰራ እንዳልነበረ ነው።

አክላም "እኔ ራሴ ሁለት ካርዶች ነበሩኝ። አንደኛው [የወጋገን] የይለፍ ቃል ረስቼዋለሁ፣ ሁለተኛው ደግሞ [የንግድ ባንኩን] ካርዱ ሳልይዝ ነው የመጣሁት" ስትል ተናግራለች።

ቢቢሲ ሰኞ ዕለት ለግለሰቦቹ ቃለ መጠይቅ ባደረገበት ወቅት አካውንታቸው የተዘጋባቸው ግለሰቦች በአንዳንድ የአዲስ አበባ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በአካል ተገኝተው እንዲያመለክቱ ተጠይቀዋል።

አንዳንዶቹ ሂሳባቸውን መክፈት እና መጠቀም መቻላቸውን ተናግረዋል።

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባንክ ባለሙያ ለቢቢሲ የአንበሳና የወጋገን ባንኮች አመራሮች ሰኞ ዕለት ተገናኝተው ከንግድ ባንክ ጋር በተመሳሳይ መልኩ አገልግሎት ለመጀመር ውሳኔ ለማስተላለፍ መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገረው የባንኩ ባለሞያ በትግራይ ክልል የተከፈቱ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀሱ የሚል የጽሑፍ ትዕዛዝ ስለመኖሩ እንደማያውቅ ተናግሯል።

ሆኖም መንግሥት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የባንክ አካውንት የሚዘጋበት ምክንያቶች እንዳሉት ይናገራል።

ይህ ሊሆን የሚችለው ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ወይም በግጭቱ ውስጥ ያሉ ወገኖች ገንዘብ እንዳያገኙ ለመከላከል ሊሆን እንደሚችል ይገምታል።